ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“ከሦስት ወራት ኮማ ስወጣ የሕይወት ትርጉም ገባኝ”
የ31 ዓመቷ ግሬስ ቪክትሪ ዩቲዩብ ላይ በምትለቃቸው ቪድዮዎች ትታወቃለች። በኮሮናቫይረስ በጠና በመታመሟ የተነሳ ለሦስት ወራት ኮማ ውስጥ ቆይታለች።
በሕይወት የመትረፍ ዕድሏ 5 በመቶ ብቻ እንደሆነ ተነግሯት ነበር። ዕድለኛ ሆና ግን ከሞት ተርፋለች። ግሬስ አስገራሚ ታሪኳን ለቢቢሲ እንደሚከተለው ተርካለች።
ሲያመኝ የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ነበርኩ። ልጄ ሳይፕረስን ለመውለድ ገና ሁለት ወር ይቀረኝ ነበር።
ሆስፒታል ስሄድ የኦክስጅን መጠኔ ዝቅተኛ እንደሆነ ተነገረኝ። ልጄ በገና ዋዜማ በድንገተኛ ቀዶ ሕክምና ተወለደ።
ቀዶ ሕክምና ባይደረግልኝ ልጄ አይተርፍም ነበር።
ስወልድ ሕመም አልተሰማኝም። ልጄ ተወልዶ ስዳብሰው ትውስ ይለኛል።
ወዲያው ግን ወደ ጽኑ ሕሙማን ማቆያ እንድገባ ተወሰነ።
ከገና በኋላ ኮማ ውስጥ ገባሁ።
ፍቅረኛዬ ሊ ሲያለቅስ አስታውሳለሁ።
ሕመሜ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ስላልገባኝ፣' ለምን ያለቅሳል?' ብዬ ነበር።
ኮማ ውስጥ ሳለሁ፣ አንዳች ቅዠት ውስጥ እንደገባሁ ይሰማኝ ነበር።
አረንጓዴ ብርሃን ይታየኝ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር እንደተነጋገርኩ ተሰምቶኛል።
አንድ ጊዜ እንዲያውም ወደ ማሌዥያ የበረርኩ ይመስለኛል።
ከአንድ ወር በኋላ ልቤ ቆመ። ለአምስት ደቂቃ ሞቼ እንደነበር ተነግሮኛል።
መጋቢት ላይ ከኮማ ወጣሁ። ሐኪሞቹ ‘ያንቺ መትረፍ ተዓምር ነው። ባንቺ መዳን የማይደነቅ አይኖርም’ አሉኝ።
ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼ እና ወዳጆቼ አጥብቀው ስለጸለዩልኝ እንደተረፍኩ አምናለሁ።
ያለ አእምሮ ጉዳት ከኮማ መውጣቴ አስገራሚ ነው።
ለአንድ ወር ያህል ተዓምረኛ ሰው ነኝ እያልኩ ኖርኩ።
እያደርኩ ግን ራሴን ዳግመኛ ከሕይወት ጋር ማላመድ ነበረብኝ።
ለምሳሌ መራመድን እንደ አዲስ መማር ይጠበቅብኝ ነበር።
ኮማ ውስጥ ሳለሁ ልጄ እኔን መናፈቁም አስቆጨኝ።
“ልጄ የእኔ አልመስል አለኝ”
በጽኑ ሕሙማን ማቆያ ሳለሁ ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው ያየሁት። ያውም በፌስ ታይም።
ሌላ ሰው ሲንከባከበው ከሩቅ ማየት ያማል።
ልጄ የእኔ አልመስል አለኝ።
ያኔ ሰውነቴ ተዳክሞ በግሉኮስ ድጋፍ ነበር ያለሁት።
ጀርሞችን ፈርቼ ልጄን መሳም እንኳን አልቻላኩም።
ወደ ማገገሚያ ክፍል ሲወስዱኝ ነው እናት እንደሆንኩ የተሰማኝ።
ልጄ ከስምንት ሰዓት እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት እኔ ጋር እንዲቆይ ተፈቀደ።
ዳይፐሩን መቀየርና ማጥባት ጀመርኩ።
ልጅ በተወለደ በመጀመሪያዎቹ ወራት ከእናቱ ጋር የሚኖረው ቅርርብ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ አውቃለሁ።
ሆስፒታል ሳለሁ ፀጉሬ ተያይዞ ስለነበር ስወጣ ተላጨሁት።
የሆስፒታሉ ሽታና ስሜቱም ከፀጉሬ ጋር እንዲወገድ ፈልጌ ነበር።
ፀጉሬን ስላጭ ጥሩ ስሜት ተሰማኝ።
“ስለ ፈጣሪ ግራ ይገባኝ ጀመር”
አውራ ጣቴ እንደ ቀድሞው ቁሳቁስ አይጨብጥም። ግን በቀዶ ሕክምና እንደሚስተካከል ተነግሮኛል።
ሳምባዬ እና ሌሎችም የሰውነቴ ክፍሎች አገግመዋል። ይህም ሐኪሞቹን አስገርሟል።
ጉሮሮዬ ላይ ያለው ጠባሳ ገና አልዳነም።
ድምጼም ሸካራ ሆኗል። ግን ብዙም አያሳስበኝም።
ከሁሉም የከበደኝ በሥነ ልቦና ማገገም ነው። የብዙ ሰው እርዳታ አስፈልጎኛል።
ከእግዚአብሔር ጋር ያለኝ ግንኙነት ተለውጧል። አሁን ላይ ስለ ፈጣሪ ግራ ይገባኝ ጀምሯል። ተበሳጭቼበታለሁ።
ያሳለፍኩት ነበር መንፈሳዊ ዓለም እውነት እንደሆነ አረጋግጦልኛል።
ነገር ግን ቁጣ እና ግራ መጋባቴን መሸሸግ አልችልም።
የደረሰብኝን ነገር ብቀበለውም፣ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሳስበው ስሜቱ ይናወጣል።
“በድጋሚ ኮቪድ-19 ሲይዘኝ ፈራሁ”
ሞቶ መመለስ ለእኔ ከባድ አልነበረም።
የቤት ውስጥ ጥቃት የሚፈጸምበት ቤት ስላደግኩ ከሞት መትረፍ አዲስ አልሆነብኝም።
ሕይወትን እንደ አዲስ መማር ግን ከባድ ነው። ሆስፒታል ከመተኛት በላይ ሕይወትን እንደ አዲስ መላመድ ይከብዳል።
በድጋሚ ኮቪድ-19 ሲይዘኝ ደግሞ በጣም ፈራሁ።
ሕመሙ እንደፈራሁት አልጠናብኝም።
አሁን ክትባት ወስጃለሁ።
ክትባቱን ስወስድ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ሐኪሞች እርግጠኛ አልነበሩም። ግን ደኅና ነኝ።
መጀመሪያ ኮሮናቫይረስ ሲይዘኝ ኮማ ውስጥ እስከመግባት ነው ያደረሰኝ። ያ በድጋሚ የሚሆንበት ዕድል ውስን ነው።
አሁን ጤናማና ጠንካራ ነኝ። ስለ ኮቪድ-19 አልጨነቅም።
ከሞት የተመለስኩ ሰው ስለሆንኩ አልፈራም።
የሥነ ልቦና ድጋፍ እያገኘሁ ነው። ያጠነከረኝም እሱ ነው።
“ሁለተኛ ልጄን አርግዣለሁ”
ስለሚሰማኝ ነገር የማዋራው ሰው አለኝ። ይሄ በጣም ጠቅሞኛል።
አሁን ነፍሰ ጡር ነኝ። ሁለተኛ ልጃችን ከወራት በኋላ ትወለዳለች።
ያለፍኩት መከራ ሕይወትን የማይበትን መንገድ ለውጦታል።
ቀድሞ ያለ እረፍት የምሠራ ሰው ነበርኩ።
ያለ መታከት መሥራት የሚፈልጉት ቦታ ያደርሳል የሚለውን አመለካከት አምንበት ነበር።
አሁን ግን ቅድሚያ የምሰጠው ነገር ተለውጧል።
ዋናው የሕይወቴ ማጠንጠኛ እናትነቴ ነው።
ከሥራ በፊት ከሰዎች ጋር ላለኝ ግንኙነት ቅድሚያ መስጠት ጀምሬያለሁ።
ሰዎች የአእምሮ ጤናቸውን እንዲጠብቁ አበረታታለሁ። በተለይም ነርሶች።
ሆስፒታል አልጋ የያዙ ሰዎች የተሻለ ቆይታ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው ሕልሜ።
ለምሳሌ እኔ ለሞት ተቃርቤ ይረብሸኝ የነበረው ፀጉሬን መንከባከብ አለመቻሌ ነው።
ጥቁር ታማሚዎች ፀጉራቸውን እንዲንከባከቡ ማድረግ እሻለሁ።
በቀጣይ ምን እንደምሠራ ገና አልወሰንኩም።
መታመሜ፣ ከረዥም ጊዜ በኋላ ስለሚሆነው ነገር እንዳልጨነቅ አስተምሮኛል።
ዛሬ ላይ መኖር ጀምሬያለሁ።
ሰውነቴን እንከባከባለሁ። ውስጤን አዳምጣለሁ።
ያሳለፍኩት መከራ ብዙ አስተምሮኛል። ሕይወቴን የለወጠ አጋጣሚ ነው።