እስራኤል የጋዛን የተኩስ አቁም ለማራዘም ወሰነች

የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ ድንበር ላይ ታንክ ላይ ቆመው ይታያሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እስራኤል የሙስሊም ረመዳን እና የአይሁዶች የፋሲካ በዓል እስኪያልፍ ድረስ በሚል ለቀጣይ ስድስት ሳምንታት የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነትን በጊዜያዊነት ለማራዘም ወሰነች።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ይህንን ያስታወቀው ቀደም ሲል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ ቅዳሜ እኩለ ሌሊት ላይ ካበቃ በኋላ ብዙም ሳይዘገይ ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ባቀረቡት የተኩስ አቁም ሃሳብ መሰረት፣ እስካሁን ሃማስ በጋዛ ካገታቸው መካከል ግማሾቹ ፣ በሕይወት ያሉ እንዲሁም የሞቱ፣ በመጀመሪያው ቀን እንደሚለቀቁ የኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ቀሪዎቹ ታጋቾች "ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከተደረሰ" ሊለቀቁ ይችላሉ ይላል መግለጫው።

ሃማስ ስለ አዲሱ የእስራኤል እርምጃ በይፋ የሰጠው አስተያየት የለም።

የእስራኤል መንግሥት በኔታንያሁ በተጠራ ስብሰባ ላይ ለአራት ሰዓታት ከተነጋገረ በኋላ የተኩስ አቁም መራዘሙን ደግፏል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሃማስ የዊትኮፍ እቅድን ለመደገፍ "እስካሁን ፈቃደኛ አልሆነም" ሲል ቡድኑ አቋሙን ከቀየረ እስራኤል ወዲያውኑ ድርድር እንደምትጀምር ተናግሯል።

ፍልስጤማውያን በጋዛ

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

በአሜሪካው ልዑክ ዕቅድ መሰረት እስራኤል በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ የሚደረገው ድርድር አልተሳካም ብላ ካመነች ከ42 ቀናት በኋላ ወደ ጦርነት ልትመለስ ትችላለች።

አርብ ምሽት ላይ ሃማስ የድርድር ቀጣይ ምዕራፍ እንደሚካሄድ ከአሜሪካ፣ ከኳታር እና ከግብፅ ሸምጋዮች ዋስትና ካላገኘ በስተቀር በምዕራፍ አንድ የተኩስ አቁም ማራዘም እንደማይስማማ ተናግሮ ነበር።

ሃማስ፣ በእስራኤል በተያዘው ዌስት ባንክ የፍልስጤም አስተዳደርን ጨምሮ የዕለት ከዕለት አስተዳደርን ለሌሎች የፍልስጤም ተዋናዮች ለማስረከብ ፈቃደኛ ቢሆንም በጋዛ ግን የጦር ኃይል ሆኖ ለመቀጠል የቆረጠ ይመስላል ሲል የቢቢሲው ፖል አዳምስ ከኢየሩሳሌም ዘግቧል።

እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በጥር 19 ተግባራዊ የሆነው የተኩስ አቁም የመጀመሪያው ምዕራፍ ትናንት፣ ቅዳሜ ዕለት፣ አብቅቷል።

ስምምነቱ በሃማስ እና በእስራኤል ጦር መካከል ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት በማቆም 33 እስራኤላውያን እና አምስት የታይላንድ ታጋቾችን እንዲሁም 1,900 የሚሆኑ የፍልስጤም እስረኞች ነጻ እንዲወጡ አስችሏል።

ነገር ግን በቀጣይ ቀሪ ታጋቾችን ማስልቀቅ እና የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ እንዲወጡ የሚጠይቀው የድርድር ምዕራፍ ገና አልተጀመረም።

አሁንም 24 ታጋቾች በሃማስ እጅ በሕይወት እንዳሉ ሲገመት ሌሎች 39 ሰዎች ሞተዋል ተብሎ ይታመናል።

ሃማስ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 7 2023 በእስራኤል ላይ በድንገት ጥቃት ፈጽሞ፣ ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ሲሞቱ 251 ደግሞ ታግተዋል።

እስራኤል ለጥቃቱ በጋዛ ሰርጥ ባደረገችው የአየር እና የምድር ዘመቻ ምላሽ የሰጠች ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ቢያንስ 48,365 ሰዎች መሞታቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።