ጃፓን በታሪኳ የመጀመሪያዋን ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሾመች

ሳናኤ ታካኢቺ ከጃፓን ሁለት ምክር ቤቶች የብዙሃን ድምጽን በማግኘት የመጀመሪያዋ የአገሪቱ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ታሪክ ሠሩ።

የጃፓን ሊብራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል የሆኑት ታካኢቺ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣኑን የጨበጡት በአገሪቱ የታችኛ ምክር ቤት 237 ድምጽ እንዲሁም ከላኛው ምክር ቤት የ125 ድምጽ ድጋፍ በማግኘት ነው።

አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር በጃፓን ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን፣ "የጃፓን ብረቷ እመቤት" የሚል ቅጽልንም አትርፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ በሰው እጅ የተገደሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ተከታይ ከመሆናቸው በተጨማሪ በጠንካራ ወግ አጥባቂ አቋማቸው ይታወቃሉ።

እስካሁን ባላው የጃፓን የመሪነት መንበር ላይ ወንዶች ሰፊ የበላይነት ይዘው የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ሳናኤ ታካኢቺ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መምጣታቸው ታላቅ እመርታ መሆኑ እየተነገረ ነው።

በርካቶች እንደሚሉትም ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሯ ሹመት በጃፓን ፖለቲካ ውስጥ ቀስ በቀስ እየተቀየረ ላላው የሴቶች ተሳትፎ ውክልና ታሪካዊ እርምጃ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካኢቺ መረጋጋት በሌለው የጃፓን ፖለቲካ በአምስት ዓመት ውስጥ ወደ ሥልጣን የመጡ አራተኛዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።

የታካኢቺ ድል የመጣው ፓርቲያቸው ሊብራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲካዊ ቅሌት በገጠመው እና የሕዝብ ተቀባይነቱ ዝቅ ባለበት ጊዜ ነው።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያለውን አብዛኛውን ጊዜ ጃፓንን የመራው ፓርቲው ሴት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማስሾም ከቀኝ ክንፉ የጃፓን ኢኖቬቲቭ ፓርቲ ጋር ጥምረት ለመመሥረት ከተስማማ በኋላ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ የተቀዛቀዘውን የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለማነቃቃት መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ማዋዕለ ነዋይ እንዲያፈስ የሚያደርግ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ታካኢቺ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ለመያዝ በቂ ድምጽ ቢያገኙም፣ በተገቢው ሁኔታ አገሪቱን ለመምራት ግን የተቃዋሚ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ድጋፍ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው እየተነገረ ነው።

ከሁለቱ የጃፓን ምክር ቤቶች ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የሚያስችላቸውን ድጋፍ ያገኙት ሳናኤ ታካኢቺ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ 64ኛ እና የመጀመሪያዋ ሴት የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ።

የአገሪቱ ፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትሯን ከመረጠ በኋላ ታካኢቺ የሚጠበቅባቸው ተግባራት ሚኒስትሮችን በመሾም አዲሱን ካቢኔያቸውን ይመሠርታሉ።

ከዚያም ጃፓንን በንጉሣዊ ሥርዓት ወደ ሚመሩት ንጉሥ ቤተ መንግሥት ከካቢኔዎቻቸው ጋር በማቅናት ተማኝነታቸውን ከገለጹ በኋላ የመጀመሪያውን የሚኒስትሮች ስብሰባ ያካሂዳሉ።