የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ተስፋ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚያደርገውን ጉዞ ዛሬ ምሽት ከሴራ ሊዮን ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ይጀምራል።

የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ እንዲያስተናግዱ ተመርጠዋል።

በ16 ከተሞች በሚዘጋጀው ውድድር 48 አገራት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ቀደም በነበሩት የዓለም ዋንጫዎች 32 አገራት ብቻ ይሳተፉ ነበር።

በውድድሩ 9 የአፍሪካ አገራት በቀጥታ ይሳተፋሉ። ከምድባቸው ሁለተኛ ደረጃ ያስመዘገቡ አራት ቡድኖች በጥሎ ማለፍ መልክ ተጫውተው የሚያልፈው አንድ ቡድን ከሌሎች አህጉራት ቡድኖች ጋር በመጫወት ለዓለም ዋንጫው የመብቃት ዕድል ይኖረዋል።

አሁንም ከሜዳ ውጭ

የአፍሪካ አገራት ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ በሚደረጉ ፍልሚያዎች ይጀመራሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሴራሊዮን ጋር የሚያደርገውን የመጀመርያ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ያከናወናል።

ጨዋታው በሞሮኮዋ ኤል-ጀዲዳ ከተማ በሚገኘው ኤል-አብዲ ስታዲየም ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ላይ እንዲከናወን ቀጠሮ ተይዞለታል።

በአገሪቱ ያሉ ስታዲየሞች በቂ መሠረተ ልማቶችን አላሟሉም በሚል በመታገዳቸው ብሔራዊ ቡድኑ ቡድን በሜዳው ከተጫወተ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል።

በሜዳው ማድረግ የነበረበትን ጨዋታም በተለያዩ አገራት ለማከናወንም ተገዷል።

በዚህ ምክንያት ነው የዛሬው ጨዋታ በሞሮኮ እንዲከናወን የተወሰነው።

ጨዋታውን ሞዛምቢካዊው አልቫሲዮ ሴልሶ ከአንጎላዊያን ረዳቶቻቸው ጄርሰን ኤሚሊያኖ እና ኢቫኒልዶ ኦ ሳንቾ ይመሩታል። ሞዛምቢካዊው ጉዋምቤ በርናርዶ አራተኛ ዳኛ ናቸው።

ደቡብ ሱዳናዊው ራሳስ ሊብራቶ ደግሞ በኮሚሽነርነት መመደባቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል።

አዲስ አሰልጣኝ

ዋልያዎቹ በአዲስ አሰልጣኝ ይህንን ጨዋታ ያከናውናሉ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን በይፋ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን ከሰሞኑ ነው ያስታወቀው።

የቀድሞው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ውል መጠናቀቁን ተከትሎ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አሰልጣኝ ገብረመድህንን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እንዲሆኑ በአንድ ድምጽ ተስማምቶ መወሰኑን የፌደሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በወቅቱ ገለጸዋል።

አሰልጣኙ በቆይታቸው ጥቅማ ጥቅምን ሳይጨምር የተጣራ 250 ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ ያገኛሉ።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በበኩላቸው ቡድኑን በአሰልጣኝነት እንዲመሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ በደስታ ስለመቀበላቸው አንስተው የቅጥሩ ሂደት ይፋ ከመሆኑ በፊት ጀምሮ ለቀጣይ መርሃግብሮች ተጫዋቾችን ሲመለምሉ መቆየታቸውን ገልፀው ነበር።

አሰልጣኙ ልምድ ያላቸውና ወጣት ተጫዋቾችን ያሰባጠረ ቡድን እንደሚሠሩም አሳውቀዋል።

በብሔራዊ ቡድኑ በሚኖራቸው ቆይታ በስነ-ምግባር ሆነ በታክቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ቡድኑን ለመገንባት እንደሚጥሩም ገለጸዋል።

ተጫዋቾች

አሰልጣኝ ገብረመድህን ለመጀመሪያ ጨዋታቸው ለሠላሳ ገደማ ተጫዋቾች ጥሪ አቅርበው ነበር።

ጌታነህ ከበደ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ማግለሉን ተከትሎ ከስብስቡ ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል።

ሌላኛው አጥቂ አቡበከር ናስር ከደረሰበት ጉዳት ቢያገግምም ለብሔራዊ ቡድኑ እንደማይደርስ ተረጋግጧል።

አማካዩ ሽመልስ በቀለ በበኩሉ ከደረሰበት ጉዳት ባለማገገሙ ከብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውጭ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣርያ ላለበት ወሳኝ ጨዋታ 27 ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል።

በኋላ ላይም አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አራት ተጫዋቾችን ከስብስባቸው ውጭ በማድረግ ወደ ሞሮኮ የሚጓዙ የመጨረሻ 23 ተጫዋቾቻቸውን አሳውቀዋል።

የአፍሪካ አገራት ለዓለም ዋንጫ ማጣሪው በዘጠኝ ምድቦች ተደልድለው ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

እያንዳንዱ ምድብ 6 ቡድኖችን አካቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ አንድ ተደልድሏል።

በዚሁ ምድብ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ቡርኪናፋሶ፣ ጅቡቲ፣ ግብጽ፣ ጊኒ-ቢሳው እና ሴራ ሊዮን ተደልድለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ጨዋታውን ከሴራሊዮን ጋር ካደረገ በኋላ ሁለተኛ ጨዋታውን ከቡርኪና ፋሶ ጋር ያከናውናል።