ግብፅ ሶማሊያን እደግፋለሁ ማለቷን ተከትሎ ሶማሊላንድ ‘የውጭ ጣልቃ ገብነት’ እንደምትቃወም ገለጸች

ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው ስምምነት ዙሪያ ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደምትቃወም ገለጸች።

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ጥር 13/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “በስምምነቱ ዙሪያ የሚነሱ ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንቃወማለን” ብሏል።

ከሶማሊያ ተለይታ ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ አቋሟን የገለጸችው ግብፅ ከሶማሊያ ጎን እንደምትቆም መግለጿን ተከትሎ ነው።

ግብፅ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው ሶማሊያ ጥያቄ ካቀረበች ከጎኗ ለመቆም ጣልቃ እንደምትገባ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ መናገራቸው ይታወሳል።

ሶማሊላንድ ይህንን ተክትሎ በሰጠችው መግለጫ፣ ከግብፅ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ከፍ አድርጋ እንደምትመለከት ገልጻለች።

ይሁን እንጂ በሶማሊላንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ከተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ማንኛውንም አይነት የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን እንድምትቃወም አስታውቃለች።

በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ላይ ያላትን ስጋትም እውቅና እንደምትሰጥም ገልጻለች።

ሶማሊላንድ “እንደ ሉዓላዊ አገር በተቋቋመ ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች አከብራለሁ” በማለት ገልጻለች።

በቀጠናው ፍላጎት ያላቸው አካላት “ቀጠናዊ መረጋጋትን እና አጋርነትን” በማረጋገጥ ላይ እንዲያተኩሩም ጠይቃለች።

ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በባሕር በር አጠቃቀም ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት ላይ ከደረሰች በኋላ ሶማሊያ ተቃውሞ ያቀረበች ሲሆን፣ ግብፅም በተደጋጋሚ የሶማሊያን አቋም ደግፋ አስተያየት ስትሰጥ ቆይታለች።

የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ከግብፅ መንግሥት በቀረበላቸው ግብዣ ወደ ካይሮ በመጓዝ ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር ከተወያዩ በኋላ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው ሁለቱ አገራት ከኢትዮጵያ አንጻር በጋራ እንሚቆሙ የተገለጸው።

ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ አገራቸው በሶማሊያም ሆነ በፀጥታዋ ላይ ምንም አይነት የደኅንነት ስጋት እንዲፈጠር እንደማትፈቅድ እና ለዚህም ግብፅ ጣልቃ እንድትገባ ከተጠየቀች ከሶማሊያ ጎን ትሰለፋለች ሲሉ ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ስምምነቱ በሶማሊያ ላይ የደኅንነት ስጋት የሚፈጥር አለመሆኑን ገልጸው፤ በቀጠናው ያሉ አንዳንድ ኃይሎች አጀንዳ በአፍሪካ ቀንድ ቀውስ መፍጠር ነው ብለዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “ኢትዮጵያ ለሰላምና ደኅንነት ቁርጠኛነቷ የሚገለጸው በውድ ልጆቿ ደምና ላብ ነው” ብለዋል።

አያይዘውም “ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጎረቤት ብቻ አይደሉም። ድንበርም ይጋራሉ። ቋንቋና ባህል የሚጋሩ ወንድማማች አገሮች ናቸው” ሲሉ አክለዋል።

የሶማሊላንድ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ደግሞ “ግብፅ በቀጠናው ሰላምና ምርታማ ግንኙነት ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት እንጋራለን” ብሏል።

ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በቀጣናው ከሚገኙ መሪዎች ጋር ተከታታይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ወደ አሥመራ እና ካይሮ ጉዞዎችን አድርገዋል።

የሶማሊላንድ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማትን ለማስፈን ከሁሉም ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን እና ትብብር እንደሚያደርግም መግለጫው አክሏል።

ሆኖም ግን ውጫዊ ጣልቃ ገብነትን “አጥብቀን እንቃወማለን” ሲል የሶማሊላንድ መንግሥት አቋሙን ገልጿል።

ከሦስት ሳምንታት በፊት ይፋ በተደረገው የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ለምታገኘው የባሕር ጠረፍ፤ በምላሹ ሶማሊያ እንደ አንድ ግዛቷ ለምትመለከታት ሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን ትሰጣለች ተብሏል።

ይህም ሶማሊያን በእጅጉ ያስቆጣ ሲሆን፣ በሉዓላዊነቷ ላይ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑን በመግለጽ ስምምነቱን አጥብቃ ተቃውማለች።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ከሶማሊያ እና ከደጋፊዎቿ በኩል ተቃውሞ ቢገጥማቸውም የፈረሙትን የመግባቢያ ስምምነት በአንድ ወር ውስጥ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።