ማቲው ፔሪ ለሕልፈት የተዳረገው ኬተሚን የተባለ መድኃኒት ከልክ በላይ በመወሰዱ ነው ተባለ

የፍሬንድስ ተዋናይ ማቲው ፔሪ ኬተሚን የተባለ መድኃኒት ከልክ በላይ መውሰዱ ያስከተለው ውጤት ውሃ ውስጥ ሰጥሞ እንዲሞት አድርጓል ተባለ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፍሬንድስ በተሰኘው ሲትኮም ‘ቻንለር ቢንግ’ የተሰኘውን ገጸ ባህሪ በመጫወት ዕውቅና ያገኘው ማቲው ፔሪ በ54 ዓመቱ ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል።

ተዋናዩ ሎስ አንጀለስ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ተዘፍቆ ሕይወቱ አልፎ መገኘቱን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

አሁን ላይ ይፋ የተደረገው የእስክሬን ምርመራ ውጤት ከተዋናዩ ሞት ጀርባ ምንም አይነት የወንጀል ደርጊት አለመኖሩን ያሳየ ሲሆን ጭንቀት እና ድባቴን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውለው ኬተሚን የተባለው መድኃኒት በሰውነቱ ውስጥ በከፍተኛ መጠን ተገኝቷል።

ፔሪ ኬትሚን በደም ስሩ በኩል መወሰዱ በጤና ማኅደሩ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ እንደወሰደ ተመዝግቦ የተገኘው ከሕልፈቱ አንድ ሳምንት በፊት እንደነበረ ነው። ተዋናዩ ይህን መድኃኒት ለሚያጋጥመው ጭንቀት እና ድባቴ ሲወስድ ቆይቷል።

ፔሪ መድሃኒቱን ለምን ከመጠን በላይ እንደወሰደ እንዲሁም መድሃኒቱን በምን አይነት ሁኔታ እንደወሰደ በአስክሬን ምርመራ ሪፖርት ላይ የተባለ ነገር የለም።

የአልኮል መጠንን እና የሕመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ሱሰኛ መሆኑን በይፋ ይናገር በነበረው ፔሪ ላይ የተካሄደው የእስክሬን ምርመራ እንደ አልኮል፣ ኮኬይን፣ ሄሮይን ወይም ሌሎች የሕመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን በሰውነት ውስጥ አላገኘም።

እአአ 2016 ላይ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ ፔሪ በአልኮል መጠጥ እና አደንዛዥ ዕጽ ምክንያት የፍሬንድስ ሲትኮም የመጨረሻው ሦስት ዓመታት ቀረጻን ጨርሶ አላስታውስም ብሎ ነበር።

ይሁን እንጂ በመጸሐፉ ላይ ከአልኮል እና እጽ ሱሰኝነት ለመላቀቅ ማገገሚያ ማዕከላት መግባትን ጨምሮ የሕክምና ክትትሎችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል።

ተዋናዩ ከእአአ 2001 ጀምሮም አብዛኛውን ግዜ እራሱን ከአልኮል አርቆ ማቆየት መቻሉን ጽፎ ነበር።

ካናዳዊ አሜሪካዊው ማቲው ፔሪ በሌሎች በርካታ ፊልሞች ላይ ቢተውንም ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ለአስር ዓመታት ከአውሮፓውያኑ 1994- 2004 በታየው ተወዳጁ ሲትኮም ‘ፍሬንድስ’ ነው።

በስድስት ሰዎች ጓደኝነት ላይ የሚያጠነጥነው ‘ፍሬንድስ’ ከተሰራበት አሜሪካ በተጨማሪ በበርካታ የዓለማችን የፊልም አፍቃሪዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፏል።

የመጨረሻው የፊልሙ ክፍል በ52.5 ሚሊዮን ሕዝብ በመየት በ2000ዎቹ ብዙ ተመልካች በመያዝ ቀዳሚ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር።