ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በማላዊ ለፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የተዘጋጀ ቀይ ምንጣፍ ተሰረቀ
በደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ማላዊ የአገሪቱ መሪ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ለሚያደርጉት የሥራ ጉብኝነት የተዘጋጀ ቀይ ምንጣፋ መሰረቁ ተዘገበ።
ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻክዌራ በደቡብ ማላዊ በምትገኘው ምዋንዛ ከተማ ዛሬ አርብ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል።
ይሁን እንጂ ረቡዕ ምሽት ላይ ማንነታቸውን ያልታወቁ ሌቦች ምንጣፉን እና ድንኳኖችን እየተጓዘ ከነበረ ተሽከርካሪ ላይ መስረቃቸው ተገልጿል።
የአገሪቱ ፖሊስ በምንጣፍ እና ድንኳን ስርቆት የጠረጠራቸውን ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።
ሁለቱ ሰዎች ለፕሬዝዳንቱ አቀባበል ዝግጅት ምንጣፍ እና ድንኳን ጭኖ ወደ ከተማዋ እየገባ ከነበረ ተሸከርካሪ ላይ ሳይሰርቁ አይቀርም ተብሏል።
ስርቆቱ የተፈጸመበት አካባቢ ነዋሪ የሆነች አንዲት ሴት ማላዊ24 ለተባለ ጋዜጣ እንደተናገረችው በአካባቢው ያለው መንገድ ዳገታማ በመሆኑ በዝግታ ከሚጓዙት ተሸከርካሪዎች ላይ ንብረት መሰረቅ የተለመደ ነው።
“በዳገታማው መንገድ ምክንያት ምሽት ላይ ሰዎች እንደ ስኳር፣ ምርጥ ዘር፣ በቆሎ እና ሌሎች ነገሮችን ይሰረቃሉ። በጣም ብዙ ሰዎች ብስጭታቸውን ሲገልጹ እንሰማለን” በማለት ይህች ሴት ተናግራለች።
ፕሬዝዳንት ቻክዌራ በከተማዋ የተገነባውን አዲስ ስታዲየም ለመመረቅ እና የፖሊስ አባላት መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሂደትን ለመጎብኘት ነው ለሥራ ጉብኝት ወደ ምዋንዛ ከተማ የሚያቀኑት።
የምንጣፍ እና የድንኳኖች ስርቆት የተሰማው ከጥቂት ቀናት በፊት እስካሁን ማንነታቸው ያልተለዩ ግለሰቦች በመዲናዋ ሊሎንግዌ ከሚገኘው ምክትል ፕሬዝዳንት ቢሮ ዘረፋ መፈጸማቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።