ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፖርት ሱዳን ይፋዊ ጉብኝት አደረጉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሱዳን ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለማግዝ የሱዳን የወደብ ከተማ ወደ ሆነችው ፖርት ሱዳን ሱዳን ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ከአገሪቱ ጦር ኃይሎች አዛዥ ጋር ተወያዩ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት እንዳለው “ጉዞው ለሱዳን መረጋጋት የሚያከናውኑት ጥረት ቀጣይ እርምጃ ነው” ሲል ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሱዳን ያቀኑት በእርስ በርስ ጦርነት ለምትታመሰው አገር ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማበጀት አዲስ አበባ ላይ ረቡዕ ሐምሌ 3/ 2016 ዓ.ም ፖለቲካዊ ውይይት በታቀደበት ወቅት ነው።
ሁለቱን የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ወደ ሰላም ለማምጣት ያለመው የአዲስ አበባው ውይይት ለአምስት ቀናት እንደሚቆይ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ሰኔ 14/ 206 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ገልጾ ነበር።
የሱዳን ዜና ወኪል - ሱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም. ፖርት ሱዳን አየር ማረፊያ ሲደርሱ፣ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ መንበር እና የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሌተናንት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን እና ሌሎች ባለሥልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፖርት ሱዳን ያደርጉት ጉብኝት ሱዳን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ከገባች በኋላ በአንድ አገር መሪ የተደረገ ይፋዊ ጉብኝት ነው ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከጄኔራል አል ቡርሐን ጋር ውይይት ከማድረጋቸው በተጨማሪ በኢትዮጵያ እያካሄዱት እንዳለው ሁሉ እዚያም ችግኝ ተክለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖርት ሱዳን ጉብኝት እና የሚያደርጉት ውይይት ነገ [ረቡዕ] ከሚጀምረው የአዲስ አበባው ውይይት ጋር ግንኙነት እንዳለው የተባለ ነገር የለም።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ከሱዳን የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ፓናል እና ከኢጋድ ጋር በመተባበር በሱዳን ያለውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለመቋጨት፣ ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ወደነበረበት ለመመለስ እና ሕዝብ መራሽ መፍትሄ ለማግኘት ይህ ውይይት ትኩረት እንሚያደርግ የምክር ቤቱ መግለጫ አስታውቋል።
ከአዲስ አበባው ቀደም ብሎም በግብፅ መዲና ካይሮ ውይይት እንደሚደረግም የአፍሪካ ኅብረት ከሳምንታት በፊት ባወጣው በመግለጫው አመልክቶ ነበር።
ምክር ቤቱ “ጎረቤት አገራት ከአፍሪካ ኅብረት እና ከኢጋድ ጋር በመሆን በሱዳን በተጀመረው ሰላም የማምጣት ጥረት ላይ ላላቸው ሚና ምስጋናውን” ገልጿል።
የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር በኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የሚመራ ኮሚቴ በማቋቋም በአጭር ጊዜ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪዎች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች እንዲያመቻች ተልዕኮ እንደተሰጠው መግለጫው አክሏል።
ምክር ቤቱ “ወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ጦርነቱን እያባባሱ ያሉ የውጭ ተዋንያን ከተግባራቸው ይቆጠቡም” አሳስቧል።
በሙሴቬኒ የሚመራው ኮሚቴ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እና ከአፍሪካ የመረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት (ሲአይኤስኤስ) ጋር በመተባበር “ለተፋላሚዎች ወታደራዊ፣ የገንዘብ እና የፖለቲካዊ ድጋፍ የሚሰጡ የውጭ አካላትን የመለየት ኃላፊነት ተሰጥቶታል” ተብሏል።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በጄኔራል አል ቡርሐን በሚመራው በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በጄኔራል ዳጋሎ በሚመራው በፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ሱዳን ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።
አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አል ቡርሐን ጊዜያዊ መቀመጫ ወደ ሆነችው ፖርት ሱዳን የሚያደርጉት ጉብኝት እና ውይይት በሱዳን ሰላም ለማምጣት የሚደረገው ጥረት አካል እንደሆነ ተነግሯል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በአዋሳኝ ድንበራቸው ላይ የይገባኝል ውዝግብ እና በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ አለመግባባት ያላቸው ሲሆን፣ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ግን ጉዳዩ እምብዛም ተነስቶ አያውቅም።
ኢትዮጵያም በተለያዩ አጋጣሚዎች በሱዳን ጦርነት ውስጥ ከየትኛውም ኃይል ጋር እንዳማትወግን ስትገልጽ ቆይታለች።
ባለፈው ሳምንትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር “ከሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች 100 ፐርሰንት ገለልተኛ አቋም ይዘን፣ ሁለቱም ወደ ሰላም እንዲመጡ ስንሠራ ቆይተናል፤ አሁንም የምንሠራው በዚያው መንገድ ነው” ብለው ነበር።
ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እየተፋለሙ ያሉት የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አገሪቱን ለሰብዓዊ ቀውስ እና እልቂት እየዳረጓት ይገኛሉ።
ጦሩ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሚቆጣጠራቸው ስፍራዎች ላይ ምግብ እና ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ አድርጓል በሚል እየተከሰሰ ነው።
በተጨማሪም የፈጥኖ ደራሹ ኃይሉ በከፍተኛ ምዝበራ ላይ በመሳተፍ እየተወቀሰ ሲሆን፣ ሁለት ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሉባትን ኤል ፋሽርን ከአንድ ወር በላይ በከበባ ውስጥ አስገብቶ ቆይቷል።
አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሕጻናት የተፈናቀሉባት ሱዳን፣ በሕጻናት ተፈናቃዮች አንጻር ከዓለም ከፍተኛውን አሃዝ ይዛለች። ይህም የአገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታን አጣብቂኝ ውስጥ ይከተዋል ተብሏል።