እጣ ፈንታቸው በዓለም አቀፍ መድረክ እያከራከረ የሚገኘው የጋዛ ነዋሪዎች የገጠማቸው አጣብቂኝ

ጃባሊያ፣ ከአየር ላይ ስትታይ ልብ ቀጥ ታደርጋለች።

እንደ ሂሮሺማ ያለ ጠፍ መሬት ለዓይን እስከሚያታክት ድረስ ዘልቆ ይታያል። የፈራረሱ የሕንጻ ቅሪቶች ይታያሉ፤ አንዳንዶቹ ዘምመዋል።

አባጣ ጎባጣ የበዛበት የፍርስራሽ ክምር በአንድ ወቅት ግርግር የማይለየው እና በእንቅስቃሴ የተሞላ የነበረውን የስደተኞች ካምፕ ለመለየት አዳጋች ያደርገዋል።

ሆኖም ግን፣ ሰው አልባ ካሜራ ከፍርስራሹ በላይ ሲያንዣብብ፣ ክፍት መሬት ላይ ከተተከሉ ሰማያዊ እና ነጭ ትናንሽ የድንኳን ካምፖች የሚፈነጥቁ ነጸብራቆች እይታ ውስጥ ይገባሉ።

በተጨማሪም በፈራረሱ ሕንጻዎች ላይ ለመንጠላጠል የሚደረግ ትግል፣ በቆርቆሮ ጣሪያ እና በሸራ መሸፈኛ ስር ያሉ የምግብ ገበያዎች፣ በቆሸሹ ጎዳናዎች ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎችም እይታ ውስጥ ይገባሉ።

እየተንገዳገደ ከስድስት ሳምንታት በላይ ከቆየው የጋዛ የተኩስ አቁም በኋላ ጃባሊያ ቀስ በቀስ ወደ ሕይወት እየተመለሰች ነው።

ነቢል፣ በአልቃሲብ ሰፈር መስኮት፣ በሮች እና በአንዳንድ ቦታዎች ግድግዳዎች ወደሌሉት ባለ አራት ፎቅ ቤት ተመልሷል።

ከፍ ካለው ወለል ጃባሊያን የሞላትን የፍርስራሽ ውቅያኖስ በዓይኑ እየቃኘ "ይህን ውድመት ተመልከቱ" ይላል።

"እነሱ እንደገና ሳንገነባው እንድንሄድ ይፈልጋሉ? እንዴት ልንሄድ እንችላለን? እኛ ማድረግ የምንችለው ትንሹ ነገር ለልጆቻችን መልሰን መገንባት ነው።"

ነቢል ምግብ ለማብሰል በሰው አልባው ደረጃው ላይ፣ በተቀደደ ካርቶን በጥንቃቄ እያራገበ እሳት አቀጣጠለ።

በሌላኛው ወለል ላይ ላኢላ አህመድ ኦካሻ በገንዳ ውስጥ ታጣጥባለች።

"ውሃ፣ መብራት ወይም ፍሳሽ ማስወገጃ የለም" ትላለች። "ውሃ ከፈለግን ሩቅ ቦታ መሄድ ይኖርብናል"

ወደ ቤቷ ስትመለስ እና ወድሞ ስታገኘው እንዳለቀሰች ትናገራለች።

ቀድሞ የምታውቀውን መንደር ስላጠፉባት እስራኤል እና ሃማስን ትወቅሳለች።

"ሁለቱም ተጠያቂ ናቸው፤ ጥሩ እና ምቹ ሕይወት ነበረን" ትላለች።

ጦርነቱ እ.አ.አ በጥቅምት 2023 ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ፣ እስራኤል ጃባሊያን ጨምሮ በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል ላሉ ፍልስጤማውያን ለደህንነታቸው ወደ ደቡብ እንዲሄዱ ጥሪ አስተላልፋ ነበር።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያውን ሰምተው ነበር፤ ነገር ግን ብዙዎች ጦርነቱን እናልፋለን በሚል ተስፋ ቀሩ።

ላይላ እና ባለቤቷ ማርዋን የእስራኤል ጦር ሃማስ በካምፑ ጠባብ ጎዳናዎች ውስጥ የተዋጊ ክፍሎችን እንደ አዲስ አቋቁሟል በሚል ምክንያት ጃባሊያን በድጋሚ እስከወረረበት ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ድረስ ቆይተው ነበር።

ሊላ እና ማርዋን በአቅራቢያው በሚገኘው የሻቲ ካምፕ ውስጥ ለሁለት ወራት ከተጠለሉ በኋላ ሲመለሱ ወትሮ የሚያውቋትን ጃባሊያን አላገኟትም፤ ፈራርሳለች።

"ተመልሰን ስንመጣና እንዴት እንደወደመች ስመለከት ከአሁን በኋላ እዚህ መቆየት አልፈለግኩም" ይላል ማርዋን።

"ጥሩ ሕይወት ነበረኝ፤ አሁን ግን ሲዖል ሆኗል። የመውጣት እድል ካገኘሁ እሄዳለሁ። ለአፍታም አልቆይም።"

ይቆዩ ወይም ይሂዱ? የጋዛ ንጹኃን የወደፊት እጣ ፈንታ አሁን የዓለም አቀፍ ሙግት ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።

በየካቲት ወር ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ ጋዛን እንድትቆጣጠር እና ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የፍልስጤም ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ ሐሳብ አቅርበው ነበር።

ዓለም አቀፍ ቁጣ እና የአረብ መሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥማቸው ትራምፕ ምክረ ሃሳብ አቀረቡ እንጂ ማንንም እንደማያስገድዱ በመግለጽ ከዕቅዳቸው አፈግፍገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብፅ ማክሰኞ በካይሮ በሚካሄደው የአረብ አገራት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ የሚቀርብ አዋጭ የሆነ አማራጭ ሃሳብ እንዲቀርብ የአረብ አገራትን ጥረት እየመራች ነው።

አካባቢው እንደገና በሚገነባበት ጊዜ የፍልስጤም ሕዝብ በጋዛ መቆየት አለበት ስትል ግብጽ በአንጽንኦት ተናግራለች።

የዶናልድ ትራምፕ ጣልቃ ገብነት በጋዛን ጉዳይ የማይናወጥ አቋም ያላቸውን አውጥቷል።

"ትራምፕ እንድንሄድ ከፈለገ በጋዛ ውስጥ እቆያለሁ" ትላለች ላይላ። "በራሴ ፈቃድ መጓዝ እፈልጋለሁ፤ በእሱ ምክንያት አልሄድም።"

ከመንገዱ ማዶ ባለ ዘጠኝ ፎቅ ቢጫ ሕንጻ ይታያል። በጣም ክፉኛ ተጎድቷል፤ አለመውደቁን ለማመን ይከብዳል።

ቀሪውን ክፍል ስጋት ላይ በጣለ መልኩ የላይኛው ወለል ሙሉ በሙሉ ፈርሷል።

ከጊዜ በኋላ፣ በእርግጥ መፍረስ አለበት፤ አሁን ግን የብዙ ቤተሰቦች መኖሪያ ነው።

በመስኮቶቹ ላይ በበጋው ፀሐይ እንዲደርቅ የታጠበ ልብስ ተሰጥተዋል።

ከአካባቢው ጋር በማይጣጣም መልኩ በምድር ወለል ጥግ ላይ ካለው ጊዜያዊ የፕላስቲክ በር ውጭ፣ ከቆሻሻ ክምር አጠገብ፣ የሙሽራ ልብስ የለበሰ ጭንቅላት አልባ አሻንጉሊት ቆሟል።

የሳናዕ አቡ ኢሽባቅ የሙሽራ ልብስ መሸጫ ሱቅ ነው።

የ11 ልጆች እናት የሆነችው የ45 ዓመቷ የልብስ ስፌት ባለሙያ፣ ከጦርነቱ ሁለት ዓመታት አስቀድሞ የጀመረችውን ንግድ በሕዳር 2023 ወደ ደቡብ ስትሸሽ መተው ነበረባት።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንደታወጀ ተመልሳ መጣች። ከባለቤቷ እና ከሴት ልጆቿ ጋር፣ ከሱቅ ፍርስራሾችን በማጽዳት፣ በተንጠለጠሉ መሰቀያዎች ላይ ቀሚሶችን በማዘጋጀት እና ለንግድ ሥራ በማዘጋጀት ባተሌ ሆና ቆይታለች።

"የጃባሊያ ካምፕን እወደዋለሁ እና እስክሞት ድረስ ከዚህ አልሄድም" ትላለች።

ሳናዕ እና ላኢላ ከቻሉ ለመቆየት የወሰኑ ይመስላሉ። ነገር ግን ሁለቱም ስለ ወጣቶቹ ሲናገሩ በተለያየ መንገድ ነው።

ላኢላ የልጅ ልጇ "የራሷን ስም እንዴት እንደምትጽፍ እንኳን አታውቅም" ትላለች።

"በጋዛ ውስጥ ምንም ትምህርት የለም።"

በጦርነቱ ወቅት የልጅቷ እናት ተገድላለች። ላኢላ አሁንም በምሽት እንደምታዋራት ትናገራለች።

"እሷ የነፍሴ እስትንፋስ ነበረች እና ልጇን በእቅፌ ውስጥ ትታት ሄዳለች። የመጓዝ እድል ካገኘሁ፤ ለልጅ ልጄ ስል አደርገዋለሁ"