ናይጄሪያዊው ዴቪዶ ‘በኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ቀልድ ምክንያት የኬንያውን ቴሌቭዥን ጣብያ ፍርድ ቤት ሊያቆም ነው

ናይጄሪያዊው የሙዚቃ ኮከብ ዴቪዶ የብዙዎች መነጋገሪያ ባደረገው ‘የኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ቀልድ ምክንያት ክስ ሊመሰረት መሆኑን ይፋ አደረገ።

አፍሮቢትሱ ኮከብ በኬንያ በነበረበት ወቅት ኮኬይን በግል ጄቱ ከተገኘ በኋላ በቁጥጥር ስር ስለመዋሉ በውሸት ተገልጿል።

በምስራቅ አፍሪካ የነበረውን የሙዚቃ ድግስ ከሰሞኑ ያጠናቀቀው የ31 ዓመቱ ዴቪዶ የሀሰት ዘገባውን "እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ነው" ብሎታል።

"በየትኛውም የዓለም ክፍል በማንኛውም ወንጀል ምክንያት በማንም ተይዤ አላውቅም" ብሏል።

“በአገሬ ናይጄሪያ፣ በአገሬ አሜሪካ ወይም በሥራ ዘመኔ ሁሉ ባደረግኳቸው በመቶዎች በሚቆጠሩ አገሮች ውስጥ ይህ አልሆነም” ሲል በኤክስ ላይ አስተያየቱን አስፍሯል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በኬንያው ኬ24 የቴሌቭዥን ጣብያ የተዘገበው ‘የአፕሪል ዘ ፉልስ’ ታሪክ ሰኞ ዕለት በማህበራዊ ድረ ገጾች ሲሰራጭ ውሏል።

በካምፓላ እና በናይሮቢ በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት የሙዚቃ ስራዎቹን ያቀረበው ናይጄሪያዊው ኮከብ በርካታ የስልክ ጥሪዎች እንደደረሱት ተናግሯል።

የኬንያ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት (ዲሲአይ) ሰኞ ረፋድ ላይ "ሐሰተኛ ዜና" ሲል በተሰራጨው ዜና ላይ አስፍሮ በኤክስ ገጹ ምላሽ ሰጥቷል።

"እነዚህ ዘገባዎች ሙሉ በሙሉ ከእውነት የራቁ መሆናቸውን ለአድናቂዎቼ ላረጋግጥላቸው እፈልጋለሁ። በኡጋንዳ እና በኬንያ ያቀረብኳቸውን የሙዚቃ ድግሶች በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቄ ወደ አገሬ ናይጄሪያ ተመልሻለሁ" ብሏል።

“’ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ምንም ይሁን ምን የእንደዚህ ዓይነት ዓለም አቀፍ የውንጀላ ፈጠራ እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ጠበቃዬ ይህንን የተሳሳተ መረጃ በማዘጋጀት ተጠያቂ በሆኑ የመገናኛ ብዙሃን አካላት ላይ ህጋዊ ክስ ለመመሥረት እየሠራ ነው።”

ኬ24 የተሰኘው የቴሌቭዥን ጣብያ ዴቪዶ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በማቀዱ ዙሪያ የሰጠው ምላሽ የለም።

በርካታ ኬንያውያን ቀልዱ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል። አንዳንዶችም የተፈጠረውን አለመግባባት በሠላማዊ መንገድ እንደሚፈታ ተስፋቸው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አስፍረዋል።