የአፍሪካ ዋንጫ፡ ሴኔጋል ድል ሲቀናት አልጄሪያና ካሜሩን ነጥብ ጥለዋል

የአህጉሪቱ ትልቁ የእግር ኳስ ውድድር አራተኛ ቀኑን ይዟል።

በአይቮሪ ኮስት አስናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ ዋንጫ ገና ከጀምሩ ያልተጠበቁ ውጤቶች አስመዝግቧል።

ሰኞ በተደረጉ የምድብ ሲ እና ዲ ውድድሮች ኃያላን ሀገራት ነጥብ ሊጥሉ ተገደዋል።

ቀን 11፡00 በተደረገ ፍልሚያ ያለፈው ዋንጫ ባለቤት ሴኔጋል ጋምቢያን ሶስት ለምንም ረትታለች።

በምሽት ጨዋታዎች ደግሞ ካሜሩን ከጊኒ እንዲሁም አልጄሪያ ከአንጎላ በተመሳሳይ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የቴራንጋ አናብስት ዋንጫውን ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ሊያነሱ እንደሚችሉ ትልቅ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

ፓፕ ጌዬ ከሳዲዮ ማኔ የተሻገለትን ኳስ መረቡ ላይ በመወዝወዝ በአራተኛ ደቂቃ ሀገሩ ሴኔጋልን መሪ አድርጓል።

ከእረፍት በኋላ ላሚን ካማራ ባስቆጠራቸው ሁለት ተጨማሪ ጎሎች ሴኔጋል ጨዋታውን 3-0 በማሸነፍ የምድቡ መሪ ሆናለች።

ጋምቢያዎች በሁለተኛው አጋማሽ መባቻ ጎል ለማስቆጠር ያደረጉትን ሙከራ የሴኔጋሉ ግብ ጠባቂ ሜንዲ አክሽፎባቸዋል።

በዚሁ ምድብ ከጊኒ የተገናኘችው የአምስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤቷ ካሜሩን አንድ አቻ ተለያይታለች።

በዓለም የእግር ኳስ ሰንጠረዥ 80ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ጊኒ የመጀመሪያውን ጎል በማስቆጠር ካሜሩንን ብታስደነግጥም ሁለተኛውን አጋማሽ በ10 ተጫዋች ለማጠናቀቅ ተገዳለች።

የጊኒው አምበል ፍራንኳ ካማኖ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተሰናበተ ካሜሩን አንድ ጎል ብታስቆጥርም ጊኒዎች አጥብቀው በመከላከል አንድ ነጥብ ይዘው ወጥተዋል።

አይበገሬዎቹ አናብስት ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት በጊኒው ግብ ጠባቂ ኢብራሒም ኮኔ ከሽፎባቸዋል።

ካሜሩን ሁለት ትላልቅ ስም ያላቸው ተጫዋቾቻቸውን ሳይዙ ነው ወደ አይቮሪ ኮስት ያቀኑት።

ግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና ማንቸስተር ዩናይትድ ከቶተንሀም እሑድ ለነበረበት ጨዋታ ጉዞውን ያዘገየ ሲሆን አጥቂው ቨንሴንት አቡባካር ደግሞ በጉዳት ምክንያት ሳይሰለፍ ቀርቷል።

ካሜሩን ከግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና ይልቅ ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ የነበረው ቪንሴንት አቡበከር አለመኖር እንደጎዳት መመልከት ይቻላል።

ምሽት 5፡00 በነበረ የሰኞ የመጨረሻ ጨዋታ ለዋንጫ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል የሆነችው አልጄሪያ ከአንጎል አቻ ተለያይታለች።

ባግዳድ ቦኔድጃህ አልጄሪያን ቀዳሚ ቢያደርግም አንጎላ በማቡሉሉ ፍፁም ቅጣት ምት አቻ የሚያደርጋት ጎል አስቆጥራለች።

አልጄሪያ እንደ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ግብፅ እና ጋና እንዲሁም ካሜሩን የመጀመሪያውን ጨዋታ መርታት ከተሳናቸው ኃይላን ብሔራዊ ቡድኖች ተርታ ተሰልፋለች።

የአፍሪካ ዋንጫ ሲቀጥል ማክሰኞ ቀን 11፡00 ቡርኪና ፋሶ ከሞሪታኒያ፣ 2፡00 ቱኒዚያ ከናሚቢያ ምሽት 5፡00 ደግሞ ማሊ ከደቡብ አፍሪካ ይጫወታሉ።