ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ብሪክስን መቀላቀል ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ምን ያስገኛል?
በደቡብ አፍሪካዋ የንግድ መዲና ጆሃንስበርግ 15ኛውን ጉባኤያቸውን ያካሄዱት የብሪክስ አገራት ኢትዮጵያን አዲስ የስብስቡ አባል አድርገው ከሌሎች አምስት አገራት ጋር ተቀብለዋታል።
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ግብፅ፣ አርጀንቲና፣ ኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ ከሚቀጥለው ዓመት ጥር ጀምሮ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ተወስኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ቡድኑን የተቀላቀለችው በታሪኳ፣ በሕዝብ ብዛቷ በተለይ ደግሞ በዓለም ላይ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ስለታመነበት እና የመደመጥ አቅሟም እያደገ በመምጣቱ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል መወሰኑም ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብሎም ለአፍሪካ “ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በስብሰባው ወቅት የብሪክስ መሥራች አባል ከሆኑት አገራት ቻይና እና ሕንድ መሪዎች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።
ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር በነበራቸው ውይይት የሚቀጥለው ዓመት የዕዳ ክፍያን በተመለከተ የሚደረገው አጠቃላይ የዕዳ ሽግሽግ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የአንድ ዓመት የዕዳ እፎይታ እንዳገኙ ተናግረዋል።
ከሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሙዲ ጋር ባደረጉት ንግግርም በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ፣ በወታደራዊ፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት አብረው ለመሥራት ተስማምተናል ብለዋል።
ለመሆኑ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የመሠረቱትን ብሪክስን መቀላቀል ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ምን ያስገኛል?
ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድ፣ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆኗ በምጣኔ ሃብቷ ላይ የሚያስገኝላትን ጥቅም ለመዘርዘር በቅድሚያ ከብሪክስ የምታገኘው ዕድል ምን እንደሆነ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያም ይህንን ዕድል ለመጠቀም በምላሹ ምን ማድረግ እንዳለባት ማወቅ ያስፈልጋል ይላሉ።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም አባል በነበረችበት አጎዋ (የአፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌን) ጥሬ እቃዎችን ያለ ቀረጥ ወደ አሜሪካ በመላክ ተጠቃሚ እንደነበረች በማንሳት ብሪክስም መሰል ዕድል ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ይናገራሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በአገራቱ ከተቋቋመው የልማት ባንክ ብድር የማግኘት ዕድል ሊኖራት እንደሚችል ይጠቅሳሉ።
“ምን አልባት የብሪክስ አባል ከሆነች፣ ከዚህ ባንክ ብድር ለማግኘት እንደ የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ጥብቅ የሆነ ግዴታ ላይኖርባት ይችላል። ኢትዮጵያም የውጭ ምንዛሬ በጣም ስለምትፈልግ ያንን የማግኘት ዕድል ይኖራታል” ብለዋል።
አቶ አብዱልመናን እንደሚሉት አሁን ላይ የብሪክስ ስምምነት ዝርዝር ባይታወቅም፣ የብሪክስ አገራት ኤክስፖርት ሲያደርጉ ቀረጥ የማያስከፍሉ ከሆነ ወደ ኢትዮጵያም ሲልኩ ኢትዮጵያ እንዳትቀርጥ ሊያደርጉ ይችላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ በቅርቡ የባንክ ፖሊሲዋን ብታሻሽልም የንግድ እና የፋይናንስ ሕጓ ላይ ተጨማሪ ማሻሻያ ማድረግ ሊጠበቅባት እንደሚችልም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
የብሪክስ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም
ብሪክስ በተለይም ደቡባዊ የዓለም ክፍልን በማማከል አዲስ አሰላለፍ እየፈጠረ ያለ ቡድን እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ቡድኑ ምዕራባውያኑን ለመገዳደር የተቋቋመ እንደሆነም ይታሰባል።
ከምዕራባውያኑ ጋር የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ምን ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅምስ ያስገኝላታል?
አምባሳደር እውነቱ ብላታ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ “ዲፕሎማሲያዊ ድል አይመስለኝም” ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ነው የሚሉት አምባሳደር እውነቱ፣ በደርግ ሥርዓትም ሆነ በኢህአዴግ ዘመን ከምሥራቁ ዓለም ጋር ግንኙነት ቢኖርም በተለይ በኢህአዴግ ዘመን ከሁለቱም ጋር ያለውን ግንኙነት አመጣጥኖ ለመሄድ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ያወሳሉ።
ይሁን እንጂ ባለፉት አምስት ዓመታት ከምዕራባውያኑ ጋር የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ጦርነት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት በጣም እየተዳከመ ሄዷል ይላሉ።
በመሆኑም ብሪክስ ገና ያልተፈተነ ስብስብ በመሆኑ እና በአባላቱ መካከል የሚኖረው ግንኙነት ምን ይሆናል የሚለው ባልታወቀበት ሁኔታ ቡድኑን በመቀላቀሏ የሚገኝ ዲፕሎማሲያዊ ድል አይታየኝም ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑን የተቀላቀሉ አገራት በኢኮኖሚ አቅማቸውም ሆነ በዓለም አቀፍ ተፅዕኗቸው የሚወዳደሩ አገራት ባለመሆናቸው ስኬት ነው አይደለም ለማለት ብዙ ጊዜ እንደሚፈልግ አምባሳደር እውነቱ ተናግረዋል።
“የዓለም አቀፉን ዲፕሎማሲያዊ ምኅዳር ተቆጣጥረው ከነበሩት ጋር ያለውን ግንኙነት እያፈረሱ እና እያዳከሙ አዲስ ከሚመጣው ጋር መግባት አላስፈላጊ መስዋዕትነት ሊያስክፍል ይችላል” ሲሉም ያስጠነቅቃሉ።
“ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ፈተና ውስጥ ገብቷል” የሚሉት አምባሳደሩ፣ ይህ ሲጨመርበትም “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” ነው የሚሆነው ብለዋል።
ከሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥበቃ ጋር በተያያዘም፣ ብሪክስ ውስጥ ያሉ አገራት ለልማት የሚሰጡት ብድር እና ድጋፍ እንጂ የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥበቃ ጉዳይ እንደ ቅድመ ሁኔታ ባለመካተቱም በአገራቱ የሚፈፀሙ ጥሰቶች ከቁብ እንዳይቆጠሩ በር ሊከፍት ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
“የምዕራቡ ዓለም የራሱ ፖለቲካዊ ፍላጎት ቢኖርም ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው የሰብዓዊ እና የዲሞክራሲያዊ መብት ጥበቃ አንዱ ምሰሶ ነው። ይህም ለአገራቱ ይጠቅም ነበር።ይህንን የሚነቅፉት አምባገነን የሆኑ መሪዎች እና ድርጅቶች ናቸው” ይላሉ።
በመሆኑም ሚዛኑን የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊኖር እንደሚገባ ይመክራሉ።
የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል እና ምዕራባውያን
የብሪክስ አባል አገራት ቡድናቸው እንደ ምዕራባውያን ተገዳዳሪ እንዲታይ አይፈልጉም። ነገር ግን ብሪክስ የምሥራቅ ኃያል አገራትን ያካተተ ስብስብ ነው። ለመሆኑ ብሪክስን መቀላቀል ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ሊያሻክር ይችላል?
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ አብዱልመናን ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል ሲወሰን “ከምጣኔ ሃብቱ ይልቅ በፖለቲካዊ መንገድ የታሰበች ይመስለኛል” ይላሉ።
ብሪክስ ውስጥ የገቡ አገራትም ፖለቲካቸውም ሆነ ምጣኔ ሃብታቸው የተለያዩ መሆናቸውን የጠቀሱት ባለሙያው፤ “ኢትዮጵያ የተመረጠችው ለአፍሪካ መግቢያ በር ስለሆነች ይመስለኛል። በመሆኑም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋታል” ሲሉ አሳስበዋል።
“ከምሥራቁም ከምዕራቡም ጋር ያላትን የግንኙነት ሚዛን ጠብቃ መሄድ ይስፈልጋታል” ሲሉም መክረዋል።
አምባሳደር እውነቱም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።
የደርግ ሥርዓት የወደቀው ከምዕራቡ ጋር ያለው ግንኙነት ደካማ ስለነበር ነው ሲሉም ታሪካዊ ተሞክሮን እንደ አብነት ያነሳሉ።
የምዕራባውያኑ ኃይልነት በቀላሉ እና በአጭር ጊዜ የሚለቅ ባለመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በእነዚህ ሽኩቻዎች ውስጥ ገብተው ሊላተሙ እንደሚችሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
“መርከቦች ሲቀዝፉ ትንንሽ ጀልባዎች እንዴት እንደሚቀዝፉ ካላወቁ፣ አንደኛውን ቡድን ለማስቀናት እና ሌላኛውን ለማስደሰት የሚደረገው ሩጫ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል” ብለዋል አምባሳደሩ።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር በመሆኗ ብሪክስን የመቀላቀል መብት ቢኖራትም፣ ሚዛኗን አስጠብቃ መሄድ ካልቻለች ምዕራባውያኑ በሚሰጡት ድጋፍ እና እርዳታ ተዘዋዋሪ ጫና ሊገጥማት እንደሚችልም ጠቁመዋል።