ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኮቪድ 19 መነሻ የቻይና ቤተ ሙከራ ሊሆን እንደሚችል የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ተናገሩ
የአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ( ኤፍቢአይ) የኮቪድ 19 መነሻ የቻይና መንግሥት የሚቆጣጠረው ላብራቶሪ ሊሆን ይችላል ብሎ እንደሚያምን የተቋሙ ዳይሬክተር ክርስቶፈር ውሬይ ተናገሩ።
ዳይሬክተሩ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት ኤፍቢአይ የወረርሽኙ መነሻ በቤተ ሙከራ ውስጥ ያጋጠመ ክስተት ሊሆን እንደሚችል ገምግሟል።
ኤፍቢአይ ወረርሽኙ እንዴት እንደተቀሰቀሰ ውስን ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ቻይና በወቅቱ ወረርሽኙ በዉሃን ከሚገኝ ቤተ ሙከራ አምልጦ የወጣ ነው መባሉን የተቃወመች ሲሆን የቀረበባትን ውንጀላም “ ስም ማጥፋት” ብለዋለች።
ዳይሬክተሩ የሰጡት አስተያየት የተሰማው በቻይና የአሜሪካው አምባሳደር ቻይና ስለ ኮቪድ ወረርሽኝ መነሻ ሐቀኛ እንድትሆን ጥሪ ካቀረቡ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ማክሰኞ ዕለት በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ቻይና “ የዓለም አቀፍ ወረርሽኙን ምንጭ ለማወቅ የሚደረገውን ጥረት ለመከላከልና ለማድበስበስ እየሞከረች ነው። ይህም በጣም የሚያሳዝን ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።
አንዳንድ ጥናቶች ቫይረሱ በቻይናዋ ዉሃን ከተማ ምን አልባትም በከተማዋ የባሕር ምግቦች እና የዱር እንስሳት ገበያ ከእንስሳት ወደ ሰው መዛመቱን አመላክተዋል።
ይህ ገበያ በኮሮናቫይረስ ላይ ምርምር ካደረገው ቤተሙከራ፣ ዉሃን የቫይረስ ጥናት ተቋም የሚርቀው በ40 ደቂቃ የመኪና ጉዞ ነው።
ሌላ የአሜሪካ መንግሥት ተቋማትም ኤፍቢአይ ከደረሰበት ድምዳሜ ላይ የደረሱ ሲሆን በግኝታቸውም በቫይረሱ አመጣጥ ዙሪያ የተለያየ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የአሜሪካ ሚዲያ እሁድ እለት እንደዘገበው የአሜሪካ ኢነርጂ መሥሪያ ቤት፣ በግኝቱ ዝቅተኛ መተማመን እንዳለው በመግለጽ ኮቪድ ከቤተ ሙከራ አመልጦ የወጣ ቫይረስ እንደሆነ ገምግሟል። ተቋሙ ቀደም ብሎ ቫይረሱ እንዴት እንደተቀሰቀሰ እንደማይታወቅ ገልጾ ነበር።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ስለኮቪድ ወረርሽኝ መነሻ ለማወቅ መንግሥታቸው የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ የዋይት ሃውስ ብሔራዊ የደኅንነት ካውንስል ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢይ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ እስካሁን አሜሪካ ግልጽ የሆነ መግባባት ይጎድላታል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት “ እዚያ ላይ ገና አልደረስንም።የሆነ ነገር ካገኘን ለአሜሪካ ሕዝብ እና ለምክርቤቱ ለመግለጽ ዝግጁ ነን።ይህንን ደግሞ እናደርገዋለን” ብለዋል።
እአአ በጥቅምት 2021 ከአሜሪካ ከፍተኛ የስለላ ባለሥልጣን የወጣ አንድ መረጃ እንዳመለከተው አራት የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ቫይረሱ በቫይረሱ ከተያዘ እንስሳ አሊያም ከተዛማጅ ቫይረስ መከሰቱን ዝቅተኛ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ለወራት ያህል ስለ ወረርሽኙ አስከፊነትም ሆነ ከቤተ ሙከራ አምልጦ ስለመውጣቱ በስፋት ውድቅ ተደርጎ ነበር። ከፍተኛ የጤና ባለሠልጣናትም ቫይረሱ ከማምለጡ በፊት በቤተ ሙከራ የተፈጠረ ሊሆን ይችላል መባሉን በይፋ አጣጥለውታል።
የዓለም ጤና ድርጅት ከቤተ ሙከራ አምልጦ ወጥቷል መባሉን “ የማይሆን ነው” ያለ ሲሆን፤ ነገር ግን በምርመራው ላይ ከፍተኛ ትችት ከደረሰበት በኋላ፣ የተቋሙ ዳይሬክተር ጀኔራል አዲስ ምርመራ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል። “ ሁሉም መላ ምቶች ቀርበዋል ተጨማሪ ጥናት ግን ያስፈልጋል” ብለው ነበር ዳይሬክተሩ።
ኮቪድ 19 በ2019 መጨረሻ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተ ሲሆን ወደ ሰባት ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።