ህወሓት ሁሉም የትግራይ ተወላጆች እንዲዘምቱ አዲስ ጥሪ አቀረበ

ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኙት የትግራይ ኃይሎች ሁሉም የክልሉ ተወላጆች ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምቱ አዲስ ጥሪ አቀረቡ።

ትናንት ምሽት የህወሓት ንብረት በሆነው ድምጺ ወያኔ ቴሌቪዥን ላይ በተነበበው መግለጫ “ኅልውናችንን ለማረጋገጥ” ሁሉም የትግራይ ተወላጅ “ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሷል” ባለው ጦርነት ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል።

የትግራይ መሪዎች ለነዋሪው ይህን መልዕክት ያስተላለፉት በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ የነበረው የሰላም ንግግር ‘በሎጅስቲክስ’ ችግር ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ከተገለጸ በኋላ ነው።

ህወሓት ያወጣው ይህ መግለጫ በደቡብ አፍሪካ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የሰላም ንግግር ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ ፈጥሯል።

“የትግራይ መንግሥት ሃብቶቻችንን በማቀናጀት ወሳኝ ደረጃ ላይ በደረሰው ጦርነት በመሳተፍ ኅልውናችንን እንድናረጋግጥ ጥሪ አቅርቦልናል” ብሏል በድምጺ ወያኔ የቴሌቪዥን ጣቢያ የተነገረው መግለጫ።

የትግራይ ኃይሎች ማዕከላዊ ዕዛ የተባለው አካልም ባወጣው መግለጫ ለኤርትራ ድንበር ቅርብ በሆነችው ራማ እና በአዲግራት ከተማ ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ እየተካሄደ ነው በማለት፤ “ጦርነቱ በትግራይ ሕዝብ ኅልውና ላይ የተጋረጠ አደጋ በመሆኑ ሁሉም ሊመክት ይገባል” ብሏል።

የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥታት በተደጋጋሚ ከትግራይ ኃይሎች በኩል ለሚሰነዘርባቸው ክሶች እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልሰጡም።

ሁለት ዓመት ሊደፍን የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ካለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ወዲህ በተለያዩ ግንባሮች የሚደረጉ ውጊያዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ይነገራል።

የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ትናንት እሁድ መስከረም 29/2015 ዓ.ም. በትዊተር ገጻቸው የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መሪዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቻቸውን በተለያዩ ግንባሮች ማሰማራታቸውን ገልጸዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኃይሎች አዲስ መጠነ ሰፊ የፀረ ማጥቃት እርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮችን ያካተተ ሜካናይዝድ ጦር በሁለቱ አገራት ድንበር አቅራቢያ በሚገኙት ዛላምበሳ፣ ጾረና እና ራማ አሰማርተዋል።

የትግራይ ክልልን ተቆጣጥሮ የሚገኘው ህወሓት፣ ከፌደራል መንግሥቱ እና ከኤርትራ ጦር ጋር ለሚያደርገው ውጊያ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምቱ ጥሪ ሲያቀርብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

በተመሳሳይ የሦስተኛው ዙር ጦርነት መጀመር በኋላ የኤርትራ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በታች የሆኑ ተጠባባቂ ኃይሎች በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ አውጥቶ ነበር።

ለሦስተኛ ዙር ያገረሸው ጦርነት

የኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. በትግራይ ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ አጎራባች ክልሎች ተስፋፍቶ ጦርነቱ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራን አስከትሏል።

ይህ የእርስ በእስር ጦርነት ላለፉት አምስት ወራት ገደማ ጋብ ብሎ ከቆየ በኋላ ባለፈው ዓመት መጨረሻ እንደ አዲስ ማገርሸቱ ይታወሳል።

ጦርነቱ ለሦስተኛ ዙር ለመጀመሩ ተዋጊ ኃይሎች አንዳቸው ሌላኛውን ተጠያቂ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፤ የኤርትራ ሠራዊትም በጦርነቱ ውስጥ እየተሳተፈ መሆኑን ህወሓት እና ሌሎች ወገኖች ይከሳሉ።

ለአምስት ወራት የቆየው ተኩስ አቁም ፈርሶ ባለፈው ዓመት ነሐሴ 18 ላይ ከተጀመረ በኋላ ዋነኛ ከሚባሉት ክስተቶች መካከል አንዱ የፌደራሉ መንግሥት ከሰሜን ወሎዋ ከተማ ቆቦ ለቅቄ ወጥቻለሁ ካለ በኋላ የትግራይ ኃይሎች መቆጣጠራቸው አንዱ ነበር።

ይሁን እንጂ ህወሓት ኃይሉን በሌላ ግንባር ማጠናከር ስላስፈለገው በቆቦ የነበረውን ኃይል ወደ ሌላ ግንባር ማዘዋወር እንዳስፈለገው በመግለጽ ለሳምንታት ይዞት ከቆየው የቆቦ አካባቢ ወጥቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አስካሁን ስለዚህ ጉዳይ ያለው ነገር የለም።

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሠራዊት ትግራይ ውስጥ የምትገኘውን የሽራሮ ከተማን የመቆጣጠራቸው ዜና የወጣው መስከረም 2015 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ነበር።

የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሠራዊት በከፈቱት መጠነ ሰፊ ጥቃት ሽራሮን ጨምሮ የተለያዩ የትግራይ አካባቢዎችን መያዛቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

የፌደራሉ መንግሥት በመቀለ ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ሲያካሂዳቸው የነበሩት የአየር ጥቃቶች ሌላኛው ጉልህ ክስተት ነበሩ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚፈጽማቸው የአየር ጥቃቶች በጥንቃቄ የተመረጡ እና ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ብቻ ያነጣጠሩ መሆናቸውን ቢገልጽም፣ በጥቃቶቹ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ የህወሓት ባለሥልጣናት እና የሆስፒታል ምንጮች ይገልጻሉ።