100 ዓመት ገደማ የሆናቸው ኤሊዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወላጆች ሊሆኑ ነው

በአሜሪካ 100 ዓመት ገደማ የሆናቸው ኤሊዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወላጆች ሊሆኑ ነው።

በፊላደልፊያ መካነ አራዊት የሚኖሩት እነዚህ ኤሊዎች ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረበ እና በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥራቸው የተመናነመነ ነው።

አብራዞ እና ማሚ የተሰኙት ኤሊዎች ከጣሏቸው ውስጥ አራት ዕንቁላሎች ተፈልፍለው ጫጩቶች መሆናቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንዳስደሰተው ነው መካነ አራዊቱ የገለጸው።

የጫጩቶቹ መገኘት በመካነ አራዊቱ ከ150 ዓመት በላይ ዓመታት ታሪክ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

በአውሮፓውያኑ 1932 ወደ መካነ አራዊቱ የመጣችው ማሚ የሚል ስያሜ የተሰጣት ሴቷ ኤሊ በእሷ ዝርያ በዚህ ዕድሜ እናት የሆነች የመጀመሪያዋ ናት።

ከምዕራብ ሳንታ ክሩዝ ጋላፓጎዝ ደሴት የተገኙት እነዚህ ኤሊዎች በዱር አካባቢ ያላቸው ዝርያ በከፋ ሁኔታ ተመናምኗል። በአሜሪካ መካነ አራዊት ያሉት ደግሞ ከ50 ያነሱ ናቸው።

የሁለቱ ኤሊዎች የመጀመሪያ እንቁላሎች የተፈለፈሉት ከአንድ ወር በፊት ሲሆን ሌሎቹም ወዲያውኑ ተከትለዋል ተብሏል።

የመካነ አራዊቱ የእንክብካቤ ቡድን በሚቀጥሉት ሳምንታትም ሊፈለፈሉ የሚችሉ እንቁላሎችን እየተከታተለ ነው። አራቱ ጫጩቶች ከ70-80 ግራሞች ይመዝናሉ።

ጫጩቶቹ በፊላደልፊያ መካነ አራዊት ውስጥ ተሳቢዎች ባሉበት ከሰው ዕይታ ራቅ ተደርገው የተቀመጡ ሲሆን በአግባቡ እየተመገቡ እና እያደጉ እንደሆነም ተቋሙ አስታውቋል።

ጫጩቶቹ ለሕዝብ ዕይታ የሚቀርቡት ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሲሆን ይህም ሴቷ ኤሊ ወደ መካነ አራዊቱ የመጣችበት 93ኛ ዓመት ለማሰብ ነው።

እንቁላሎቹ የተፈለፈሉት ዝርያዎችን እና የዘረ መል ልዩነቶችን ለመጠበቅ እና ለመታደግ ያለመ የመካነ አራዊቶች የመራቢያ ፕሮግራም አካልነት ነው።

"ይህ በፊላደልፊያ የእንስሳት መካነ አራዊት ታሪክ ትልቅ ምዕራፍ ነው፤ ይህንም ዜና ለከተማችን፣ ለአገራችን እና ለዓለም ስናካፍል በደስታ ነው" ሲሉ የተቋሙ ፕሬዚዳንት እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ኦ ኤሌ ሞገርማን ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

"ማሚ [ሴቷ ኤሊ] በአውሮፓውያኑ 1932 ነው ወደ መካነ አራዊቱ የመጣችው። እናም በባለፉት 92 ዓመታት መካነ አራዊቱን የጎበኘ ሰው በሙሉ አይቷታል" ሲሉ ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።

ወንዱ ኤሊ አብራዞ ወደ ፊላደልፊያ መካነ አራዊት ተዛውሮ የመጣው ከአምስት ዓመታት በፊት ነው።

ከዚህ ቀደም ሪቨር ባንክስ እና ጋርደን በተሰኙ መካነ አራዊቶች በደቡብ ካሮላይና ይኖር ነበር።.