ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቦይንግ 737 ማክስ አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ለአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ቅሬታቸውን አሰሙ
በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ በተከሰከሱት ሁለት የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ሳቢያ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎች በአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት እና በቦይንግ መካከል በተደረሰው ስምምነት ላይ ቅሬታቸውን አሰሙ።
ተጎጂ ቤተሰቦቹ እአአ በ2021 የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ከአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ጋር የደረሰውን ስምምነት በመቃወም ማብራሪያ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ በነበረ የቴክኒክ ችግር ምክንያት በኢንዶኔዢያ እና በኢትዮጵያ አየር መንገዶች ላይ በተለያዩ ጊዜያት በደረሰው አደጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሕልፈት መዳረጋቸው ይታወሳል።
በእነዚህ አደጋዎች የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች ቦይንግን ከሰው ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል። ቦይንግም ለደረሰው ጉዳት ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።
ቤተሰቦቻቸውን በሁለቱ አደጋዎች ያጡት ሰዎች በመሥሪያ ቤቱ እና በቦይንግ መካከል የተደረሰው ስምምነት፣ አውሮፕላን አምራች ኩባንያው “የወንጀል ክስ ሳይመሠረትበት እንዲያመልጥ” በማድረጉ ማብራሪያ መጠየቃቸውን ዘገባው ይጠቁማል።
ባለፈው ወር አሜሪካዊው ዳኛ ሪድ ኦኮነር ቴክሳስ ውስጥ ባሳለፉት ውሳኔ፣ በሁለቱ የ737 ማክስ አውሮፕላን ደጋዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን “የወንጀል ሰለባ” ናቸው ብለዋል። ምን ዓይነት ማካካሻ መሰጠት እንዳለበት እንደሚወስኑም ዳኛው ተናግረዋል።
እአአ በ2018 እና በ2019 በኢንዶኔዥያ እና በኢትዮጵያ የተከሰቱት አደጋዎች ቦይንግ 20 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንዲያወጣ ከማድረጋቸው ባሻገር 737 ማክስ አውሮፕላኖች ለ20 ወራት ከበረራ እንዲታገዱም ምክንያት ሆነዋል።
ከሁለቱ አደጋዎች በኋላ የአሜሪካ ኮንግረስ የአውሮፕላን ፈቃድ አሰጣጥ ማሻሻያ ሕግ አውጥቷል።
የሟቾች ቤተሰቦች እና ጠበቆቻቸው አርብ ዕለት ከመንግሥት ጠበቆች ጋር መገናኘታቸውንና በቦታው ያልነበሩ ሰዎች ደግሞ በበይነ መረብ ስብሰባውን እንደተካፈሉ የሮይተርስ ዘገባ ይጠቁማል።
የሟቾቹ ቤተሰቦች የአሜሪካ መንግሥት “ዋሽቶናል፣ በምሥጢራዊ ሂደት መብታችንን ቀምቶናል” ሲሉ ለዳኛ ሪድ ኦኮነር ተናግረዋል።
እአአ በ2021 ቦይንግ አውሮፕላኑ ላይ ስላሉ ግድፈቶች ይፋ ካለማድረጉ እንዲሁም ከማጭበርበር ጋር በተያያዘ ክስ 2.5 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል ከተደረገ በኋላ የተሰጠው ያለመከሰስ መብት እንዲነሳና ተጠያቂ እንዲደረግ አሳስበዋል።
ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በኢትዮጵያ እና በኢዶኔዢያ ተከስክሶ የ346 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ በቀረረበት ክስ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ለመክፈል መስማማቱ ይታወሳል።
ቦይንግ ስለ 737 ማክስ አውሮፕላኑ ዲዛይን ከአሜሪካ የደኅንነት እና ጥንቃቄ ባለሙያዎች መረጃዎችን በመደበቅ ለተመሰረተበት የወንጀል ክስ ነበር ቅጣቱን ለመክፈል የተስማማው።
በወቅቱ የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ኩባንያው “ከግልጽነት ይልቅ ትርፍን” አስቀድሟል ብሎ ነበር።
ቦይንግ ለመክፈል ከተስማማው ገንዘብ ውስጥ 500 ሚሊዮን ዶላሩ በአውሮፕላኑ አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ እንደሚከፈልም በወቅቱ ተገልጿል።
ቀደም ሲል በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦች በአሜሪካ መንግሥት ላይ ሕጋዊ ጥያቄ አቅርበው ነበር።
የሟቾች ቤተሰቦች፣ አሜሪካ ቦይንግ ራሱን ከወንጀል ክስ የመከላከል ዋስትና እንዲያገኝ የሚያስችለውን ስምምነት በምሥጢር አዘጋጅታለች ሲሉ መክሰሳቸው አይዘነጋም።
የ24 ዓመት ልጇን በአደጋው ያጣችው ናዲያ ሚልሮን “የአሜሪካ የፍትሕ ቢሮ ከቦይግ ጋር በምሥጢርና በሕገ ወጥ ሁኔታ የደረሰበትን ስምምነት ማስጠበቁ ያሳዝናል። ይህም የተጎጂዎች ድምጽ ያልተካተተበትና ቦይንግን ያለ ተጠያቂነት የሚያሳልፍ ነው” ስትል ለሮይተርስ ተናግራለች።
ቦይንግ እንዲሁም የፍትሕ ቢሮውም ቦይንግ የተጣለበትን 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ከተስማማ በኋላ በድጋሚ ጉዳዩ መነሳቱን ተቃውመዋል።
ከ2.5 ቢዮን ዶላር ቅጣቱ መካከል 500 ሚሊዮን ለተጎጂዎች የሚሰጥ፣ 243.6 ሚሊዮን በቅጣት የሚከፈል እና 1.7 ቢሊዮን ለአየር መንገዶች ካሳ የሚከፈል ነው።
የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ስምምነቱን መቀልበስ እንደሌለበት ገልጾ “ውሳኔው ከተቀለበሰ ካሳ የተሰጣቸውን ተጎጂዎች ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል” ብሏል።
የፍትሕ ቢሮው፣ ቦይንግ የደኅንነት መመሪያ ለውጦችን እንዲያደርግ ጫና ማሳደር የሚችለው ስምምነቱ ከተከበረ እንደሆነም አክሏል።
ሆኖም ግን ከተጎጂዎች ቤተሰቦች የተነሳውን ጥያቄ የፍትሕ ቢሮ ችላ እንደማይለው አስታውቋል።
ቦይንግ በበኩሉ፣ ክሱን በድጋሚ ለመክፈት የሚደረግ ጥረት እንደሚቃወም ለፍርድ ቤት ገልጿል።
ቦይንግ “ያልተጠበቀ፣ ኢ-ፍትሐዊና የማይሳካ ነው” ሲል ሂደቱን ገልጾ፣ “ምርመራ የተደረገበት አካል ከመንግሥት ጋር ከተደራደረ በኋላ ጉዳዩን የመዝጋት መብት አለው” ሲልም አክሏል።
ስምምነቱን ለሁለት ዓመታት እየተገበረ እንደሆነም ኩባንያው ተናግሯል።
በሁለቱ አውሮፕላኖች ላይ የደረሰውን አሰቃቂ አደጋ ተከትሎ ለረጅም ጊዜ ከበረራ ውጪ እንዲሆን ተደርጎ የነበረው እጅግ ዘመናዊው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አስፈላጊው ማስተካከያ እና ፍተሻ ከተደረገበት በኋላ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ በዓለም ዙሪያ ያሉ አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ወደ ሥራ መመመለሳቸውን አስታውቀዋል።