ኤሎን መስክ ከጉግል መስራች ባለቤት ጋር ጾታዊ ግንኙነት የለኝም አለ

የዓለማች ቁጥር አንድ ሃብታም ኤሎን መስክ ከጉጉል መስራቾች መካከል አንዱ ከሆነው ሰርጂ ብሪን ባለቤት ጋር ጾታዊ ግንኙነት የለኝም አለ።

መስክ ይህን ያለው ኒኮል ሻናሃን ከተባለችው የብሪን ባለቤት ጋር ጾታዊ ግንኙነት አላቸው ብሎ ዎል ስትሪት ጆርናል ከዘገበ በኋላ ነው።

ዎል ስትሪት ጆርናል በዘገባው፤ ጓደኛማቾች የነበሩት መስክ እና ብሪን በዚህ ጾታዊ ግንኙነት ምክንያት ወዳጅነታቸው ተቋርጧል ብሏል።

የቴስላ እና ስፔስ ኤክስ ባለቤት መስክ ግን ዘገባውን መሠረተ ቢስ ነው ሲል አጣጥሎታል። መስክ በትዊተር ገጹ ላይ ከብሪን ጋር ጓደኝነታቸው መቀጠሉን ጨምሮ ገልጿል።

“ሰርጂ እና እኔ ጓደኞች ነን። ትናንት ምሽት በነበረ ፓርቲ ላይ አብረን ነበርን! ኒኮልን በሦስት ዓመታት ውስጥ ያየኋት ሁለት ግዜ ብቻ ነው እሱም ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡብት። ምንም ጾታዊ ነገር የለም” ብሏል መስክ።

ዎል ስትሪት ጆርናል በዘገባው ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን ሰዎች ጠቅሶ፤ መስክ እና ሻናሃን ከአንድ ዓመት በፊት ለአጭር ጊዜ የቆየ የፍቅር ግንኙነት ነበራቸው ሲል ዘግቧል።

ይህ ግንኙነት የዓለማችን 8ኛው ሃብታም፤ ብሪን ከሻናሃን ጋር የነበረውን ትዳር እንዲያፈርስ እና ከመስክ ጋር የነረበውን የረዥም ዓመታት ግንኙነት እንዲያቋርጥ አድርጎታል ብሏል ዎል ስትሪት ጆርናል።

መስክ ማስታወስ ከምችለው በላይ ዎል ስትሪት ጆርናል እኔን እና ቴስላን የተመለከቱ መሠረተ ቢስ ዘገባዎችን ሲያወጣ ቆይቷል ሲል ጋዜጣውን አጥብቆ ከሷል።

አነጋጋሪው ኤሎን መስክ ማነው?

መስክ ትውልዱ ፕሪቶሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ ነው። እናቱ ነጭ ካናዳዊት ሞዴል ነበረች። ወላጅ አባቱ ደግሞ የታወቁ ነጭ ደቡብ አፍሪካዊ ነጋዴ፡፡

ገና በ10 ዓመቱ ከኮምፒውተር ጋር የሙጥኝ ብሎ ነበር፡፡ በ12 ዓመቱም የኮምፒውተር ጌም ፈጥሮ ነበር። 17 ዓመት ከሆነው በኋላ ወደ ሰሜን አሜሪካ አቀና።

ቴክኖሎጂን መሠረት ባደረጉ የንግድ ሃሳቦች ላይ ትኩረቱን የሚያደርገው መስክ፤ አሁን ላይ መስክ 240 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት እንዳላው የብሉምበርግ ቢሊየነርስ ደረጃ ያሳያል።