በሴቶች ላይ የአካል እና የስሜት ለውጦችን የሚያስከትለውን ማረጥ እንዴት መቆጣጠር ይቻላል?

ወ/ሮ አዲ ጉዮ እድሜያቸው ወደ 50 መሻገሩን ተከትሎ ለሁለት ዓመት ያህል የተከሰተባቸውን የስሜት መለዋወጥ ያስታውሳሉ።

“ካለ ምንም ምክንያት የተለየ ስሜት ይሰማኝ ጀመር” የሚሉት ወይዘሮዋ፣ የስሜታቸውን ድንገት መለዋወጥን ተከትሎ “. . .ያበድኩ ሁሉ መስሎኝ ነበር” ይላሉ።

“ለሊት እንቅልፍ አልነበረኝም። የምግብ ፍላጎቴም እንዲሁ ቀንሶ ነበር። ሰውነቴ ማተኮስ ብቻ ሳይሆን ላብ እንደ ውሃ ይወርደኝ ነበር። ቀጥሎ ደግሞ ብርድ ብርድ ይለኛል” በማለት የወር አበባ ማየት ካቆሙ በኋላ የታየባቸውን ምልክቶች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተለያዩ ሆስፒታሎች በመሄድ የሕክምና ባለሙያዎች እንዲያይዋቸው ቢያደርጉም ምንም ዓይነት በሽታ እንደሌለባቸው ተነገራቸው።

ይህ ደግሞ ተጨማሪ ብስጭት እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ከተታቸው።

በሕክምና ረገድ የተለያዩ ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላም “በእምነት በኩል መላ መፈለግ ጀመርኩ” በማለት ከወር አበባቸው መቆም ጋር ተያይዞ ያሳለፉትን ውጣ ውረድ ያስረዳሉ።

“ከቅጠላ ቅጠል የተቀመሙ ባሕላዊ መድኃኒቶችን ብወስድም ላጋጠመኝ ችግር መፍትሔ ማግኝት አልቻልኩም” ሲሉም ያክላሉ።

ወ/ሮ አዲ በሽታቸው ባለመታወቁ የተነሳ ቤተሰቦቻቸው ላይ የፈጠሩትን ጫና በማሰብ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገቡ።

“የአእምሮ ጭንቀት እና የእንቅልፍ መድኃኒት መውሰድ ጀምሬ ነበር። እንደማልድን በማሰብም ቤተሰቤ እና ልጆቼን ላጣ ነው ብዬ አስቤ ትልቅ ስጋት ውስጥ ገብቼ ነበር” ይላሉ።

“ባለቤቴ ታጋሽ ባይሆን ኖሮ ይኼኔ ተለያይተን ነበር። ምክንያቱም አመሌ በትንሽ ነገር ይቀያየራል። ችግሬን አይረዱኝም ብዬ በትንሽ በትልቁ አለቅስ ነበር።”

በኋላ ላይ ወ/ሮ አዲ እያለፉበት ያለው የጤና ሁኔታ በሽታ ሳይሆን፣ አንዲት ሴት በማረጫዋ ወይንም የወር አበባዋ በሚቋረጥበት ጊዜ የሚገጥማት ለውጥ መሆኑን ተረዱ።

የወር አበባ መቆም (ማረጥ) ማለት ምን ማለት ነው?

ማረጥ ማለት አንዲት ጤነኛ ሴት እድሜዋ የወር አበባ መቆሚያ ላይ ስትደርስ የሚከሰት ተፈጥሯዊ ሂደት ነው።

ይህም ማለት ልጅ መውለድ ከምትችልበት እድሜ ክልል ወጥታ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የምትጀምርበት እንደሆነ የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

እንደ ጤና ባለሙያዎች ገለጻ፣ የአንዲት ሴት የወር አበባ ቆሟል ማለት የሚቻለው በተከታታይ ለ12 ወራት የወር አበባዋን ማየት ካቆመች ነው።

ይህም ሁኔታ በአብዛኞቹ ሴቶች ላይ መታየት የሚጀምረው ከ40 ዓመት ጀምሮ ሲሆን በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ እስከ 60 ዓመት ድረስ ሳይታይ ሊቆይ እንደሚችል በሴቶች ጤና ላይ ለ37 ዓመታት የሰሩት ፕሮፌሰር ጉዮ ጀልዴሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ወቅትም በሴቲቱ ላይ የሚታዩ የአካል እና የስሜት ለውጦች ብዙ መሆናቸውን የሕክምና ባለሙያው ያስረዳሉ።

“የአንዲት ሴት የወር አበባ መቆም ተፈጥሯዊ እና ሥነ ሕይወታዊ ሂደት ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር ጉዮ በዚያ ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩት የስሜት እና የአካል ለውጦች በሴቷ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው ይናገራሉ።

“ኦቫሪ የተለመደውን ሥራውን በሚያቆምበት ጊዜ እንቁላልን ማምረት ብቻ ሳይሆን ወደ ደም የሚቀላቀል የሆርሞን መጠንም ይቀንሳል። የሆርሞን ባልተለመደ ሁኔታ መቀነስ ደግሞ አንዲት ሴት እንድትጨነቅ፣ ስሜቷ እንዲቀያየር፣ በቀላሉ አንድን ነገር የማስታወስ ችግር ሊገጥማት ይችላል” ይላሉ።

እንደ ጤና ባለሙያው አባባል የሴቶች የወር አበባ የሚያቆመው በአብዛኛው ጊዜ ቀስ በቀስ ነው።

“የወር አበባ ዑደትን የሚቆጣጠረው ኦስትሮጂን በተለመደ ሁኔታ ማመንጨቱን ስለሚያቆም አንዲት ሴት የወር አበባ ሳታይ ልትቆይ፣ ወይንም ባልተለመደ ጊዜ ልታይ፣ ካልሆነም ብዙ ደም ሊፈሳት ይችላል።”

በአንዳንድ ሴቶች ላይ ደግሞ ይላሉ ፕሮፌሰሩ፣ የወር አበባቸው በድንገት ሊቆም ይችላል።

አክለውም “በመራብያ አካላቸው ላይ ለውጥ የሚታይ ሲሆን ሰውነት እና አጥንታቸውም ይለሰልሳል። ከዚህም የተነሳ በድንገት ቢወድቁ በቀላሉ ሊሰበሩ ይችላሉ” ሲሉ የሚታዩ ለውጦችን ይዘረዝራሉ።

እነዚህ የአካል ለውጦች ሴቷን እንቅልፍ ሊነሱ እና አቅም ሊያሳጡ አንዲሁም ለልብ በሽታ በቀላሉ ሊያጋልጡ አንደሚችሉ ተናግረዋል።

በዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ ያሉ ሴቶች ወደ ጤና ጣቢያ ቢሄዱ የሚታይባቸው የሌሎች ሕመም ምልክቶች ስለሚመስሉ ተገቢውን ሕክምና ላያገኙ ይችላሉ።

በአንዳንድ ሴቶች ላይ ይህ ዓይነቱ ምልክት ለብዙ ዓመታት ሊቆይ የሚችል ሲሆን፣ ጥቂቶቹ ላይ ግን በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ የሚዘልቅ የሰውነት ትኩሳት እና ማላብ ሊገጥማቸው ይችላል ይላሉ ፕሮፌሰር ጉዮ።

ማረጥን ተከትሎ የሚከሰቱ ችግሮችን እንዴት መቀነስ ይቻላል?

የማረጫ እድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሴቶች ይህንን ችግር ለመቀነስ የሚረዱ ውጤታማ የሆኑ ሕክምናዎች ማግኘት እንደሚችሉ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በኑሮ ዘይቤ ላይ ለውጥ ማድረግን ጨምሮ የሆርሞን ሕክምና እና መድኃኒት ይገኛል።

የተለያዩ ሕክምናዎች ቢኖሩም የሆርሞን ክኒን መውሰድ ግን የሚመከር እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በ2001 እኤአ በተካሄደ አንድ ጥናት ላይ እንደተመለከተው የኦስትሮጂን መድኃኒትን የሚወስዱ ሴቶች ለጡት እና ለአንጀት ካንሰር አንደሚጋለጡ ተጠቅሷል።

ይኹን አንጂ በዚህ የኦሰትሮጂን መድኃኒት ምትክ ከአኩሪ አተር የተሰሩ ምግቦችን በብዛት መመገብ ጠቃሚ መሆኑን ፕሮፌሰር ጉዮ ይጠቁማሉ።

በተጨማሪም ከመድኃኒት ውጪ በአኗኗር ዘይቤ ላይ ለውጥ በማድረግ ይህን ማረጥን ተከትሎ የሚከሰት ሕመም መከላከል እንደሚቻል ይመክራሉ።

ማተኮስ እና ላብ የሚያስቸግራቸው ሴቶች ሲጃራ የሚያጨሱ ከሆነ እንዲያቆሙ፣ ካፌን የሚበዛባቸውን ጣፋጭ ምግቦች እና መጠጦች መቀነስ እንደሚገባቸውም አክለው ገልፀዋል።

እንዲሁም በቂ እና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ አስፈላጊ መሆኑን፣ የሰውነት አንቅስቃሴ ማድረግም እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ አስተዋጽኦ እንዳለው መክረዋል።