የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አሥመራ ገቡ

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኤርትራ፣ አሥመራ መግባታቸው ተገለጸ።

የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው፣ ፕሬዝዳንቱ ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት አሥመራ እንደገቡ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ "በሁለትዮሽ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙርያ" እንደሚወያዩ አክለዋል።

የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ድሕፈት ቤት እንዳለው ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ “በሁለቱ ወንድማማች አገራት” የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ለመምክር ነው ዛሬ ሰኞ ታኅሣሥ 29/2016 ዓ.ም. ወደ ኤርትራ የተጓዙት።

ድሕፈት ቤቱ ቪላ ሱማሊያ የፕሬዝዳንቱን ጉዞ አስመልክቶ በኤክስ ገጹ “በሁለቱ ወንድማማች አገራት የሁለትዮሽ ጉዳዮ ዙሪያ ከአቻቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈርቂ ጋር ይወያያሉ” ብሏል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት ያስችላታል የተባለውን የመግባቢያ ሠነድ መፈረሟን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ከተለያዩ መሪዎች ጋር የስልክ ውይይቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት በቀይ ባሕር ላይ ለወደብ እና ለጦር ሠፈር ልማት የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ የሚያስችላት ሲሆን በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንዲሁም እንደ አገር ከአዲስ አበባ እውቅና እንደምታገኝ ተዘግቧል።

ይህን ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ በቀጠናው ካሉ አገራት ጋር እንዲሁም ከአውሮፓ ኅብረት ኃላፊ ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ባለፉት ጥቂት ቀናት ከግብጽ፣ ኡጋንዳ፣ ቱርክ እና ኳታር እንዱሁም ከአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል ጋር በስልክ ተወያይተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከግብጹ አቻቸው ጋር በነበራቸው ንግግር አል-ሲሲ “ግብጽ ከሶማሊያ ጎን ለመቆም ያላትን ጠንካራ አቋም” መግለጻቸው ተመላክቷል።

ከኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቪኒ ጋር በነበራቸው ውይይት ደግሞ መሪዎቹ በሁለቱ አገራት የደኅንነት ትብብር ዙሪያ መነጋገራቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ከቱርኩ ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር ደግሞ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛትን አንድነት የቱርክ መንግሥት ለሚያደርገው የማይቋረጥ ድጋፍ ምስገና መስጠታቸውን ጽ/ቤቱ ገልጿል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ከኳታሩ ኢሚር ተሚም ቢን ሐማድ ጋር ደግሞ በሁለትዮሽ እና የጋራ ፍላጎቶች በሆኑ ቀጠናዊ ግንኙነቶች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።

ከአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ አመራር ከሆኑት ጆሴፍ ቦሬል ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ደግሞ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ኅብረቱ የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸው ተሰምቷል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የደረሱት ስምምነት ይፋ መሆኑን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት ባወጣው አጭር መግለጫ የሶማሊያን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር ጠቃሚ መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን ማለቱ ይታወሳል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ሰኞ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሠነድ የሶማሊያን መንግሥት አስቆጥቷል።

የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መንግሥት ስምምነቱንም “በሶማሊያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ ላይ የተቃጣ ጥቃት ” ብሎታል።

ትናንት ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት “ውድቅ የሚያደርግ” ያሉትን ሕግ ፈርመው አፅድቀዋል።

ፕሬዝደንቱ በኤክስ ገፃቸውን “. . . የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሶማሊላንድ የገቡትን የመግባቢያ ሰነድ ውድቅ የሚያደርግ ሕግ ፈርሚያለሁ” ካሉ በኋላ የፈረሙት ሕግ “አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን እንዲሁም የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ” ወሳኝ ነው ብለዋል።

ሶማሊላንድን እንደ አንድ ግዛቷ የምትቆጥረው ሶማሊያ ጠ/ሚ ዐቢይ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ የገቡትን ስምምነት በመቃወም አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ መጥራቷ ይታወሳል።

አሁን ላይ እየወጡ ያሉ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት በኋላ በመጀመሪያው የውጭ አገር ጉዟቸው በኤርትራ ለምን ያክል ጊዜ እንደሚቆዩ የተባለ ነገር የለም።