ቲክቶክ በካናዳ ባለሥልጣናት ምርመራ እየተደረገበት ነው

በዓለም ዙሪያ በርካታ ተጠቃሚዎችን እና ታዋቂነትን እያፈራ ያለው ቲክቶክ ከተጠቃሚዎቹ በሚሰበስበው ግላዊ መረጃ ዙሪያ የካናዳ ባለሥልጣናት ምርመራ ማድረግ ጀመሩ።

ባይትዳንስ በተባለው የቻይና ተቋም ባለቤትነት የሚተዳደረው የቪዲዮ ማጋሪያ የማኅበራዊ መድረክ ቲክቶክ፣ መረጃዎችን ለቻይና መንግሥት አሳልፎ ይሰጣል በሚል ይከሰሳል።

ካናዳ በቲክቶክ ላይ ምርመራ የጀመረችው፣ የአውሮፓ ኅበረት ኮሚሽን ሠራተኞቹ የቲክቶክ መተግበሪያን ከመገልገያቸው ላይ እንዲያስወግዱ ካዘዘ በኋላ ነው።

ቲክቶክ ግን የተጠቃሚዎቹ ግላዊ መረጃን የመጠበቅ ጉዳይ “ከሁሉ የሚቀድም ኃላፊነቴ ነው” ብሏል።

የካናዳ የግላዊ መረጃ ጥበቃ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት በቲክቶክ ላይ ምርመራ ማድረግ የጀመረው በአገሪቱ ካሉ የግዛቶች ተመሳሳይ ተቋማት ጋር በመተባበር ነው።

ይህ ምርመራ የተጀመረው የቲክቶክን መረጃ አሰባሰብ እና አጠቃቀምን በተመለከተ በአሜሪካ እና በካናዳ ክስ ከቀረበ እና የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን ማውጣታቸውን ተከትሎ መሆኑ ተገልጿል።

ምርመራው ቲክቶክ “የካናዳን የግል መረጃ ጥበቃ ሕግን የተከተለ እንደሆነ” መለየት ዋነኛ ዓላማው ያደረገ ሲሆን፣ ድርጅቱ የሚጠበቅበትን ግልጽነት ምን ያህል ተግባራዊ እንደሚያደርግም ይጠራል።

ምርመራውን የጀመረው የካናዳ ተቋም እንዳለው ቲክቶክን የሚጠቀሙት አብዛኞቹ ወጣቶች በመሆናቸው “የልጆችን ግላዊ መረጃን መጠበቅ” እጅግ አስፈላጊ ነው ብሏል።

የቲክቲክ ቃል አቀባይ እንዳሉት የሚደረገው ምርመራ ድርጅቱ ምን ያህል ለካናዳውያን ተጠቃሚዎቹ የግል መረጃ ጥበቃ እንደሚያደረግ “የሚያረጋግጥ” አጋጣሚ ነው ብሏል።

ካናዳ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ያሉ በርካታ አገራት ቲክቶክ የተጠቃሚዎቹን መረጃ በመሰብሰብ ለቻይና አሳልፎ ይሰጣል ወይም ለተለየ ጥቅም ያውለዋል በሚል ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

ቲክቶክ ከዚህ ቀደም በሰጠው ምላሽ በመተግበሪያው ላይ የሚገኙ መረጃዎች በቻይና መንግሥት እንደማይታዩ ማስተባበያ ሰጥቶ ነበር።

በቅርቡ የኔዘርላንድስ መንግሥት ባለሥልጣናቱ ቲክቶክን እንዳይጠቀሙ የመከረ ሲሆን፣ በአሜሪካም የፌደራል መንግሥቱ ሠራተኞች ላይ መተግበሪያውን እንዳይጠቀሙ እገዳ ተጥሏል።

የአውሮፓ ኅበረት ኮሚሽን፣ የአውሮፓ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ እና የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት እንዲሁም ሠራተኞቻቸው የቲክቶክ መተግበሪያን እንዲያስወግዱ ታዘዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወሰድ ባለሥልጣናት ግፊት እያደረጉ ነው።