ዩክሬንና ሩሲያን ለማሸማገል የሄደው የአፍሪካ ልዑክ ያሳካው ነገር አለ?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ባለፈው ሳምንት ለሽምልግልና ኪየቭና ሞስኮ ተጉዘው ነበር።
ጉዞው ጦርነት አስቁሞ ሰላም ለማምጣት ያለመ ነው። የመጣ ሰላምም የቆመ ጦርነትም የለም፤ ለጊዜው።
ራማፎሳ ግን ያደረጉትን ጉዞ ታሪካዊ ብለውታል። አፍሪካ 'አህጉር ተሻግራ ለማስታረቅ ያደረገችው ታሪካዊ ጉዞ' ሲሉ አዳንቀውታል። ለምን?
ከራማፎሳ ጋር ከሰባት አገራት የተወጣጡ መሪዎችና ተወካዮች አብረው ተጉዘዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲንን አግኝተዋል፤ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪንም እንዲሁ።
ይህ ጉዞ ልዩ የሚያደርገው ከራስ ችግር ወጥታ በማታውቅ አህጉር፤ በጦርነት በምትቆላ አህጉርና መሪዎቿ መመራቱ ነው።
ለዚያውም ብልጹግ አገራትን ለማስታረቅ የተደረገ መሆኑ።
በእርግጥ አፍሪካ ከጦርነቱ ሩቅ አይደለችም፤ የዩክሬን የጦርነቱ ዳፋ ሕዝቦቿን አመሰቃቅሏል።
ስለዚህ የአፍሪካ መሪዎች የዩክሬን ነገር ይመለከተናል ቢሉ ግራ አይሆንም።
ይህ በፕሬዝደንት ራማፎሳ የተመራው ቡድን ከግብጽ፣ ሴኔጋል፣ ከኮንጎ ብራዛቪል፣ ኮሞሮስና ዛምቢያ እንዲሁም ኡጋንዳ ተወካዮችን አካቷል።
ዐሥር የሰላም ሐሳቦችንም አቅርቧል። ከነዚህ መሀል የሩሲያና የዩክሬን ሉአላዊነት መከበር፣ እንዲሁም ያልተቋረጠ የስንዴ አቅርቦት እንዲኖር የሚል ይገኝበታል።
ከዚህ ባሻገር ጦርነቱ እንዲጋጋም ከሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ሁለቱም እንዲቆጠቡ፣ ለንግግር በራቸውን እንዲከፍቱ፣ የጦር እስረኞችን እንዲፈቱ የሚል አለበት።
ሩሲያና ዩክሬን ለሽምልግናው በጎ ምላሽ ቢያሳዩም ፑቲን ቅዳሜ ዕለት አብዛኛዎቹን የስምምነት ሐሳቦችን ውድቅ አድርገዋል። ዘለንስኪም ቢሆን ቀዝቃዛ ምላሽ ነው ያሳዩት።
ጦርነቱን ከአፍሪካ መነጽር ካየነው ብዙ ጉዳት አምጥቷል።
የማዳበሪያና የስንዴ እጥረት አስከትሏል። ከሩሲያና ከዩክሬን ዕቃ ያስገቡ የነበሩ የአፍሪካ አገራትን ጎድቷል። በመላው አፍሪካ የዋጋ ንረትን አባብሷል።
የአፍሪካ ዴቨሎፕመንት ባንክ እንደሚለው ጦርነቱ በአፍሪካ አህጉር 30 ሚሊዮን ቶን ስንዴ እጥረት እንዲከሰት ቀጥተኛ ምክንያት ሆኗል።
በዚህ ላይ ፑቱን የዩክሬን ስንዴ ከዚህ ወዲያ አገራቸው ቁጥጥር ሥር ባለ ወደብ በኩል እንዳያልፍ አደርጋለሁ ሲሉ ይዝታሉ።
እርሳቸው ወደብ ካልፈቀዱ በአፍሪካ ዳቦ ይወደዳል።
በቱርክና በተባበሩት መንግሥታት አሸማጋይነት ሩሲያ ወደቧን ለዩክሬን ስንዴ ማለፊያ ለማድረግ ፈርማ ነበር። ፑቲን ይህን ፊርማ ከእንግዲህ አላድስም እያሉ ነው።
ፑቲን እንዲህ እያሉ ሲዝቱ ይህ የመጀመርያቸው አይደለም።
ነገር ግን ዛቻቸውን ከተገበሩት በአፍሪካ ሌላ ምስቅልቅል ይፈጥራል።
ፖለቲካውን በቅርብ የሚከታተሉ ግን ፑቲን ይህን አያደርጉም ይላሉ፤ ምክንያቱም የአፍሪካ አገራትን ማስቀየም አይሹም።
አፍሪካ ይህን የሩሲያን ወረራ እንድታወግዝ ብርቱ ግፊት እየተደረገባት ነው።
በተለይ ዘለንስኪ ሁሉም አገራት ሩሲያን በማውገዝ ሩሲያዊያን አገራቸው ከዓለም የተገለለችው በፑቲን ፖሊሲ እንደሆነ እንዲያውቅ መደረግ አለበት ብለው በጽኑ ያምናሉ።
ይሁንና ይህን የሽምግልና ጉዞ ካደረጉት መካከል በቀጥታ ሩሲያን ወራሪ ብሎ ለማውገዝ የሚደፍር የለም።
እንዲያውም ኡጋንዳና ደቡብ አፍሪካ የፑቲን ጥብቅ ወዳጅ እንደሆኑ ነው የሚታመነው።
ባለፈው ወር የአሜሪካ አምባሳደር ደቡብ አፍሪካ የገለልተኝነት ስምምነትን በመጣስ ለሩሲያ ጦር መሣሪያ ታቀብላለች ሲሉ በይፋ ከሰዋታል።
ደቡብ አፍሪካ ግን ይህ ሐሰት ነው ትላለች።
ከዚህ ሌላ ብሪክስ በሚል ምሕጻር የሚጠራው ቡድን አባል የሆነችው ደቡብ አፍሪካ በመጪው ነሐሴ ጉባኤ ታሰናዳለች።
ይህን ጉባኤ ፑቲን ይታደሙታል ተብሎ ይጠበቃል።
ደቡብ አፍሪካ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ማዘዣ የወጣባቸውን ፑቲንን አሳልፋ ትሰጣለች ወይ የሚለው የሚታይ ጉዳይ ነው።
ዞሮ ዞሮ የዚህ ጉዞ ዋነኛ ዓላማ ሁለቱን ተዋጊ ኃይሎች እንዲደራደሩ ማግባባት ነበር። ይህ ደግሞ አልተሳካም።
ከዚህ የአፍሪካ መሪዎች ሽምግልና ጥረት በፊትም ሆነ በኋላ የሁለቱም አገር መሪዎች ይህ እንደማይሆን በማያሻማ ቋንቋ ተናግረዋል።
ዩክሬን ለድርድር የምቀመጠው ድንበሬ በ1991 ዓ/ም (እአአ) ወደነበረበት ከተመለሰልኝ ብቻ ነው ትላለች።
ይህ ማለት ሩሲያ በዚህ ጦርነት ከጠቀለለቻቸው ሰፋፊ አውራጃዎች ብቻ ሳይሆን ከክሪሚያ ባሕረ ሰላጤ ጭምር መውጣት አለባት።
የሚፈጸም አይመስልም።
ሩሲያ በበኩሏ ወደ ጠረጴዛ የምመለሰው ኪየቭ አሁን ያላትን ግዛት ማለትም አዲሱን እውነታ ተቀብላ ለመቀጠል ስትስማማ ብቻ ነው ብላለች።
ይህ ደግሞ ለዩክሬን ሽንፈት ብቻ ሳይሆን ውርደትም ነው የሚሆነው።
ለዚህም ነው በአፍሪካ ሽምግልና ጠብ ያለ ነገር የለም ያስባለው።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት ከአፍሪካ ተወካዮች ጋር መነጋገሩ ወደፊትም ቢሆን ይቀጥላል።
ምንም እንኳ ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ለመነጋገር ዝግጁ እንዳልሆኑ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ይፋ ቢያደርጉም ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ግን የአፍሪካው ልዑክ ለንግግር አዲስ በር ከፍቶ ተመልሷል ብለው ይከራከራሉ።
ራማፎሳ አገራቸው በችግር ተተብትባለች።
የኃይል ቀውስ ገጥሟታል ደቡብ አፍሪካ።
መሠረተ ልማት እየፈራረሰባት ነው ደቡብ አፍሪካ።
ዜጎች ሥራ አጥነት እያንከላወሳቸው ነው በደቡብ አፍሪካ።
የወንጀል ብርካቴ ሕዝብን አማሮታል በደቡብ አፍሪካ።
ያም ሆኖ ራማፎሳ በዓለም መድረክ አሸናፊ ሆነው ለመታየት እየተፍጨረጨሩ ይመስላል።












