ትራምፕ ከፑቲን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ እያመቻቹ እንደሆነ አሳወቁ

ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ እየተመቻቸ እንደሆነ ተናግረዋል።

መጪው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሁለቱ መሪዎች የሚገናኙበትን ቀን አልጠቀሱም።

"እሱ እንድንገናኝ ይፈልጋል። የምንገናኝበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው" ሲሉ ትራምፕ ፍሎሪዳ ከሚገኘው ማራላጎ የተባለው የተንጣጣለ መኖሪያቸው አስተያየት ሰጥተዋል።

ክሬምሊን ይህን የትራምፕ ንግግር ተከትሎ በሰጠው አስተያየት ፑቲን ለውይይቱ ፈቃደኛ መሆናቸውን ጠቁሞ ነገር ግን የተቆረጠ ቀን እንደሌለ አሳውቋል።

ትራምፕ ጥር 20/2017 ዓ.ም. ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ በፍጥነት በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም ቃል ገብተዋል። ትራምፕ አሜሪካ ለዩክሬን የምትለግሰው ወታደራዊ እና የፋይናንስ እርዳታ ተገቢ አይደለም የሚል አስተያየት ከዚህ ቀደም ሰጥተው ነበር።

ሐሙስ ዕለት በሰጡት አስተያየት "ፕሬዝደንት ፑቲን መገናኘት ይፈልጋል" ብለዋል።

"ይህ በሕዝብ ፊት ያለው ነገር ነው። ጦርነቱን በፍጥነት መቋጨት አለብን። በጣም የተወሳሰበ ጦርነት ነው።"

የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አርብ ዕለት እንዳሉት ትራምፕ ቃለ-መሐላቸውን ከፈፀሙ በኋላ ከፍተኛ ልዑካን የሚሳተፉበት ንግግር እንደሚኖር ይጠበቃል።

ቃል አቀባዩ አክለውም የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከትራምፕ ጋር ምክክር እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።

ተመራጩ ፕሬዝደንት ትራምፕ የቀድሞው የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ እና የአሜሪካ ጦር ሉቴናንት ጀኔራል የነበሩት ኪዝ ኬሎግ የዩክሬን እና የሩሲያ ልዩ መልዕክተኛ እንዲሆኑ መሾማቸው ይታወሳል።

ኬሎግ ባሳተሙት የጥናት ፅሑፍ የዩክሬን ጦርነት ሊቋጭ የሚችልበትን የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል። ፅሑፉ ባለፈው ሚያዝያ አሜሪካ ፈርስት ፖሊሲ ኢኒስቲትዩት በተባለ የትራምፕ ደጋፊ በሆነ ድረ-ገፅ ላይ ነው የታተመው።

የመፍትሔ ሐሳቡ እንደሚለው ዩክሬን ከዩናይትድ ስቴትስ እርዳታ ማግኘት ያለባት ከሞስኮ ጋር የሰላም ድርድር ለማድረግ ፈቃደኛ ስትሆን ብቻ ነው።

ፅሑፉ አክሎ እንደሚጠቁመው ሞስኮ የሰላም ድርድር የማትፈልግ ከሆነ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ መቀጠል አለባት።

ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ኅዳር ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ዜሌንስኪ በሰጡት አስተያየት በትራምፕ ዘመነ መንግሥት "ጦርነቱ ይቋጫል" ማለታቸው አይዘነጋም።

ዜሌንስኪ በወቅቱ ከትራምፕ ጋር በስልክ "ገንቢ የሆነ ውይይት" ማድረጋቸውን ቢያሳውቁም ተመራጩ ፕሬዝደንት ከሩሲያ ጋር ስለሚደረግ የሰላም ውይይት ያስቀመጡት ቅደመ ሁኔታ እንዳለ ከመናገር ተቆጥበዋል።