ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማራዘም በሚቀርብ ሐሳብ ላይ ለመወሰን የተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ልዩ ስብሰባ ያደርጋል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ከስድስት ወራት በፊት የተደነገገውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማራዘም በሚቀርብ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ዛሬ አርብ ልዩ ስብሰባ ያደርጋል።
ምክር ቤት በዚሁ ስብሰባው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላትን የሥራ ጊዜንም እንደሚያራዝም ሦስት የምክር ቤቱ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በልዩ ስብሰባው ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ የሚሆንበት ጊዜን ለማራዘም በሚቀርብ የውሳኔ ሐሳብ ላይ የሕዝብ እንደራሴዎቹ ውይይት በማድረግ ድምጻቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዛሬ አርብ ጥር 24/2016 ዓ.ም. በሚካሄደው ስብሰባ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጊዜ ለማራዘም የሚቀርበው የውሳኔ ሐሳብ የምክር ቤቱን ሁለት ሦስተኛ አባላት ድጋፍ ማግኘት ይጠበቅበታል።
ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል በፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል እየተባባሰ የሄደውን ግጭት ተከትሎ ክልሉ በየፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነበር መጀመሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የደነገገው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በአማራ ክልል እና “እንዳስፈላጊነቱ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች” ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ነበር።
በ16 ተቃውሞ የጸደቀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት የጸና እንደሚሆን በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ጥር 28/2016 ዓ.ም አዋጁ ስድስት ወር ይሞላዋል።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ለስድስት ወራት የታወጀን የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ “ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል” ሲል ይደነግጋል።
ከዚሁ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተመሳሳይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላትን የሥራ ጊዜ ለማራዘም የሚቀርበውን የውሳኔ ሃሳብም ምክር ቤቱ መርምሮ ያጸድቃል። የመርማሪ ቦርዱ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ከሕግ ባለሙያዎች የተውጣጡ ሰባት አባላት አሉ።
ቦርዱ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱ እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢ ሰብዓዊ አለመሆናቸው መቆጣጠር እና የመከታተል” ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ ተሰጥቶታል።
በአማራ ክልል ካለፈው ዓመት አጋማሽ አንስቶ የተከሰተውን አለመረጋጋት መባባሱን ተከትሎ ሁኔታው ከአቅሙ በላይ መሆኑን በመግለጽ የፌደራል መንግሥቱ ሕግ እና ሥርዓትን እንዲያስከብር የክልሉ መስተዳደር ሐምሌ 27/2015 ዓ.ም. ያቀረበውን ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው “በትጥቅ የተደገፈ ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ ተሸጋግሯል” በማለት በክልሉ እና እንዳስፈላጊነቱ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. መደንገጉ ይታወሳል።
በእረፍት ላይ የነበረው የሕዝብ ተወዮች ምክር ቤትም ነሐሴ 8/2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል እንዲተገበር ያሳለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ12 ድምጸ ተአቅቦ እና በ16 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆት ባለፉት ስድስት ወራት ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲደነገግ ምክንያት የሆነው በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች አሁንም ድረስ እየተካሄዱ መሆናቸውን ነዋሪዎች እና የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።