ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬን ታዋቂ ጄት አብራሪ እና ሌሎች በረራ ላይ ተጋጭተው ሕይወታቸው አለፈ
ከዩክሬን የተከበሩ ተዋጊ ጄት አብራሪዎች አንዱ የሆነው ግለሰብና ሌሎች ሁለት አብራሪዎች በረራ ላይ ሳሉ ተጋጭተው ሕይወታቸው አለፈ።
አንድሪ ፒልሺኮቭ የዩክሬን ጦርነት በተጀመረ ሰሞን ኪይቭ ላይ በነበረው ግጭት ነው ዝና ያተረፈው።
የዩክሬን ጦር ኃይል የተዋጊ ጄት አብራሪዎቹን ሞት “ልብ ሰባሪ እና ሊተካ የማይችል ነው” ብሎ አንድሪን “ጥልቅ ዕውቀትና ተሰጥዖ ያለው አብራሪ ነበር” ብሎታል።
ኤለ-39 የተባሉት ሁለት አውሮፕላኖች በሰሜናዊ ዩክሬን ሰማይ ላይ እየበረሩ ሳለ ነው የተጋጩት።
አርብ ዕለት በዚቶሚር አብላስት የደረሰው አደጋ በበረራ ቅድመ ዝግጅት ጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት ይሆን ወይ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ምርምራ ተከፍቷል።
ቀጠናው ከዋና ከተማዋ ኪይቭ መዕራባዊ አቅጣጫ የሚገኝ ሲሆን ጦርነት ከሚካሄድበት ሥፍራ ብዙ ኪሎ ሜትሮች የራቀ ነው።
የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በምሽታዊ መግለጫቸው የአብራሪዎቹን ሞት አረጋግጠው ሃገራቸው “የዩክሬንን ሰማይ ነፃ ለማውጣት የታገሉ ሰዎችን አትረሳም” ብለዋል።
በውጊያ ስሙ “ጁስ” በመባል የሚታወቀው ፒልሺኮቭ ሩሲያ በርካታ ክሩዝ ሚሳዔሎችና ድሮኖች በላከች ወቅት ሚግ-29 የተሰኘችውን ጄት እያበረረ ጥቃቱን የማምከን ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር።
በወቅቱ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረገው አብራሪ ጄቱን እያበረረ ጥቃት መመከት ምን እንደሚመስል ያለውን የጫና ስሜት አጋርቶ ነበር።
ኤፍ-16 የተባሉ 61 ተዋጊ ጄቶችን ከአጋሮቿ ለመቀበል ዝግጅት ላይ ላለችው ዩክሬን የአብራሪዎቹ ሞት የሚያሳዝን ዜና ሆኗል።
ባለፈው ሐሙስ ፔንታገን [የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት] ለዩክሬናዊያን በእንግሊዝኛ ቋን ስለ ኤፍ-16 ጄቶች በመስከረም ወር ሥልጠና እንደሚሰጥ አረጋግጧል።
በወርሃ ጥቅምት ደግሞ የበረራ ሥልጠና በአሜሪካዋ አሪዞና የሚሰጥ ሲሆን ሌሎች የዩክሬን አጋሮች በያዝነው ወር መገባደጃ ሥልጠና እንደሚሰጡ ገልጠዋል።
ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶችን ለማብረር የሚደረገው ሥልጠና አምስት ወራት ገደማ ይስዳል።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም ኤፍ-16 ጄቶችን ለዩክሬን ለመለገስ ቃል ገብታ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን አሜሪካ እና ኔቶ ይህ ሩሲያ ኒውክሌር እንድትጠቀም ምክንያት ሊሆናት ይችላል በማለት ውሳኔውን ቀልብሰውታል።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎችም በአብራሪዎቹ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን እየገለጡ ይገኛሉ።