ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን በአሜሪካ ለተፈጸመባት ጥቃት ምን ዓይነት ምላሽ ልትሰጥ ትችላለች?
የእስራኤል እና ኢራን ጦርነት ሁለተኛ ሳምንቱን ሊይዝ በተቃረበበት ጊዜ፤ አሜሪካ ጥብቅ ጥበቃ የሚደረግለትን የፎርዶን ጨምሮ በሦስት የኢራን ቁልፍ የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ያሳየችው ጣልቃ ገብነት በቴህራን አለመረጋጋትን ፈጥሯል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ 13,600 ኪሎግራም የሚመዝነው እና የተቀበሩ ዒላማዎችን ለመምታት የሚውለው "ማሲቭ ኦርዲንስ ፔኔትሬተር" የተባለ ቦምብ ከመሬት በታች የሚገኙኘውን ፎርዶ የኒውክሌር ጣቢያን ጨምሮ ናታንዝ እና ኢስፋሃንን ለመምታት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቅደዋል።
አሜሪካ በጥቃቱ ጣቢያዎቹ "ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል" ያለች ሲሆን፣ ቴህራን የአጸፋ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ ከዚህም "እጅግ የላቀ ኃይል" እንደምትጠቀም አስጠንቅቃለች።
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እንደዚህ ዓይነት የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የሚኖር ከሆነ "የማይጠገን ጉዳት" ሊደርስ እንደሚችል ቀድሞውኑም ተናግረው ነበር።
እናም አሁን እስላማዊ ሪፐብሊኩ አስቀድሞ ያዘጋጃቸውን በርካታ አማራጮችን እያመዛዘነ ነው።
በቀጣናዉ የሚገኙ አሜሪካ የጦር ሰፈሮችን ማጥቃት
ኢራን ማንኛውም የዩናይትድ ስቴትስ ጥቃት በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካን ፍላጎት ያለባቸውን ስፍራዎች በሙሉ ዒላማ ውስጥ እንደሚያስገባ ቀድማ አስጠንቅቃለች።
አብዮታዊ ዘብ ከጥቃቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ ጥቃቱን ያመቻቹት የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ያላቸውን ተጋላጭነት በመጥቀስ የቴህራን ምላሽ "አሜሪካን በድርጊቷ እንድትጸጸት ያደርጋታል" ብሏል።
በኢራቅ፣ በባህሬን፣ በኳታር፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በሳውዲ አረቢያ፣ በኩዌት፣ በዮርዳኖስ እና በሶሪያ የሚገኙት ሁሉም የአሜሪካ ማዘዣ ሰፈሮች የኢራን ባላስቲክ ሚሳዔሎች ሊደርሱ የሚችሉባቸው ናቸው።
ከተጠቃሾቹ ስፍራዎች መካከል ኳታር ውስጥ ያለው ሰፊው የአል ኡዲድ አየር ኃይል ሰፈር እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ የሚንቀሳቀሰው የአሜሪካ 5ኛው የባሕር ኃይል ዕዝ የሚያርፍበትን እና ባህሬን ውስጥ የሚገኘው የባሕር ኃይል ሰፈር ይገኙበታል።
በአውሮፓውያኑ 2020 ኢራን በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካን ወታደሮች የሚያስተናግደውን የአል አሳድ አየር ኃይል ሰፈር መትታ እንደነበር ይታወሳል። አሜሪካ በፕሬዝዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ በወሰደችው የአጸፋ ምላሽ የኢራን ከፍተኛ የጦር አዛዥ የነበሩትን ጄነራል ቃሲም ሱሌማኒን ገድላለች።
ቴህራን ጥቃቱን ከመፈጸሟ አስቀድሞ ለአሜሪካ ማስጠንቀቂያ በመስጠ በጥቃቱ ምንም ሰው አልሞተም። ነገር ግን ተምሳሌታዊ ምላሽ ተደርጎ እንዲታይ በሚያስችል መልኩ በጦር ሰፈሩ ላይ ጉዳት አድርሷል።
በዚህ ጊዜም ቴህራን ተመሳሳይ አካሄድ ልትከተል ትችላለች።
ይሁን እንጂ አሁን ባለው የከፍተኛ ውጥረት ሁኔታ፤ ግጭት ቀጥሎ ኢራን ተጨማሪ የምታጣው ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሰማት የሚያደርግ ደረጃ ከደረሰ፤ በቀጣናው የሚገኙ ኤምባሲዎችን ጨምሮ ወታደራዊ ያልሆኑ የአሜሪካ ጥቅም ያለባቸው ስፍራዎች ላይ ቀጥተኛ ጥቃቶች የመፈጸም ሀሳብ ጠረጴዛው ላይ ሊቀርብ ይችላል።
ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚያስከትለው አደጋ ግን እጅግ ከፍተኛ ነው።
የሆርሙዝ ሰርጥን መዝጋት
የድፍድፍ የነዳጅ ዘይት መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ሰርጥ የመዝጋት ጉዳይ በኢራን እና በምዕራባውያን ባላንጣዎቻቸው መካከል የሚፈጠር ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ጊዜ ሁሉ በኢራን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ለዓመታት ሲደጋገም የቆየ የተለመደ ማስፈራሪያ ነው።
ይህ ጠባብ የባህረ ሰላጤ የውሃ መተላለፊያ፤ አንድ አምስተኛ የሚጠጋው የዓለም አቀፍ ነዳጅ የሚተላለፍበት የባሕር መስመር ስትራቴጂካዊ ማነቆ መፍጠሪያ ነጥብ ነው።
አሁን ላይ ሆርሙዝን የመዘጋት ሃሳብ እየጠነከረ የመጣ ሲሆን፣ የከረረ አቋም ያላቸው አካላትም እርምጃው በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ እና በአሜሪካ ኢኮኖሚ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ከፍተኛ ጉዳት በመጥቀስ ሀሳቡን ይደግፋሉ።
የሆርሙዝ ሰርጥን የመዝጋት አማራጭ በተለያዩ ወታደራዊ መንገዶች ሊፈጸም ይችላል። ከእነዚህ መካከል በባሕር ውስጥ ሚቀበሩ ፈንጂዎችን በመጠቀም፣ ረጅም ርቀት የሚጓዙ ክሩዝ ሚሳዔሎችን በማስወንጨፍ እንዲሁም የባሕር ኃይልን መጠቀም ይገኙበታል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሲያመርት እና ሲያከማቻቸው የነበሩ ፈጣን የጥቃት ጀልባዎችም ሰርጡን ለመዝጋት ሊውሉ ይችላሉ።
ነገር ግን የሆርሙዝ መዘጋት ኢራን ዋና የነዳጅ ደንበኛዋ ከሆነችው ከቻይና ጋር ባላት የንግድ ትስስር ላይም ተጽዕኖ ስለሚኖረው እርምጃው ያልተጠበቀ ውጤት ሊያስከትል ይችላል።
ኢራን በባሕረ ሰላጤው እና በቀይ ባሕር ላይ የሚገኙ መርከቦችን እና ተቋማትን በድሮን፣ ሚሳዔሎች እና በተቀበሩ ፈንጂዎች የጥቃት ዒላማ የማድረግ ታሪኳ እምብዛም ነው።
ከሰሞነኛው የአሜሪካ ጥቃት በኋላ ግን ቴህራን እንደ ሳዑዲ አረቢያ ወይም አረብ ኤምሬቶች ባሉ በአቅራቢያዋ ባሉ ሀገራት ውስጥ ሚገኙ የነዳጅ ማከማቻዎችን፣ ወደቦችን ወይም የኃይል ተቋማትን ዒላማ በማድረግ ከፍ ባለ መጠን እርምጃ የምትወስድበት ዕድል አለ።
ይህንን በማድረግ የዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ድንጋጤ መፍጠርን ተስፋ ልታደርግ ትችላለች።
በትራምፕ ትዕዛዝ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ በተለይም የኢራን አክራሪ አመራሮች የሳዑዲ አረቢያ የኃይል ማመንጫ ተቋማትን የማጥቃት ዕቅድን ያነሱት ወዲያውኑ ነበር።
የእጅ አዙር ኃይሎችን የመጠቀም ሀሳብ
ከእስራኤል ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት እንዲሁም የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት፤ በኢራን እና ከእርሷ ጋር ግንኙነት ባላቸው የቀጣናው አጋር ታጣቂዎች መካከል "የችግር ጊዜ ወዳጅነትን" ሊያስነሳ ይችላል።
በአሜሪካ ንብረቶች ወይም የአቅርቦት መስመሮች ላይ የእጅ አዙር ኃይሎች የሚፈጸሙ የተቀናጁ ጥቃቶች በተገደበ ደረጃም እንኳን ቢካሄዱ በአሜሪካ እና በቀጣናው ባላት ጥቅም ላይ ትክክለኛ ስጋት ይደቅናል።
ይሁን እንጂ ኢራን ምንም እንኳ ለዓመታት እነዚህን ቡድኖች በገንዘብ ስትደግፍ እና መሳሪያ ስትሰጥ የነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ታጣቂዎቹ ወታደራዊ ጥንካሬያቸው ተዳክሟል። በዚህም የተነሳ ትርጉም ባለው መልኩ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላል።
ካለፈው ዓመት ጥቅምት እስከ ዘንድሮ ኅዳር ድረስ ከእስራኤል ጋር በተካሄደው ጦርነት የተዳከመው ሔዝቦላህ እስካሁን ድረስ ጦርነቱን እየተመለከተ ያለው በታዛቢት ነው። የኢራን ኃይሎችን ለመርዳት ጠንካራ ቁርጠኝነትም አላሳየም።
ሔዝቦላህ ትጥቅ እንዲፈታ እንዲሁም መልሶ ግንባታ እና ራሱን የቤይሩት መንግሥት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ እንዲያካትት በሊባኖስ መንግሥት እና መገናኛ ብዙኃን ጫና እየደረሰበት ነው። የሀገሪቱ መንግሥት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል መልሶ ግንባታ እና የተራዘመውን ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ መፍታትን ይገኙበታል።
የየመን ሁቲዎችም በአሁኑ ጦርነት ወቅት በእስራኤል ላይ የሚያደርሱት ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ አልታየም። ከሰሞነኘው የአሜሪካ ጥቃት በፊት እና በኋላ ግን በቀይ ባሕር ላይ የአሜሪካ መርከቦችን የጥቃት ዒላማ እንደሚያደርጉ አስጠንቅቀዋል።
እነዚህን ቃላት ወደ ተግባር መቀየር ባለፈው ግንቦት ከዋሽንግተን ጋር የተስማሙበትን የተኩስ አቁም መጣስ ማለት ይሆናል።
ከኢራቅ በኩል እስከአሁን ማስጠንቀቂያዎች ከመስጠት እና አጋርነትን የሚያሳዩ መግለጫዎችን ከማውጣት የዘዘለ የታማኝነት ምልክት አልታየም።
በሶሪያ ደግሞ የኢራን አጋር የሆነው ባሻር አል-አሳድ ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ ከደማስቆ መንግሥት እና ከምትደግፋቸው ቡድኖች የምታገኘው ድጋፍ እየቀነሰ መጥቷል።
ይህም ቢሆን ግን እስላማዊ ሪፐብሊኩ ለ46 ዓመታት የዘለቀውን የሥልጣን መሠረቱን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ከባድ የጦርነት መባባስ የሚከሰት ከሆነ የቀጣናው አጋር ቡድኖች በተለያየ ደረጃም ሊሳተፉ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኃይሎቹ ተሳትፎ የሚወሰነው በአሁኑ ወቅት ባላቸው ሀብት ላይ ነው።
የስጋት ግምገማ
ከቴል አቪቭ ጋር እየተደረገ ባለው ጦርነት ኢራን ትኩረቷን ያደረገችው በእስራኤል ከተሞች እና ወታደራዊ ተቋማት ላይ ሚሳዔሎችን ማስወንጨፍ ላይ ነው። ይህም የአሜሪካን ምላሽ ሊያስከትል የሚችል ማንኛውንም እርምጃ ከመውሰድ ለመቆጠብ ጠባቡን መንገድ እየተራመደ እንደሆነ ያመለክታል።
ጦርነቱ አሁን በያዘው አቅጣጫ ከቀጠለ ኢራን ወደ እስራኤል የምታስወነጭፋቸውን ሚሳዔሎች ብዛት መገደብ ሊኖርባት ይችላል። በመጀመሪያው ቀን ጥቃት የተተኮሱት 150 ሚሳዔሎች ሲሆኑ፣ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ግን ቁጥሩ በቀን ወደ 30 ያህል ቀንሷል።
የመሳሪያ ክምችት ቀነሰ ማለት በአሜሪካ ንብረቶች ላይ ሰፊ እና የተራዘመ ዘመቻ ለማካሄድ የሚኖርን አቅም ውስን ያደርገዋል ማለት ነው።
በአሜሪካ ላይ የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ኢራን በሁለት ግንባሮች ጦርነት እንድትገጥም ሊያደርጋት ይችላል። የበቀል እርምጃ የአሜሪካን ከፍተኛ የመልሶ ማጥቃት ጥቃቶች የመጋበዝ እንዲሁም የእስላማዊ ሪፐብሊኩን አመራርን ወደ ገደል አፋፍ የመግፋት ዕድል አለው።
የኢራን መሪዎች አማራጮቻቸውን እና መዘዞቹን ሲያመዛዝኑ ምናልባትም አንድ ዓይኑን በሕይወት የመቆየት ጥያቄ ላይ ማድረጉ አይቀርም። ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ ከባድ ግጭት የሚያስከትለው መዘዝ የማይገመት፣ የኅልውና ጥያቄን የሚያስነሳ ሊሆን ይችላል።