ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማኅበራዊ ሚድያ እና የጋዛ ግጭት፡ ሞሐመድ ሳላህ ለስፖርቱ ዓለም “አርአያ” ነው
ሞሐመድ ሳላህ በእስራኤል-ጋዛ ግጭት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሰጠው ምላሽ ለሌሎች አርአያ ሊሆን ይገባል ሲሉ የቀድሞ የስፖርት ምሑራን ገለጡ።
ግብፃዊው የሊቨርፑል አጥቂ “ተጨማሪ የንፁሐን ነፍስ ከመጥፋቱ በፊት የዓለም መሪዎች አንድ ነገር እንዲሉ” ሲል ባለፈው ወር ጥሪ አቅርቧል።
የ31 ዓመቱ ሳላህ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል እየተካሄደ ስላለው ግጭት አስተያየት ከሰጡ በማኅበራዊ ሚድያ ትልቅ ተከታይ ካላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው።
ሐማስ በዩናይትድ ስቴትስ እና በብሪታኒያ መንግሥታት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ መፈረጁ ይታወቃል።
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ ወደ እስራኤል ዘልቆ በመግባት 1400 ሰዎችን ከገደለ እና ከ240 ያላነሱ ሰዎችን ካገት በኋላ ነው እስራኤል በጋዛ ጥቃት መሰንዘር የጀመረችው።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደሚለው በጋዛ በደረሰው ጥቃት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
“ሳላህ በዜግነቱ ምክንያት አንድ ጎን ሊይዝ ይችላል የሚል ጫና ያለበት ተጫዋች ነው” ይላሉ በስታፈርድሻየር የስፖርት ጋዜጠኝነት አስተማሪው ኢያን ቤይሊ።
“ነገር ግን ቆም ብሎ «እኔ የምቆመው ለሰላም እንዲሁም ስቃይ እንዲቆም ነው» አለ።”
ምሑሩ እንደሚሉት የሳላህ መግለጫ በቂ አይደለም የሚሉ ሰዎች አለ። እኚህ ሰዎች ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ምርጡ ተብሎ የተሸለመው ሳላህ የበለጠ “ፖለቲካዊ አቋም እንዲይዝ” ይጠበቃሉ።
“መልዕክቱን ሲያስተላልፍ በርካቶች ለሰብዓዊ መብት በመቆሙ አድንቀውት ነበር፤ ሌሎች ደግሞ አቋሙ የበለጠ ለአረቡ ዓለም እና ለፍልስጤም ያደላ መሆን ነበረበት ሲሉ ተችተዋል” ይላሉ ኢያን።
“ነገር ግን ይህን ማድረግ አይችልም፤ ምክንያቱም ማኅበራዊ ሚድያን በተለመከተ የክለቡን ፖሊሲ መጣስ አይችልም።”
ቱኒዚያዊው የቴኒስ ኮከብ ኦንስ ጃብውር በያዝነው የአውሮፓውያኑ ወር መባቻ ከሽልማት ከሚያገኘው ገንዘብ የተወሰነውን ለፍልስጤማዊያን እለግሳለሁ ብሎ ነበር።
ይህ “ፖለቲካዊ መልዕክት ሳይሆን ሰብዓዊነት ነው” የሚሉት ምሑሩ የቴኒስ ተጫዋቹን መልዕክት ያደንቃሉ።
እና ሳላህ፣ ኦንስ እና ሌሎች የስፖርቱ ዓለም ሰዎች ፖለቲካዊ አቋምን በተመለከተ ምን ያስተምሩናል? ያላቸውን መድረክ ተጠቅመው ምልከታቸውን ቢያሰራጩስ ምን አደጋ አለው?
ማኅበራዊ ሚድያ “ታላቁ የለውጥ መንገድ”
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በርካታ የአፍሪካ በተለይ ደግሞ የሰሜን አፍሪካ እግር ኳስ ክለቦች፣ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ለፍልስጤማዊያ ያላቸውን ድጋፍ ገልጠዋል።
የአልጄሪያው አምበል ሪያድ ማሕሬዝን ጨምሮ በርካታ ተጫዋቾች የፍልስጤምን ባንዲራ ስታድየም ውስጥ አውለብልበዋል።
“በፍልስጤም እየተካሄደ ስላለው ነገር ከሞላ ጎደል ሁሉም አልጄሪያውያን ተጫዋቾች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል” ይላል አልጄሪያዊው የስፖርት ጋዜጠኛ ማሔር ሜዛሒ።
ሜዛሒ የሳላህን መግለጫ “ታዋቂ ሰዎች እንዲናገሩ ጫና ሲያድርባቸው ምን ማለት እንዳለባቸው” የታየበት ነው ይላል።
የዲጂታል ሚድያ ስትራቴጂስት የሆነችው ኬንያዊቷ ካሮል ኪሙታይ ያለንበት ዓለም ይህ እንዲሆን ያስገድዳል ትላለች።
“ዘረኝነት፣ ሃይማኖት፣ የፆታ ጉዳይ፣ ግጭት የመሳሰሉ ርዕሶች ሲነሱ የስፖርቱ ዓለም ሰዎች ከፈለጉ መናገር ካልሆነ ዝም ማለት ይችላሉ” ትላለች።
“ነገር ግን ጉዳዩ ለግለሰቡ ቅርብ ሲሆን ሰዎች እውነተኛ ማንነት እንዲወጣ ይሻሉ። ጋዛ ለሳላህ ቅርብ ነው። ይህ እንደ ሳላህ ያሉ ተጫዋቾች ምን ያክል ቀላል ያልሆነ ውሳኔ እንደሚጠብቃቸው ያሳያል።”
ሳላህ ያደገው ናግሪግ በተሰኘው የግብፅ ክፍል ነው። ናግሪግ ከጋዛ 350 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው።
እንደ ክሪስታል ፓላስ ያሉ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ለእስራኤል ያላቸውን ድጋፍ ማሳየታቸውስ ችግር አለው?
የስኪማ ቢዝነስ ስኩል ፕሮፌሰሩ ለሳይመን ቻድዊክ ዕይታ ይህ ችግር የለውም።
“ሁለቱ የክለቡ ባለቤቶች አይሁዳዊያን ናቸው። ሦስተኛው ባለቤትም ቢሆን ከአይሁዳዊ አሜሪካውያን ጋር ቅርበት ያለው ሰው ነው። የክለቡ ባለቤቶች ማናቸው የሚለው የክለቡ ባሕል ወሳኝ ናቸው” ይላሉ።
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወተው ማኖር ሶሎሞን የሐማስን ጥቃት ካወገዙ ታዋቂ ሰዎች መካከል ነው።
የቶተንሃሙ ሶሎሞን ወደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከመምጣቱ በፊት በዩክሬን ይጫወት ነበር። በእስራኤል-ጋዛ ግጭት ምክንያት ቤተሰቦቼ “ገሃነም” ውስጥ ነበሩ ይላል።
ቤይሊ የማኅበራዊ ሚድያን ተፅዕኖ ይረዳሉ።
“ይህ ግጭት የዛሬ 30 ዓመት ሆኖ ቢሆን ኖሮ ተጫዋቾች ዘንድሮ በማኅበራዊ ሚድያ የሚደርስባቸው ተፅዕኖ አይደርስባቸውም ነበር” ይላሉ።
የማኅበራዊ ሚድያ አደጋ
ታዋቂው አሜሪካዊ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ሌብሮን ጀምስ ሐማስን አውግዞ ለእስራኤል ያለውን ድጋፍ በመግለጡ ከብዙዎች ነቀፋ ደርሶበታል።
የቡጢ ተጋጣሚው ፍሎይድ ሜይዌዘርም እንዲሁ በተመሳሳይ በማኅበራዊ ሚድያ ትችት አስተናግዷል።
ከዚህ አልፎ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ በለጠፉት ነገር ከክለቦቻቸው የዲሲፕሊን ቅጣት የተሰጣቸው አሉ።
ለፈረንሳዩ ኒስ የሚጫወተው አልጄሪያዊው ተከላካይ ዩሴፍ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የለጠፈው መልዕክት ፀረ-ሴማዊ ነው በሚል እንዲያጠፋ እና ይቅርታ እንዲጠይቅ ተደርጓል።
የፈረንሳዩን ሊግ 1 የሚያስተዳድረው የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዩሴፍ ሰባት ጨዋታ እንዲቀጣ ፈርዶበታል።
ኑሳይር ማዝራዊ ለፍልስጤም የሚያደላ ቪድዮ በኢንስታግራም ገፁ ለጥፎ ክለቡ ባየርን ሙኒክ ከሞሮኳዊው ተጫዋች ጋር ውይይት አድርጊያለሁ ካለ በኋላ መልዕክቱን ቀይሮ ለጥፏል።
በሌላ በኩል የሜይንዝ ተጫዋቹ ኔዘርላንዳዊው አንዋር ኤል ጋዚ የለጠፈውን መልዕክት ለማጣፋት እና ይቅርታ ለመጠየቅ አሻፈረኝ በማለቱ ከክለቡ ጋር ያለው ውል ተቋርጧል።