አሜሪካ ‘እየሰለለ አስቸገረኝ’ ያለችውን የቻይና ፊኛ አፈነዳች

ላለፉት ቀናት በቻይናና አሜሪካ መሀል ውጥረት እንዲነግስ ምክንያት የሆነውን የቻይና ፊኛ አሜሪካ መ’ታ ጣለች።

አሜሪካ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው በጉዳዩ ላይ ብዙ ካወጣችና ካወረደች በኋላ ነው።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፊኛዎቹ በተዋጊ ጄቶች ተመ’ተው እንዲወድቁ መደረጉን አረጋግጦ፣ የወደቁትም በውሃ አካል ላይ ነው ብሏል።

ከዚህ ቀደም ይህ ፊኛ ተመ’ቶ እንዲወድቅ የሚለው ሐሳብ ውድቅ ሆኖ የነበረው ምናልባት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነገር ይዞ ከሆነ በሚል ነበር።

የቻይና መንግሥት በጉዳዩ ላይ ለተወሰነ ጊዜ ዝምታን ከመረጠ በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣው መግለጫ አሜሪካ በፊኛው ላይ በወሰደችው እርምጃ “ፍጹም ደስተኛ አይደለሁም” ብሏል።

ፊኛውን መ’ትቶ በአንድ ሚሳኤል የጣለው የአሜሪካ ኤፍ-22 ተዋጊ ጄት ነው ተብሏል።

የፊኛው የውስጥ ስብርባሪ በማይርትል የባሕር ዳርቻ ሳውዝ ካሮላይና ግዛት ወድቋል።

የተወሰነው ስብርባሪ ዉሃ ጥልቀት ውስጥ የገባውም 14 ሜትር ያህል ብቻ ነው።

አሁን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ፊኛው ላይ ተገጥሞ የነበረን ስብርባሪ እየለቀሙ ይገኛሉ።

ስብርባሪው 11 ኪሎ ሜትር ያህል ተበታትኖ ነው የወደቀው። ሁለት የባሕር ኃይል መርከቦች በቦታው ተሰማርተዋል።

“ለኛ ይሄ የቻይና ፊኛ ጠቃሚ መረጃ ይሰጠናል” ብለዋል የአሜሪካ ባለሥልጣናት።

ቻይና ይህ ፊኛ ለአየር ንብረት ጥናት ወደ ሰማይ ልኬው፣ ድንገት ከቁጥጥሬ ውጭ በሆነ መልኩ ወደ አሜሪካ ሰማይ ሄዶብኝ ነው ችግሩ የተፈጠረው ስትል አስተባብላ ነበር።

የዚህ ፊኛ ጉዳይ በዋሺንግተንና በቤጂንግ መካከል የዲፕሎማሲ ኩርፊያን ያስከተለ ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ወደ ቤጂንግ ዛሬ እሑድ ያደርጉት የነበረውን ጉዞ እንዲሰርዙም ምክንያት ሆኗል።

ይህ ፊኛ ተመ’ቶ እንዲወድቅ የመጨረሻ ውሳኔ ይጠበቅ የነበረው ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ነበር።

በመጨረሻም በተጠንቀቅ ላይ የነበረው ጄት ፊኛውን መት’ቶ እንዲጥል ውሳኔ ካስተላለፉ በኋላ ኦፕሬሽኑ ተጠናቋል።

ባይደን “ይህን ላሳኩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት አድናቆቴ የላቀ ነው” ብለዋል።

የታይዋን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በበኩሉ ከአሜሪካ ጎን በመቆም የቻይና መንግሥት የዓለም አቀፍ ሕጎችን ጥሷል ሲል ወቀሳ አቅርቧል።

ቻይና ታይዋንን የራሷ አንድ አካል አድርጋ ነው አሁንም የምትመለከታት።

የጊዜ ጉዳይ እንጂ ታይዋን የዋናዋ ቻይና አስተዳደር ውስጥ መካተቷ አይቀርም ይላሉ የቻይና ባለሥልጣናት።

ይህ የታይዋን ከአሜሪካ ጎን ቆማ ቻይናን ማውገዟ የቻይና ባለሥልጣናትን አላስደሰተም።

የዚህ ፊኛ ጉዳይ ይበልጥ አሳሳቢ ያደረገው ፊኛው አሜሪካ በርካታ ወታደራዊ መሠረተ ልማትና የጦር ቀጠና ባኖረችበት ሞንታና ግዛት ሰማይ ላይ ሲንሳፈፍ መታየቱ ነበር።

ባይደን ፊኛው ላይ እርምጃ እንዲወሰድ መመሪያ የሰጡት ረቡዕ ቢሆንም ፊኛው ይበልጥ ወደ ዉሃ አካል እንዲወድቅ ስለተፈለገ እስከ ትናንት እርምጃ ሳይወሰድበት ቆይቷል።

የአሜሪካ የአቪየሽን መሥሪያ ቤት በዚህ ፊኛ ላይ እርምጃ ሊወሰድ ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ ለሦስት ሰዓታት በሳውዝ ካሮላይና ግዛት ማንኛውም የመንገደኞች በረራ እንዲቆም አድርጓል።

እርምጃው ሲወሰድ ተመለከትኩ ያለ አንድ የዐይን እማኝ ለቢቢሲ ሲናገር፣ “በቅድሚያ ሦስት ጄቶች ፊኛው ላይ ከበባ ሲያደርጉ ከሩቅ ተመለከትኩ፤ ከዚያ ከባድ ፍንዳታ ሰማን፤ ቤታችንም ተነቃነቀ” ብሏል።