ሊዮኔል ሜሲ የፊፋ ምርጡ ተጫዋች ሲባል ጉዋርዲዮላ ምርጡ አሠልጣኝ ሆኖ ተሸለመ

አርጀንቲናዊው አጥቂ ለዮኔል ሜሲ በፊፋ የምርጦች ሽልማት የወንዶች ምርጡ ተጫዋች ተብሎ ተሸልሟል።

ለንደን በተካሄደው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት የማንቸስተር ሲቲው አሠልጣኝ ፔኦፕ ጉዋርዲዮላ ሽልማት አግኝቷል።

የኢንተር ማያሚው ሜሲ የሲቲውን ኧርሊንግ ሃላንድን ቀድሞ አንደኛ ሲሆን፣ ፈረንሳዊው ኪሊያን ምባፔ ሦስተኛ ወጥቷል።

የሲቲው ኤደርሰን፣ የሪያል ማድሪዱን ቲቦ ኮርቱዋ እና የአል ሂላሉን ያሲን ቦኖን በልጦ ምርጡ ግብ ጠባቂ ተብሏል።

ማንቸስተር ሲቲ ባለፈው የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፣ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኤፍኤ ዋንጫ በማንሳት ታሪክ መፃፉ ይታወሳል።

የዓመቱ ምርጦች

የ36 ዓመቱ ሜሲ ያለፈውን ዓመት የውድድር ዘመን ከፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ዠርማ ጋር ቢጀምርም ባለፈው ሰኔ ወደ አሜሪካው ኢንተር ማያሚ አቅንቷል።

የፊፋ ምርጥ ሽልማት ከተጀመረበት የአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ ሜሲ ይህን ክብር ሲጎናፀፍ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

ለፒኤስጂ እየተጫወተ ሳለ 9 ጎሎች በማስቆጠር ክለቡ የፈረንሳይ ሊግ አንድ ዋንጫን እንዲያነሳ ሲያስችል፣ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አቅንቶ ለኢንተር ማያሚ በሰባት ጨዋታዎች 10 ጎሎች በማስቆጠር ክለቡ የመጀመሪያውን የሊግስ ካፕ እንዲያገኝ አግዟል።

ሃላንድ ባለፈው ዓመት በፕሪሚዬር ሊጉ 36 ጎሎች በማስቆጠር ክብረ-ወሰን ሲሰብር፣ በሁሉም ውድድሮች 52 ጎሎች በማስቆጠር አስፈሪ አጥቂ መሆኑን አስመስክሯል።

ለክለቡ 18 ጎሎች ያስቆጠረው ፈረንሳዊው ምባፔ ደግሞ ከሊዮኔል ሜሲ ጋር በመሆን የሊግ አንድ ዋንጫን ከማንሳቱ በላይ ለአምስተኛ ተከታታይ ጊዜ የወርቅ ጫማ ተሸልሟል።

ፊፋ አሸናፊዎችን ለመለየት ከብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች፣ ከአምበሎች እና ከጋዜጠኞች እንዲሁም በድረ-ገፁ ከደጋፊዎች ድምፅ ሰብስቧል።

ከእግር ኳስ አድናቂዎች የተሰበሰበው ድምፅ ከጠቅላላው ድምር 25 በመቶ ድርሻ አለው።

ሃሪ ኬን፣ ምባፔ፣ ሞሐመድ ሳላህ፣ ሮበርትሰን፣ አሮን ራምሴ እና ሉካ ሞድሪች ለሜሲ ድምፃቸውን ሲሰጡ፤ ኢካይ ጉንዶዋን እና ካሴሚሮ እንዲሁም ሜሲ ለሀላንድ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

የፊፋ ምርጥ ሽልማት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጫዋቾች ያሳኩትን ድል የሚመለከት ሲሆን፣ ባለን ደ ኦር ደግሞ የውድድር ዘመን ስኬትን የሚመለከት ነው።

ነገር ግን በዚህ ዓመት የፊፋ ምርጥ ሽልማት ከታኅሣሥ 2022 እስከ ነሐሤ 2023 ያለውን ጊዜ የሸፈነ ነው።

የዓመቱ ምርጥ ቡድን

በሥነ-ሥርዓቱ የመጀመሪያው ሽልማት የነበረው የወንዶች ምርጥ አሠልጣኝ ዘርፍ ነበር።

ፔፕ ጉዋርዲዮላ፤ ሉቺያኖ ስፓሌቲ እና ሲሞን ኢንዛጊን አስከትሎ ምርጡ አሠልጣኝ ተብሎ ተሸልሟል።

ስፓሌቲ በሴሪ አ ናፖሊን ከ33 ዓመታት በኋላ ባለድል ያደረጉት ክብረ-ወሰን የሆነ አምስት ጨዋታ እየቀራቸው ነው።

ኢንዛጊ ደግሞ ኮፓ ኢታሊያን ከማሸነፋቸው በላይ ኤሲ ሚላንን ይዘው ለቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ መብቃት ችለዋል።

በወንዶች የዓመቱ ምርጥ ቡድን ስብስብ ውስጥ ስድስት የማንቸስተር ሲቲ ተጫዋቾች ተካተዋል።

ተከላካዮቹ ጆን ስቶንስ፣ ካይል ዎከር እና ሩበን ዲያዝ፤ አማካዮቹ በርናርዶ ሲልቫ እና ኬቪን ደ ብረይነ እንዲሁም አጥቂው ኧርሊንግ ሃላንድ ስድስቱ ተጫዋቾች ናቸው።

የሪያል ማድሪድ እና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አማካዩ ጁድ ቤሊንግሀም በዓመቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።

የቡድን አጋሩ ቲቦ ኮርቱዋ ግብ ጠባቂ ሆኖ ሲካተት ኪሊያን ምባፔ፣ ሊዮኔል ሜሲ እና ቪኒሲየስ ጁኒየር ሌሎች በምርጥ 11 የተካተቱ ተጫዋቾች ናቸው።

ስፔናዊቷ አቲያና ቦንማቲ ደግሞ ምርጧ ሴት ተጫዋች ተብላ ተሸልማለች።

ብራዚላዊው ጉዊልሄርሜ ማድሩጋ የዓመቱ ምርጥ ጎል ሽልማትን ወስዷል።