ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ያፈነዳችውን የቻይና 'የስለላ' ፊኛ ስብርባሪ እየፈለገች ነው
አሜሪካ በአየር ክልሌ ገብቶ ሲሰልለኝ ነበር ያለችውን ፊኛ በታዋጊ ጄት ከአየር በተተኮሰ ሚሳኤል ካደባየች በኋላ ስብርባሪውን ፍለጋ ገብታለች።
የአሜሪካ ባሕር ኃይል ቀን ተሌት በፍለጋ ተሠማርቷል ተብሏል።
ጆ ባይደን ረቡዕ ዕለት ፊኛው በተዋጊ ጄት እንዲመታ የመጨረሻ ውሳኔ ካስተላለፉ በኋላ ሰው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የሚል ስጋት ሰለተፈጠረ ከባሕር ትይዩ እስኪሆን ቆይቶ ነው ቅዳሜ ዕለት እርምጃ የተወሰደበት።
አሁን ከፊኛው ጋር የተገጠመ ስብርባሪ በሳውዝ ካሊፎርኒያ ግዛት በሚገኝ የውሃ አካል ነው እየተፈለገ ያለው።
አሜሪካ ይህ የቻይና ፊኛ ለቀናት ሲሰልለኝ ነበር ትላለች።
የቻይና መንግሥት ደግሞ ለአየር ንብረት ጥናት ተልኮ ከኔ ቁጥጥር ውጭ ወደ አሜሪካ ሰማይ ተንሳፎብኝ ነው ስትል ታስተባብላለች።
የቀድሞ የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣን አድሚራል ማይክ ሙለር ምናልባት ቻይና የብሊንከንን ጉብኝት ለማደናቀፍ ሆን ብላ የላከችው ፊኛ ሳይሆን አይቀርም ብለው ጠርጥረው እንደበረ ለሚዲያ ተናግረዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ትናንት ቤጂንግ ሊሄዱ ቀጠሮ ተይዞላቸው ነበር።
ይሁንና የፊኛው ጉዳይ በቤጂንግና በዋሺንግተን መሀል ቅራኔ ስላስከተለ ጉብኝታቸው ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል።
ቻይና በዚህ መረጃ ይቃርም ነበር በተባለው ፊኛ ላይ የተወሰደው እርምጃ “ምንም አላስደሰተኝም” ስትል በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል ገልጣለች።
ለአየር ንብረት መረጃ ፍለጋ ተልኮ በዚያው እየተንሳፈፈ ወደ አሜሪካ ሰማይ ሄዶብኝ ነው የምትለው ቻይና አሜሪካ የወሰደችው እርምጃ ትክክል አይደለም ብላለች።
አድሚራል ሙለር በበኩላቸው “እንዲህ ዓይነት መረጃ ቃራሚ ፊኛዎች ያለ መቆጣጠሪያ ወደ ሰማይ አይላኩም፤ ቻይና ለስለላ እንደላከችው ምንም አያጠራጥርም” ሲሉ ተናግረዋል።
ሪፐብሊካኖች ጆ ባይደን ፈጥነው በፊኛው ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ባለማድረጋቸው አገራችንን እንድትሰለል አድርገዋል ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።
የሴኔት የደኅንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ማርኮ ሩቢዯ በበኩላቸው ለሲኤንኤን ጣቢያ እንደተናገሩት ይህ የቻይና የስለላ ፊኛ ነገ ማክሰኞ በሁለቱ ምክር ቤቶች ህብረት ባይደን የሚያደርጉትን ንግግር ለማደናቀፍና ፕሬዝዳንቱን ለማዋረድ የተደረገ ሙከራ ነው ብለዋል።
ይህ ፊኛ በተለይ አሜሪካ የወታደር ቀጠናዎች በሚገኙበት ሞንታና ግዛት ሰማይ ላይ ሲንሳፈፍ መሰንበቱ ቻይና ወታደራዊ መረጃዎችን ለመልቀም ተጠቅማበት ይሆናል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
አውሮፕላኖች ከሚበሩበት ከፍታ በላይ ሲንሳፈፍ የነበረው ፊኛ የሦስት የከተማ አውቶቡሶች መጠን ያለው ነው ተብሏል።
በአሜሪካ ኤፍ-22 ተዋጊ ጄት እንዲመታ ሲደረግም ፍንዳታው ከፍተኛ እንደነበር የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ስብርባሪው እስከ 11 ኪሎ ሜትር ያህል ተበታትኖ ስለወደቀ እሱን ለመልቀም ጊዜ ሊወስድ ይችላል።
ፊኛው በወደቀበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ማንኛውም ባዕድ ነገር ካገኙ ሪፖርት እንዲያደርጉና እንዳይነኩት ተነግሯቸዋል።
የአሜሪካ አቪየሽን በፊኛው ላይ እርምጃ ሊወሰድ ሲል ማንኛውም የመንገደኞች በረራ በአካባቢው ለሦስት ሰዓት ዝግ እንዲሆን አድርጎ ነበር።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ዐርብ ዕለት ሁለተኛው የቻይና መረጃ ለቃሚ ፊኛ በላቲን አሜሪካ ሰማይ ላይ መታየቱን ይፋ አድርገዋል።
በተመሳሳይ ቀን የኮሎምቢያ አየር ኃይል አንድ ምንነቱ ያልተለየ ግዙፍ ነገር በአገሪቱ የአየር ክልል እየገባ እንደሆነ ገልጿል። ይህ ፊኛ እንደሆነ የተገመተው ነገር በ55ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ነው የታየው።
ቻይና በዚህ ሁለተኛው መረጃ ለቃሚ ፊኛ ጉዳይ ያለችው ነገር የለም።