በናይጄሪያ የመካነ አራዊት ጠባቂ በሚመግበው አንበሳ በደረሰበት ጥቃት ሞተ

በደቡብ-ምዕራብ ናይጄሪያ አንድ የእንስሳት ጠባቂ አንበሳ ለመመገብ በሄደበት ወቅት ፍርግርጉን መቆለፍ ባለመቻሉ ምክንያት በአንበሳ ጥቃት ደርሶበት ህይወቱ ማለፉን ፖሊስ ገለጸ።

የ35 ዓመቱ ናይጄሪያዊ በቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ባለቤትነት በሚተዳደረው እና በኦጉን ግዛት ዋና ከተማ በሚገኘው ፕሬዚዳንሽያል ላይብረሪ ዋይልድ ላይፍ ፓርክ ውስጥ ይሠራ ነበር።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ኦሞሎላ ኦዱቶላ በሰጡት መግለጫ “አንበሳው በሰውየው አንገት ላይ ለሞት የሚያደርስ ከባድ ጉዳት አድርሶበታል” ብለዋል።

አክለው አንበሳው “ግለሰቡን እንዲለቅ ለማድረግ” ተተኩሶበታል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ፕሬዚዳንሽያል ላይብረሪ ዋይልድ ላይፍ ፓርክ መግለጫ ከሆነ፣ የአንበሳውን የአመጋገብ ስርዓት ለማሳየት ጠባቂው ከተወሰኑ እንግዶችን ጋር ነበር።

“የእንስሳት ጠባቂው ከአንበሳው ጋር የመላመድ ስሜት ስለነበረው የደህንነት ጥበቃውን በር (ፍርግርጉን) ከፍቶ አንበሳውን መመገቡን ቀጠለ። ነገር ግን አንበሳው ባደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል” ይላል መግለጫው።

"ሰውየው አካል ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል እንበሳው በፓርኩ ሠራተኞች ወዲያውኑ እንዲመታ ተደርጓል" በማለት ሁኔታውን ያስረዳል።

ተጎጂው ባባጂ ዳውሌ የሚባል ሲሆን የሰለጠነ አንበሳ ተቆጣጣሪ ነበር ሲል ፖሊስ ገልጾታል።

ከጥቂት ወራት በፊት በደቡብ-ምዕራብ ናይጄሪያ በሚገኘው ኦባፌሚ አዎሎዎ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ መንገድ ሌላ የእንስሳት ጠባቂ በአንበሳ ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል።

ክስተቶቹ በአገሪቱ የመካነ አራዊት እና የዱር እንስሳት አያያዝ ሕጎች ላይ ጥያቄዎች እንዲነሱ ምክንያት ሆኗል።