ቦይንግ ከ737 ማክስ ጋር በተያያዘ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ

ቦይንግ ስለ 737 ማክስ አውሮፕላኑ ዲዛይን ከአሜሪካ የደኅንነት እና ጥንቃቄ ባለሙያዎች መረጃዎችን በመደበቅ ለተመሰረተበት የወንጀል ክስ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ለመክፈል ተስማማ።

የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ እንዳለው ከሆነ ኩባንያው "ከግልጽነት ይልቅ ትርፍን" አስቀድሟል።

ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በኢትዮጵያ እና በኢዶኔዢያ ተከስክሶ የ346 ሰዎች ህይወት አልፏል።

ቦይንግ ለመክፈል ከተስማማው ገንዘብ ውስጥ 500 ሚሊዮን ዶላሩ በአውሮፕላኑ አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ የሚከፋፈል ይሆናል።

ቦይንግ እንዳለው ይህ ስምምነት ኩባንያው "ያለበት ጉድለት" ምን ያህል መሆኑን ያሳያል።

የቦይንግ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ዴቪድ ካልሁን እንዳሉት "ወደ እዚህ ስምምነት መግባታችን ትክክለኛው ነገር እንደሆነ በጽኑ አምናለሁ፤ ይህም ከእሴቶቻችን እና ከሚጠበቅብን ምን ያህል ወደ ኋላ መቅረታችንን ያሳያል።"

"ይህ ስምምነት ሁላችንንም የሚያስታውሰን ለግልጽነት የገባነው ግዴታ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ፤ እንዲሁም አንዳችንም እንኳን እርሱን ሳናሟላ ብንቀር መዘዙ የከፋ መሆኑን ነው።"

የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ እንዳለው ከሆነ የቦይንግ ባለስልጣናት በኢንዶኔዢያ እና በኢትዮጵያ ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያት ስለሆነው ኤምካስ የተባለው አውቶማቲክ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ ስላለ ለውጥ መረጃ ደብቀዋል።

ይህ ውሳኔ የሚያሳው የአውሮፕላን አብራሪው ስልጠና መመሪያ ስለሥርዓቱ በቂ መረጃ አለመያዙን፣ ይህም በተሳሳተ መረጃ የአውቶማቲክ ሥርዓቱ የአብራሪውን ውሳኔ እንደሚሽረውና፣ ይህም አውሮፕላኑ ከማኮብኮቢያው በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አፍንጫውን አዘቅዝቆ ቁልቁል እንዲምዘገዘግ እንደሚያደርገው ነው።

ቦይንግ ከምርመራ ባለሙያዎች ጋር ለስድስት ወር ያህል ትብብር አለማድረጉን የፍትህ ቢሮው ጨምሮ ተገልጿል።

"በላየን አየር መንገድ በረራ 610 እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ 302 አውሮፕላኖች ላይ የደረሰው አሳዛኝ አደጋ፣ በዓለማችን ቀዳሚ የንግድ አውሮፕላኖች አምራች የሆነው ኩባንያ ሠራተኞች የማጭበርበር እና ማታለል ባሕሪያቸውን አጋልጧል" ያሉት ደግሞ ረዳት ተጠባባቂ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዴቪድ በርንስ ናቸው።

"የቦይንግ ሠራተኞች 737 ማክስ አውሮፕላንን በሚመለከት መረጃን ከተቆጣጣሪው መስሪያ ቤት በመደበቅ፣ ስህተታቸውን ለመሸፋፈን በመተባበር ከደኅንነት ይልቅ ትርፍን አስቀድመዋል" ብለዋል።

ኩባንያው ሊከፍል ከተስማማው አብዛኛው ገንዘብ፣ 1.7 ቢሊዮን ዶላሩ ለተጎጂ ቤተሰቦች የሚሰጥ ሲሆን፣ የተወሰነውም ተከፍሏል ተብሏል።

ኩባንያው 243.6 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ለመክፈልም ተስማምቷል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሕይወታቸወን ላጡ ቤተሰቦች ጥብቅና የቆሙት ባለሙያዎች ግን ይህ የኩባንያው ውሳኔ የመሰረቱትን ክስ እንዲያቋርጡ እንደማያደርጋቸው ገልፀዋል።

ጠበቆቹ አክለውም ሁሉም የኩባንያው 737 ማክስ አውሮፕላኖች ደኅንነት በገለልተኛ ወገን እስኪረጋገጥ ድረስ ወደ በረራ እንዲገቡ መፈቀድ የለበትም ብለዋል።

የአሜሪካ ደኅንነት ተቆጣጣሪዎች ከታኅሣስ ወር ጀምሮ አውሮፕላኖቹን ለበረራ ዝግጁ ናቸው በማለታቸው ወደ ሥራ ተመልሰዋል።