አንድ ጥናት ጤናን ለመጠበቅ በቀን 5ሺህ እርምጃ ማድረግ በቂ ነው አለ

ከረጅም ጊዜ በፊት አንድ ሰው ጤናውን አስጠብቆ ለመኖር በቀን ቢያንስ 10 ሺህ እርምጃ መጓዝ እንደሚያስፈልገው ይታመን ነበር።

አዲስ በተደረገ ጥናት ግን በቀን 5ሺህ እርምጃ ብቻ በመራመድ ጤናን ማስጠበቅ ይችላል ተብሏል።

በመላው ዓለም ከ226 ሺህ በላይ ሰዎች የተደረገው ጥናት እንዳረጋገጠው ቢያንስ 4 ሺህ እርምጃ በቀን ማድረግ በየትኛውም ምክንያት ሊከሰት የሚችልን በለጋ ዕድሜ የመሞት ዕድልን እንደሚቀንስ አሳይቷል።

የልብ እና የደም ስር ጤናን ለመጠበቅ ደግሞ በትንሹ 2300 እርምጃ ማድረግ በቂ ነው ተብሏል።

የአካል እንቅስቃሴ በጨመረ ቁጥር ጤናማነትም በዚያው ልክ እንደሚያሳድግ ጥናቱ አረጋግጧል።

ከ4 ሺህ በላይ ያለ እያንዳንደዱ ተጨማሪ 1 ሺህ ርምጃ ያለዕድሜ የመሞትን ዕድል በ15 በመቶ እንደሚቀንስም ተገልጿል።

ከፖላንድ እና አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡት ይህ አይነቱ የጤና ጠቀሜታ ለየትኛውም ጾታ እና በየትኛውም ዕድሜ ለሚገኝ ሰው፣ በየትኛውም ቦታ ተመሳሳይ የጤና ውጤት የሚያስገኝ ነው።

ይሁን እንጂ ከ60 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ደግሞ በተለየ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የመድሃኒት ጥገኛ ከመሆን ይህንን የጥናት ውጤት እና የምግብ ምጣኔን በማስተካከል ብቻ የልብ እና ተያያዥ ሕመሞችን በማስወገድ ብዙ የመኖር ዕድልን ማስፋት እንደሚቻል የጥናቱ ተሳታፊዎች መክረዋል።

በዓለም ብዙ ሰዎች ከሚሞቱባቸው የጤና እክሎች መካከል በአራተኛ ደረጃ የሚገኘው የጤና ችግር ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማነስ የሚፈጠር ሞት ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ 3.2 ሚሊዮን በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው በየዓመቱ ሕይወታቸው ያልፋል።

ብዙ መቀመጥ በአብዛኛው የወገብ ሕመም የሚያመጣ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ቢሮ ውስጥ በመቀመጥ የሚያሳልፉ ሰዎች በዕድሜያቸው መጨረሻ ላይ ለወገብ ህመም ተጋላጭ እንደሚሆኑም ሙያተኞች አብራርተዋል።

ሙያተኞች እንደሚሉት እንቅስቃሴ ማድረግ የደም ግፊትን ይቀንሳል፣ ጡንቻዎችን ያጠነክራል፣ ከተመጣጠነ ምግብ ጋር የሰውነት ክብደትን ሚዛን ያስጠብቃል፣ ንቁ እና ጠንካራ ያደርጋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት ራስን ከሞባይል ስልክ እና ከኮምፒውተር ማራቅ የአእምሮ እረፍት እና ጤናንም ያመጣል።

ባለሙያዎች እነዚህን የእንቅስቃሴ ጥቅሞች ለማግኘት ተግባራዊ ቢደረጉ የሚሏቸውን ሁኔታዎችም መክረዋል።

መኪና ወይም አውቶብስ ከመጠቀም ይልቅ በእግር መጓዝ፣ ቢሮ ውስጥ የሚሰራ ሰው በተወሰነ የጊዜ ልዩነት ማስታወሻ ደውል [አላርም] በመሙላት ከመቀመጫ ተነስቶ መንቀሳቀስ፣ በቀን የ30 ደቂቃ ጉዞ ማድረግ፣ ከጓደኛ ጋር መንቀሳቀስ እና ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰድ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።