ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰሜን ኮሪያ ከስድስት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር አካሄደች
ሰሜን ኮሪያ ከስድስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የፒዮንግያንግ ኢንተርናሽናል ማራቶን አካሄደች።
በዚህ ውድድር ላይ ከ200 የተለያዩ አገራት የመጡ ሯጮች እንዲሳተፉ ማድረጓ ተገልጿል።
እአአ በ1981 የተጀመረው ይህ የማራቶን ውድድር በየዓመቱ በሚያዝያ ወር የአገሪቱን መስራች የሆኑትን ኪም ኢል ሱንግ ልደት ለማክበር ይካሄዳል።
ከእሁዱ የማራቶን ውድድር በፊት ውድድሩ ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደው እአአ በ2019 ሲሆን 950 የውጭ አገር ዜጎች ተሳትፈውበት ነበር።
በቀጣዩ ዓመት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ሰሜን ኮርያ ራሷን ከቀሪው ዓለም ነጥላ ቆይታለች።
ሰሜን ኮሪያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ዋና ከተማዋ የሩስያ ቱሪስቶች ብቻ እንዲገቡ ፈቅዳለች።
ሯጮች፣ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት እንደነበረው በተደራጀ የጎብኝዎች ቡድን ውስጥ ተካትተው ወደ አገር ውስጥ መግባት ተፈቅዶላቸዋል።
የውድድሩ አዘጋጆች በድረ-ገጻቸው ላይ "አጋር" ሲሉ የጠቀሱት መቀመጫው ቤጂንግ ያደረገው ኮርዮ ቱርስ የጉዞ ኤጀንሲ ለስድስት ቀናት የማራቶን ጉብኝቶች እና ቤጂንግ ደርሶ መልስ ትኬት 2,406 ዶላር ያስከፍላል።
ኤጀንሲው በድረ-ገጹ ላይ "የፒዮንግያንግ ማራቶን ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ለመገናኘት እድል የሚሰጥ በመሆኑ እጅግ በጣም ልዩ የሆነ ተሞክሮ ነው" ሲል ጽፏል።
በትናንቱ የማራቶን ውድድር ላይ የተሳተፉ ሯጮች በከተማው ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች ማለፍ ይጠበቅባቸው ነበር።
እነዚህም የኪም ኢል ሱንግ ስታዲየም፣ ኪም ኢል ሱንግ የጃፓንን አገዛዝ በመቃወም የተጫወቱትን ሚና ለማስታወስ የተሰራውን የድል ሀውልት እና የሳይንቲስቶች እና መሐንዲሶች መኖሪያ የሚገኝበት አውራ ጎዳና ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል።
በኦንላይን የተለቀቁ ምስሎች ሯጮች ውድድሩን በሚጀምሩበት እና በሚጨርሱበት ስታዲየም የተሰበሰቡ በርካታ ተመልካቾች ባንዲራ እያውለበለቡ ያሳያሉ።
የሰሜን ኮሪያው ሯጭ ፓክ ኩም ዶንግ ለሮይተርስ የዜና ወኪል "ዜጎች በእኔ ላይ ዓይናቸውን መጣላቸው ድካም በተሰማኝ ጊዜ ሁሉ እንድቋቋም ረድቶኛል" ብሏል።
ስለ ሩጫ ውጤቶች በይፋ የተቀመጠ ምንም ዓይነት መረጃ የለም።
ሰሜን ኮሪያ በ 2023 አጋማሽ ላይ የኮቪድ-19 ገደቦችን ማላላት ጀምራለች።
በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ አንዳንድ ምዕራባውያን ጎብኚዎች ከዋና ከተማዋ ርቀው የሚገኙ ከተሞችን አንዲጎበኙ ብትፈቅድም ከሳምንታት በኋላ ታግደዋል።