ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲሱ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ዕቅዴ የጨዋታ ስልት በመቀየር ውጤት ማምጣት ነው አሉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት ገብረመድህን ኃይሌ ዋና እቅዴ የዋሊያዎቹን የአጨዋወት ስልት በመቀየር ውጤት ማምጣት ነው አሉ።
አስልጣኝ ገብረመድህን ትናንት አርብ ጥቅትም 23/2016 ዓ.ም. የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ለአንድ ዓመት ለማሰልጠን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ውል መግባታቸው ይፋ ተደርጓል።
አሰልጣኙ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለማሰልጠን እቅዱ ባይኖራቸውም የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ቡድኑ ከገባበት ቀውስ ለማውጣት የአጨዋወት ስልቱን በመቀየት ውጤት ለማምጣት እንደሚሰሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“እውነት ለመናገር በቅርቡ እንደዚህ አይነት እቅድ አልነበረኝም (ብሔራዊ ቡድኑን ለማሰልጠን)። ወጣቶች ላይ በመስራት አንድ ቡድን ይዤ የሆነ ደረጃ ላይ ማድረስ ነበር እቅዴ።”
ገብረመድህን ከ7 ዓመታት ገደማ በፊት ለአጭር ግዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ሁለት ያክል ጨዋታዎችን ከመሩ በኋላ አለመግባባት ተፈጥሮ ከቡድኑ በመለያየታቸው አሁን ላይ ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ ሲጠየቁ ጥያቄውን ለመቀበል ማንገራገራቸውን ይገልጻሉ።
“ለተወሰነ ግዜ ዋና አሰልጣኝ ሆኜ ለሁለት ጨዋታ መጥቼ ነበር። . . . ግን ተጣልተውኝ ሁለተኛ አልደርስም ብዬ ትቼ ወጣሁ። በወቅቱ በጣም ተበሳጭቼ ነበር። አሁን የመጡት (በፌዴሬሽኑ) ሌሎች ናቸው። ሁለተኛ ደግሞ የውጤት ችግር አለብን የሚል ነገር አነሱ። ‘አገር ትፈልግሃለች’ ሲሉ የማገዝ ግዴታ እንዳለብኝ ስላመንኩኝ ኃላፊነቱን ተቀብያለሁ” ብለዋል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ብሔራዊ ቡድኑን ለማሰልጠን ከስምምነት የደረሱት አሁን ላይ እያሰለጠኑ የሚገኙትን የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት የስፖርት ክለብን ጎን ለጎን ለማሰልጠን ከስምምነት ከተደረሰ በኋላ መሆኑን ይገልጻሉ።
“በመድህን ረዥም ውል ነው ያለኝ። ከ20 ዓመት በታች ያሉት አሳድጌ፤ ዋናው ቡድን አስገብቼ ነው ያለሁት። እነሱን ማሳደግ ላይ ነበር ትኩረቴ። ብዙም እየሰራሁ ነው ያለሁት” የሚሉት አሰልጣኝ ገብረመድህን ክለቡም በእርሳቸው መልቀቅ ደስተኛ ባለመሆኑ ብሔራዊ ቡድኑን እና ክለቡን ጎን ለጎን እንዲያሰለጥኑ በሁሉም ከስምምነት መደረሱን ይገልጻሉ።
ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋች የነበሩት አሰልጣኝ ገብረመድህን ዋሊያዎቹን እና ክለቡን በተመሳሳይ ወቅት ማሰልጠን ጫና ሊፈጥርባቸው እንደሚችል ቢያምኑም፤ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ኃላፊነቱን መቀበላቸውን ይገልጻሉ።
አሰልጣኙ በቅርብ ጊዜያት የዓለም ዋንጫ፣ የአፍሪካ ዋንጫ እንዲሁም የቻና ማጣሪያዎች እንዳሉባቸው ገልጸው የውድድሮቹ ተሳታፊ ለመሆን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተለያዩ ክለቦችን በማሰልጠን ይታወቃሉ።
መቀለ 70 አንደርታ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ መከላከያ እና ሲዳማ ቡና በዋና አሰልጣኝነት ከመሯቸው ክለቦች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር እና መቀለ 70 አንደርታ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሱ አስችለዋል።
በመከላከያ እግር ኳስ ክለብ በነበራቸው ቆይታ ሁለት ጊዜ የኮንፌዴሬሽን ወይም ጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ መሆን ችለዋል።
አሰልጣኙ በቅርቡ ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከሴራ ሊዮን እና ቡርኪና ፋሶ ጋር ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ዝግጅት እንዲሆነው ትናንት ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ አስተላልፈዋል።
አሰልጣኙ ከዛሬ ቅዳሜ ጀምሮ ከብሔራዊ ቡድን አባላት ጋር የልምምድ እና ዝግጅት ስራቸውን በአዳማ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሴራ ሊዮን ጋር ኅዳር 5 እንዲሁም ከቡርኪና ፋሶ ጋር ደግሞ ኅዳር 11 ጨዋታውን ታደርጋለች።