‘አማዞን ጫካ ውስጥ የተገኙት ሕፃናት እናት፤ ልጆቿ እሷን ትተው እራሳቸውን እንዲያድኑ ነግራቸዋለች’

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከ40 ቀናት በኋላ በጥቅጥቁ የአማዞን ጫካ ውስጥ የተገኙት ልጆች እናት ሕፃናቱ እሷን ትተዋት እርዳታ ፍለጋ እንዲሄዱ እንዳደረገች ተሰምቷል።
እናት ማግዳሌና ሙኩቱይ ከአውሮፕላን አደጋው በኋላ ለአራት ቀናት በሕይወት መቆየቷን የልጆቹ አባት ማኑዌል ራኖኩዌ ይናገራል።
አባት ትልቋ ልጄ ነገረችኝ ብለው እንደገለጹት ከሆነ እናትየው ለመሞት እያቃሳተች ሳለ ልጆቿ እሷን ትተው በመሄድ ለእራሳቸው እርዳታ እንዲሹ ነግራቸዋለች።
ዕድሜያቸው 13፣ 9፣ 5 እና 1 የሆኑት እህት እና ወንድማማቾች ከእናታቸው እና ከአብራሪዎች ጋር ሆነው ይጓዙበት የነበረው አውሮፕን ከተከሰከሰ በኋላ፣ ሦስቱ አዋቂዎች ሕይወታቸው አልፎ በሕይወት የተረፉት አራት ታዳጊዎች 40 ቀናት በጫካ ለመቆየት ተገደዋል።
ልጆቹ አርብ ከጥቅጥቁ ጫካ በሄሊኮፕተር እንዲወጡ ተደርገዋል። ዋና ከተማዋ ቦጎታ በሚገኝ አንድ ወታደራዊ ሆስፒታል ውስጥ እርዳታ እየተደረገላቸውም ይገኛሉ።
“የ13 ዓመት ልጄ ሌዝሊ እንደነገረችኝ ከሆነ እናታቸው ለአራት ቀናት ያክል በሕይወት ነበረች” ሲሉ አባት ከሆስፒታሉ ውጭ ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“ከመሞቷ በፊት እናታቸው ጠርታቸው 'እናንተ አሁን መሄድ አለባችሁ። አባታችሁ መልካም ሰው ነው። እኔ ያሳየኋችሁን ዓይነት ፍቅር ያሳያችኋል' ብላቸዋለች” ይላል አባት።
ልጆቹ እንዴት አድርገው እዚያ ጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ እንደቆዩ አዳዲስ መረጃዎች እየወጡ ነው። ተዓምራዊ የሆነው የልጆቹ የመትረፍ ዜና በርካቶችን አስደንቋል።
ሕፃናቱ ሲገኙ ከነበሩት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መካከል አንዱ የሆነው ኒኮላስ ኦርዶኔዝ ጎሜዝ ታሪኩን እንዲህ ያጋራል።
“ትልቋ ልጅ ሌዝሊ ትንሿን ልጅ በክርኗ ደግፋ ይዛት ወደእኔ እየሮጠች መጣች። ከዚያም 'ርቦኛል' አለችኝ” ይላል።
እሑድ የተለቀቀ አንድ አዲስ ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው፣ ልጆቹ አማዞን ጫካ ውስጥ ሳሉ በምግብ እጥረት በመጎዳታቸው ሰውነታቸው ገርጥቷል።
ማግዳሌና እና ልጆቿ በፈረንጆቹ ግንቦት 1/2023 ሴስና 206 በተባለችው አውሮፕላን አራራኩዋራ ወደተባለ ሥፍራ እያቀኑ ነው የአነስተኛዋ አውሮፕላን ሞተር የተበላሸው።
አውሮፕላኑ ሲከሰከስ እሷ እና ሁለቱ አብራሪዎች ሞተዋል።
ሬሳቸው በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት ሥፍራ ሲገኝ፣ አብረዋቸው የነበሩት ሕፃናት ግን እርዳታ ፍለጋ ወደ ጥቅጥቁ ጫካ ወጥተው ሄዱ።
የጠፉት ልጆች ጉዳይም ላለፉት ጥቂት ሳምንታት መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የእግር ዳና እና በከፊል ተበልቶ የተጣለ ፍሬ ባገኙ ቁጥር ተስፋቸው እያደር እየጨመረ በስተመጨረሻ ልጆቹ ተገኝተዋል።












