ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት እንዴት ጀመረ? ምን ያህል ጉዳትስ አደረሰ?
ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሰደድ እሳት የሎስ አንጀለስን አንዳንድ አካባቢዎችን ወደ አመድነት እየቀረ ነው። እስካሁን ቢያንስ የ10 ሰዎች ሕይወት አልፏል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕንፃዎች ተቃጥለዋል። ወደ 180 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲለቁ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል።
የእሳት አደጋ ተከላካዮች ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም እሳቱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አልተቻላቸውም። ካለው የአየር ሁኔታ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ጋር ተያይዞ በመጪዎቹ ቀናት እሳቱ ተባብሶ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።
እስካሁን ያለውጉዳት ምን ይመስላል?
ከሎስ አንጀለስ ወደ 180 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው እንዲለቁ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል። ብዙዎቹ የቻሉትን ዕቃ ይዘው ቤታቸውን ጥለው ወጥተዋል። 200 ሺህ ነዋሪዎች ደግሞ ለመልቀቅ ተዘጋጁ የሚል ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል። እነዚህ ሰዎችም በቅርቡ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሊደርሳቸው ይችላል ማለት ነው።
ቢያንስ 10 ሰዎች መሞታቸውን እና አስከሬናቸውም እየተለየ መሆኑን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
ሐሙስ ዕለት ባለሥልጣናቱ በፓስፊክ ፓሊሳዴስ የእሳት አደጋ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ለመጀመሪያ ጊዜ አረጋግጠዋል። ከአንድ ቀን በፊት እንደተናገሩት ከሆነ ደግሞ በኤቶን እሳት የሞቱት ሰዎች አምስት ሳይሆኑ ሦስት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የሎስ አንጀለስ አካባቢ ፖሊስ ሮበርት ሉና እንደተናገሩት ከሆነ በአንዳንድ አካባቢዎች ዘረፋ እና ስርቆት ተስፋፍቷል። እስካሁንም 20 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
አዲስ እሳት ደግሞ ሐሙስ ዕለት በከተማው ዌስት ሂልስ አካባቢ ተቀስቅሷል። የእሳት አደጋውን ቀስቅሷል በሚል አንድ ሰው ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።
የሌሎቹ ቃጠሎዎች መንስኤ እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን በምርመራ ላይ ይገኛል።
በሎስ አንጀለስ ታሪክ እጅግ አስከፊ በሆነው የፓሲፊክ ፓሊሳዴስ እሳት 5300 ያህል ቤቶች ወድመዋል። አምስት ሺህ ሕንፃዎች ደግሞ ከከተማዋ ወጣ ብላ በምትገኝ አካባቢ በኤቶን እሳት ወድመዋል።
በርካታ ታዋቂ ሰዎች ቤታቸውን በእሳቱ ምክንያት አጥተዋል። ሌይተን ሚስተር፣ አዳም ብሮዲ እና ፓሪስ ሂልተን ይጠቀሳሉ።
ይህም በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ወጪን ካስወጡ የሰደድ እሳቶች አንዱ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት የመድን ኩባንያዎችን ረብሿቸዋል። ቃጠሎው ውድ በሚባሉ አካባቢዎች ላይ በመከሰቱ ከ8 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንሹራንስ ኪሳራ ይጠበቃል።
በደቡብ ካሊፎርኒያ ያለው የእሳት አየር ሁኔታ "ከእጅግ አሳሳቢ" ወደ "አሳሰቢ" መቀነሱ ለእሳት አደጋ ተከላካዮች የተስፋ ጭላንጭል ፈጥሯል።
የቢቢሲ የአየር ሁኔታ ትንበያ ባለሙያዋ ሳራ ኪት-ሉካስ ግን ቢያንስ እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ በአካባቢው ምንም ዓይነት ዝናብ አይጠበቅም። ይህም ለእሳቱ የበለጠ የተመቸ መሆኑን ገልጻለች።
በአብዛኛው የከተማው አካባቢ መብራት ተቋርጧል። የትራፊክ መጨናነቅም ተከስቷል። በርካታ ትምህርት ቤቶች እና የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሎስ አንጀለስ (ዩሲኤልኤ) ለመዝጋት ተገድደዋል።
አንዳንድ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ውሃ ማጣታቸው ከታወቀ በኋላ በከተማዋ ዝግጁነት ላይ ፖለቲካዊ አለመግባባት ተፈጥሯል። ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትችት ሰንዝረዋል።
የሎስ አንጀለስ ካውንቲ የእሳት አደጋ መከላከያ አዛዥ አንቶኒ ማሮን ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ውሃ አልቆባቸውም ወይም ዝቅተኛ የውሃ ግፊት እንዳጋጠማቸው የሚገልጹ ሪፖርቶች እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል።
የፓሳዴና የእሳት አደጋ መከላከያ አዛዥ ቻድ አውጉስቲን በበኩላቸው በአካባቢው አነስተኛ የውሃ ግፊት ለአጭር ጊዜ አጋጥሞ ነበር ብሏል። በኋላ ላይ ግን ሁሉም ችግሮች ተፈትተዋል ብለዋል።
በርካታ የእሳት አደጋ መከላከያ መኪኖች በተመሳሳይ ጊዜ ውሃ መሳባቸው እና የኃይል መቆራረጥ ለውሃ ግፊቱ መቀነስ ምክያት መሆኑን አክለዋል።
እሳቱ የትኞቹን አካባቢዎች እያወደመ ነው?
የካሊፎርኒያ የእሳት አደጋ ባለሥልጣናት ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቁት ከሆነ ቢያንስ በአምስት አካባቢዎች እሳት ተከስቷል
- ፓሊሳዴስ: የመጀመሪያው እሳት ማክሰኞ ዕለት ተቀሰቀሰ። በክልሉ ውስጥ ትልቁ እሳት ሲሆን፣ በግዛቲቱ ታሪክ በጣም አውዳሚው እሳት ሊሆን ይችላል። ከፍተኛውን የፓሲፊክ ፓሊሳዴስ ሰፈርን ጨምሮ ወደ ከስምንት ሺህ ሔክታር በላይ የሚጠጋ አካባቢን አውድሟል። ሐሙስ ምሽት ድረስ 6 በመቶው ብቻ በቁጥጥር ስር ውሏል።
- ኢተን፡ ይህኛው እሳት የሎስ አንጀለስን ሰሜናዊ ክፍል አጥቅቷል። እንደ አልታዴና ያሉ ከተሞችን በእሳቱ እየወደሙ ነው። ወደ 5665 ሔክታር የሚጠጋ አካባቢን የሚያቃጥለው እሳት በአካባቢው ሁለተኛው ትልቁ እሳት ነው። ዜሮ በመቶው ብቻ በቁጥጥር ስር ውሏል።
- ኸረስት፡ ከሳን ፈርናንዶ በስተሰሜን የሚገኘው አካባቢ ማክሰኞ ምሽት መቃጠል ጀመረ። ወደ 271 ሔክታር የተስፋፋ ሲሆን፣ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ለመቆጣጠር ሥራ ጀምረዋል።
- ሊዲያ፡ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ከሎስ አንጀለስ በስተሰሜን በምተገኘው ተራራማው አክቶን አካባቢ እሳቱ ተከሰተ። ወደ 141 ሔክታር የሚጠጋ አካባቢን አዳርሷል። 60 በመቶው እሳት በቁጥጥር ስር መዋሉን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
- ኬኔት፡ ይህ አዲስ እሳት ሐሙስ ዕለት በሎስ አንጀለስ እና በቬንቹራ አውራጃዎች ድንበር ላይ ተቀሰቀሰ። እስካሁን ወደ 404 ሔክታር አካባቢን አዳርሷል።
ቀደም ሲል የሰንሴት፣ ዉድሊ እና ኦሊቫስ እሳቶችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።
የአየር ንብረት ለውጥ ምን ዓይነት ሚና ተጫወተ?
ምንም እንኳን ኃይለኛ ንፋስ እና የዝናብ አለመኖር እሳቱን እያባባሰው ቢሆንም፤ የአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታዎችን እየቀየረ እና የእሳት አደጋ የመከሰት አጋጣሚውን እየጨመረ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ከሚከሰተው ትልቅ እና አስከፊ ሰደድ እሳት ጀርባ መሆኑን በማያሻማ መልኩ የአሜሪካ መንግሥት ጥናት ያሳያል።
"የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሙቀት መጨመር፣ የተራዘመ ድርቅ እና ውሃ የተጠማ ከባቢ በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ያለውን የሰደድ እሳት አደጋ እና መጠን ለመጨመር ቁልፍ ምክንያት ሆኗል" ሲል ብሔራዊ የውቅያኖስ እና የከባቢ አየር አስተዳደር ተናግሯል።
ባለፉት ወራት ዝናብ አለመኖሩ እና በጣም ሞቃታማውን የበጋ ወቅትን ተከትሎ ካሊፎርኒያ በተለይ ተጋላጭ ሆናለች።
በደቡባዊ ካሊፎርኒያ ያለው የእሳት ወቅት ከግንቦት እስከ ኅዳር እንደሚዘልቅ ይታሰባል። የግዛቱ ገዢ ጋቪን ኒውሰም እሳቱ ዘላቂ ችግር መሆኑን ቀደም ሲል ጠቁመዋል። "የእሳት ወራት ሳይሆን የእሳት ዓመት ነው ያለው" ብለዋል።