አልጄሪያ እና ሞሮኮ የቱኋን ወረርሽኝ ከፈረንሳይ ወደ ግዛታቸው እንዳይገባ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ

ሰሜን አፍሪካውያኑ አገራት አልጄሪያ እና ሞሮኮ በፈረንሳይ የተከሰተውን አሳሳቢ የቱኋን ወረርሽኝ ለመከላከል በድንበር መተላለፊያቸው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አዘዙ።

የሁለቱ አገራት የጤና ባለሥልጣናት የቱኋን ወረርሽኝ ከፈረንሳይ ወደ አገራቸው እንዳይዛመት ለመከላከል የጤና ቁጥጥር እና የማጽዳት ተግባር ማከናወን መጀመራቸውን አሳውቀዋል።

በዚህም መሠረት ሰዎች፣ መኪኖች፣ አውሮፕላኖች እና መርከቦች ከፈረንሳይ ተነስተው ወደ አገሮቻቸው በሚገቡባቸው መተላለፊያዎች በኩል ተባዮቹ እንዳይዛመቱ ለማድረግ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

ይህ የአልጄሪያ እና የሞሮኮ ውሳኔ ይፋ የሆነው በርካታ ሰዎች የቱኋን ወረርሽኝ ተከስቶባታል ከተባለችው አውሮፓዊት አገር በሚገቡበት ጊዜ ተባዩ አብሮ ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት በመፈጠሩ ነው።

አገራቱ የቱኋን ወረርሽኙን ለመከላከል የቅድሚያ መስጠንቀቂያ እና የመከላከል እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንጂ ወረርሽኙ በግዛታቸው ውስጥ ስለማጋጠሙ ያሉት ነገር የለም።

የፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች ውስጥ የቱኋን ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ መከሰቱ በነዋሪው ዘንድ አሳሳቢ የሆነ ሲሆን፣ ይህም ከወራት በኋላ በአገሪቱ በሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር ተስግቷል።

ማክሰኞ ዕለት የፈረንሳይ የጤና ሚኒስትር አውሬሊን ሩሶ በተከሰተው የቱኋን ወረርሽን የአገሪቱ ዜጎች እንዳይረበሹ ጥሪ አቅርበዋል።

የፈረንሳይ መንግሥት የተስፋፋውን የቱኋን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የሚያስችል አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ እንደሚወስድ ለሕዝቡ አሳውቋል።

በአገሪቱ መዲና ፓሪስ ተባዩ ምን ያህል መስፋፋቱን ለማሳየት በአውቶብሶች፣ በባቡሮች፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎች እና በሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች የተቀረጹ በርካታ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተሰራጭተዋል።

ይህ የቱኋን ወረርሽኝ የተከሰተው ፓሪስ ታላቁን የኦሊምፒክ ውድደር ለማስተናገድ የመጨረሻውን ዝግጅት እያደረገች ባለበት ጊዜ ነው።

ቱኋኖች ትንሽዬ ነፍሳት ሲሆኑ፣ በሰው እና በነፍሳት ላይ ጥገኛ በመሆን በሚያሳክክ ንክሻ ቆዳን ከማስቆጣት በተጨማሪ ደም የሚመጡ ተባዮች ናቸው።

ተባዮቹ በአብዛኛው በመኖሪያ ቤቶች እና በሆቴሎች የመኝታ ስፍራዎች እና መገልገያዎች ላይ ይራባሉ።