ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳኑ ጄኔራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን ጉብኝት በአዲስ አበባ
ከተቀናቃኛቸው ጄኔራል ሐምዳን ዳጋሎ ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኙት የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀምነበር ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ለጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ።
ወራትን ባስቆጠረው እና በሱዳን ኃያላን ጄኔራሎች መካከል በሚደረገው ጦርነት ውስጥ የአገሪቱን ጦር ሠራዊት በመምራት እየተፋለሙ ያሉት ጄኔራል አል ቡርሐን አዲስ አበባ ሲደርሱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ በጄኔራል ዳጋሎ (ሄሜቲ) በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና በጄኔራል አል ቡርሓን በሚመራው የአገሪቱ ጦር መካከል የሚካሄደው ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ተባብሶ በርካታ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
ጄኔራል አል ቡርሐን ለጉብኝት ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው፣ የዳርፉር አስተዳዳሪ እና የአገሪቱ ደኅንነት አገለግሎት ኃላፊ ካሉበት የልዑካን ቡድን ጋር ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት በማኅበራዊ ገጹ ላይ እንዳለው “ሁለቱ መሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የጋራ በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።”
ከጥቂት ወራት በፊት ጄኔራል አል ቡርሐን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ እና የአካባቢው አገራት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ ሳይመጡ ቀርተው ነበር።
በዚህ ጉብኝት “በጋራ እና ወቅታዊ ጉዳዮች” ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ከመገለጹ ውጪ በተለይ የሚያተኩሩባቸው ጉዳዮች በዝርዝር አልተገለጹም።
ነገር ግን በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ዋነኛ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት እና በኢጋድ በኩል ግጭቱ እንዲቆም ጥረት ከሚያደርጉ አገራት መካከል አንዷ ናት።
እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል በግዛት ይገባኛል ምክንያት ያልተቋጨ ውዝግብ ያለ ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት በፊት የሱዳን ጦር አወዛጋቢ አካባቢዎችን መቆጣጠሩ ይታወቃል።
ከተቀሰቀሰ ስምንት ወራትን ባስቆጠረው በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት አስካሁን ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ቀያቸውን ለቀው ለመሰደድ መገደዳቸው ተዘግቧል።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ በኃያላኑ የአገሪቱ የጦር ጄኔራሎች በሚመሩት በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሱዳንን ቀውስ ውስጥ አስገብቷታል።
አስካሁን የትኛውም ወገን በጦርነቱ የበላይነትን ያልያዘ ሲሆን፣ ሁለቱ ኃይሎች ዋና ከተማዋን ካርቱምን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ከባድ ጦርነት እኣካሄዱ ይገኛሉ።
ባለፉት ወራት ጦርነት በማቆም ከስምምነት እንዲደረስ አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ድርጅት እንዲሁም የአካባቢው አገራት ለማሸማገል ጥረት ቢያደርጉም አስካሁን አልተሳካላቸውም።