የሰሜን ኮሪያው ኪም ሴት ልጅ ለ5ኛ ጊዜ በአደባባይ መታየቷ ለምን አነጋጋሪ ሆነ?

ባለፈው ረቡዕ የሰማይ ስባሪ የሚያካክሉ ተጎታች ሚሳኤሎች ሲያጓሩ ነበር፤ በሰሜን ኮሪያዋ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ።

በሚደንቅ ሁኔታ ለሚሳኤሎቹ ቁብ የሰጠ አልነበረም።

ከኪም ጎን ፈገግ የምትለዋ ሴት ልጅ ከግዙፎቹ ሚሳኤሎች በላይ ደምቃ ትታይ ነበር።

የዚህች ልጅ ነገር ሰሜኑንም ደቡቡንም እኩል እያነጋገረ ነው። ሶልም ፒዮንግያንግ ለዚች አንዲት ፍሬ ልባቸው እኩል ይደነግጣል።

ኪም በስስት ነው የሚያይዋት። የስለት ልጅ ትመስላለች።

ከእርሷ ጋር ሲሆኑ አምባገነንነታቸው የተነነ ይመስላል።

ለማንኛውም ኪም በድንገት አደባባይ ይዘዋት እየወጡ መታየት ጀምረዋል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ።

ይሁንና እስከዛሬ ለሕዝብ በቴሌቪዥን መስኮት የታየችው በድምሩ አምስት ጊዜ ብቻ ነው።

ሰሜን ኮሪያውያንም ምዕራቡ ዓለምም እሷ በታየች ቁጥር ‘ጉድ በል ፒዮንግያንግ’ ይላል።

ምክንያቱም በዚያች አገር ቆፍጣና የአገር መሪዎች እንዲያ ሲያደርጉ ማየት አልተለመደም።

ወንድ ልጆቻቸውን እንጂ ሴት ልጆቻቸውን እንዲህ በአደባባይ ሲኮሩባቸው አይታይም።

እንዲያ ካደረጉም በምክንያት ነው የሚሆነው።

የኪም ሴት ልጃቸውን ይዞ መንጎራደድ፣ መምነሽነሽ፣ መውጣት መውረድ፣ መሳቅ መፍለቅለቅ ምን ይናገራል?

ቀጣይዋ የሰሜን ኮሪያ ዘዋሪ ታላቋ መሪ ይቺ ትንሽዬ ልጅ ትሆን?

ስሟ የማይታወቀው “ዕጹብ”

ይቺ የኪም ሴት ልጅ ገና 10 ዓመቷ ነው። ስሟን መጥራት ባይፈቀድም ጁዓ እንደምትባል ጭምጭምታ አለ።

ለአምባገነኑ ኪም ይቺ ልጅ ሁለተኛ ሴት ልጁ ሳትሆን አትቀርም የሚል ጥርጣሬም አለ።

ሌላኛዋ ሴት ልጅ የት እንደሆነች እምብዛምም አይታወቅም። ይቺኛዋ ግን ቢያንስ አምስት ጊዜ ለሕዝብ ተገልጣለች።

በቀደም በጥቁር ጃኬት ዝንጥ፣ ቁንጅት ብላ በሚሳኤሎች መሀል ከአባቷ ኪም ጋር ድንገት ብልጭ ስትል ጄኔራሎች በማያቋርጥ ጭብጨባ ተቀበሏት።

በሰሜን ኮሪያ ጭብጨባ መዳፍ ካልደማ ተጨበጨበ ይባላል?

የሰሜን ኮሪያ ሚዲያ ይቺን ልጅ “የኔ ማር”፣ “ዕጹብዬ” እያሉ ነው እንጂ በመታወቂያ ስሟ ጠርተው አያቃልሏትም።

የሰሜን ኮሪያ የታፈሩ የተከበሩ ጄኔራሎች ራሱ ይቺን የ10 ዓመት ልጅ “እጅግ የተከበሩ” እያሉ ነው የሚጠሯት።

እጅግ የተከበሩ የሚል ማዕረግ ደግሞ ኪም ሳያጸድቁት አገልግሎት ላይ የሚውል አይደለም።

እና ይቺ ጉደኛ ልጅ ለ5ኛ ጊዜ መታየቷ ነው ሰሞኑን።

ለመጀመሪያ ጊዜ ታይታ አገር ጉድ ያለው ባለፈው ኅዳር ነበር።

ያን ጊዜ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል እየተሞከረ ነበር።

ያን ጊዜ የሰሜን ኮሪያ ሚዲያ ምን ብሎ እንደሚጠራት ግራ ተጋብቶትም ነበር።

ኪም ምን አስጊ ነገር ገጥሟቸው ይሆን?

ይሁንና ይቺ ልጅ ያለ ምክንያት በአደባባይ፣ በግላጭ እንዳልታየች ምዕራቡም ምሥራቁም፣ ሰሜኑም ደቡቡም ሳይገምት አልቀረም።

ከተንታኞች መላምቶች ሁሉ አነጋጋሪ የሆነው ኪም ራሳቸው መሞቻቸው ተቃርቦ ይሆን ወይ? የሚል ነው።

በሐኪሞቻቸው ዕድሜያቸው አጭር እንደሆነ ተነግሯቸው ቢሆንስ?

ለነገሩ ይህን የተናገሩ ሐኪሞች በሕይወት ይቆያሉ? እውነት ቢሆን ራሱ ለምን ብለው እንዲያ ይነግሯቸዋል?

የኪም ጤና ቢያንስ አስተማማኝ እንዳልሆነ የምዕራብ የስለላ ምንጮች ይጠቁማሉ።

ኪም ድንገት ክብደታቸው ጨምሮ ከቴሌቪዥን ርቀው በነበረ ጊዜ ብዙ ይወራ ነበር።

እያጣጣሩ ነው ተብሎም ነበር። ከወራት በኋላ ግን ኮስተርተር ብለው በአገሬው ቴሌቪዥን ታዩ።

ምናልባት ኪም ረዥም የሕይወት ዘመን የላቸው ይሆን ይሆናል? በእርግጥ ገና 39 ናቸው። 40 እንኳ አልደፈኑም።

ዕድሜ ግን ስለምንሞትበት ዘመን ማጠር እና መርዘም ማረጋገጫ መሆን አይችልም። ስለዚህ ወራሻቸውን እያስተዋወቁስ ቢሆን?

ኪም ራሳቸው ድሮ አባታቸው ለዚህ ሥልጣን ሲያጯቸው ገና ትንሽ ልጅ ነበሩ። ምናልባትም 8 ዓመታቸው ነበር።

ነገር ግን አባታቸው ያን ጊዜ “ወራሼ ልጅ ኪም ይሆናል፤ ሰሜን ኮሪያንም ያቀናታል” ብለው ለሕዝብ ጮክ ብለው አልተናገሩም።

ለቅርብ ጄኔራሎች ብቻ ነው ሹክ ያሉት። ከዚያ ወዲህ ኪም በልዩ ክብካቤ አደገ። የሰሜን ኮሪያ ጄኔራሎች ከአህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ የሚሳኤል አረሮች እኩል የዐይን ብሌናቸው አድርገው ይመለከቱት ያዙ።

ሰፊው ሕዝብ ግን ምንም አያውቅም ነበር።

አባቱ ሲሞቱ ታዲያ ሕዝብ ለእርሱ ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛላቸው እና ቅቡልነታቸው ከፍ እንዲል ጨካኝ እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው። ስለዚህ የተወሰኑ የቅርብ ጄኔራሎቹን “ሊያሴሩብኝ አስበዋል” ብለው የመስዋዕት በግ አደረጓቸው።

ከዚያ በኋላ ነው መንበራቸው ጸና።

ምናልባት ኪም በራሳቸው የደረሰባቸውን ያለመታመን ጣጣ በዚች ሴት ልጃቸው ላይም እንዳይደርስ ከወዲሁ እያለማመዷት ይሆን?

ሌላስ ምን ይባላል?

ሌሎች ግን ሌላ ይጠረጥራሉ።

ኪም መጀመሪያ ሰው መሆናቸውን፤ ቀጥሎ ደግሞ ደግ አባት መሆናቸውን ለዓለም ማሳየት ፈልገዋል።

ሁልጊዜ ስለ ሚሳኤል የሚያወሩ፣ ጦርነት ግጠሙኝ እያሉ የሚፏልሉ አምባገነን ሳይሆኑ ሰው መሆናቸውን ዓለም እንዲያውቅላቸው ይሻሉ። ልጃቸውን ከጎናቸው የማይለይዋት ይህን ለማስመስከር ይሆናል።

እስከአሁን ለአደባባይ በበቁ ፎቶዎች የኪም ሴት ልጅ በሚሳኤል እና በጄኔራሎች ተከባ፣ እናት እና አባቷ ግራ እና ቀኝ ሆነው እሷ እንደ ጠረጴዛ አበባ መሀል ሆና ነው የምትታየው።

ፎቶዎቹ የሚነግሩን ነገር ሁሉ የነገሩ ማጠንጠኛ ማዕከል፣ የሰሜን ኮሪያ ልብ እሷው መሆኗን ነው።

ሰሜን ኮሪያ እስከ ዛሬ የተመራችው በአንድ ቤተሰብ ሦስት ትውልድ ነው።

ሁሉም የሰሜን ኮሪያ ዜጎች አገራቸው የምትመራው በዚህ “ስዩመ እግዜር” በሆነ ቤተሰብ ብቻ ነው ተብሎ ተነግሯቸዋል።

የጠራ ደም ካለው ከዚህ ቤተሰብ ውጪ አገሪቱ ከተመራች ትረክሳለች ተብለዋል። ይህንንም አምነው ተቀብለዋል።

ከኪም በኋላ የምትመጣው ይቺ “ዕጹብዬ” የምትባለው ሴት ልጁ ከሆነች እርሷ አራተኛው ትውልድን ይዛ ምሥጢረኛዋን አገር ሰሜን ኮሪያን ሰጥ ለጥ አድርጋ ትመራ ይሆናል።

ሴት ልጅ በሰሜን ኮሪያ ትልቁን ሥልጣን ልትቆናጠጥ አትችልም የሚሉ ክርክሮች ግን አሁንም አልጠፉም።

በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ አንቱ የተባሉት ተንታኝ ጄምስ ፍሬትዌል እንዲህ ይላሉ።

ሰሜን ኮሪያ አባታዊ ሥርዓት ነው ያላት። ምናልባት ከጾታዋ ይልቅ የደም ጥራቷ ጎልቶ ስሚታይ ‘እጹብዬ’ ቀጣይ የሰሜን ኮሪያ መሪ አትሆንም ብሎ መደምደም አይቻልም።

ያም ሆኖ ይላሉ ተንታኙ፤ “ሴት ልጅ ሰሜን ኮሪያን እንድትመራ የሚፈቅድ የተደላደለ ሥርዓት እና አስተሳሰብ በዚያ አገር አለ ብዬ አላምንም።”

“ዕጹብዬ” ለስድስኛ ጊዜ የምትታየው መቼ ይሆን?