በባሕር ዳር ከተማ “በከባድ መሳሪያ” የታገዘ ውጊያ እንደነበረ ነዋሪዎች ተናገሩ

በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በከተማዋ ሦስት ቀበሌዎች ዛሬ አርብ የካቲት 22/2016 ዓ.ም. ማለዳ 12፡00 ሰዓት ላይ ውጊያው መጀመሩን የተናገሩት አራት ነዋሪዎች፤ የከባድ መሳሪያ ድምጾችንም መስማታቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ በባሕር ዳር ዙሪያ የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የፀጥታ ኃይል በጋራ በመሆን ሰርጎ ገብቷል ያለውን “ጽንፈኛ ቡድን በየቤቱ የማሰስ እና የማጽዳት ሥራ እየሠራ ይገኛል” ይገኛል ብሏል።

ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ቢቢሲ ያናገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በቀበሌ 14 አቡነ ሃራ እና ልደታ በሚባሉ የመኖሪያ ሰፈሮች፤ እንዲሁም ቀበሌ 11 አባይ ማዶ እየተባለ በሚጠራ ሰፈር እና ቀበሌ 13 በዓታ ቤተ ክርስቲያን ወይም ወራሚት አካባቢ ውጊያ መደረጉን ተናግረዋል።

አንድ የከተማዋ ነዋሪ “...ከጠዋቱ 12፡20 ጀምሮ ውጊያ ነበር። ቅርብ ለቅርብ የሚመስል የክላሽ ድምጽ ነበር። ይህም እስከ 1፡40 አካባቢ ድረስ የቀጠለ ነበር። በማስከተል ድግሞ የከባድ መሳሪያ፤ ትልልቅ መሳሪያዎች ድምጽ ይሰሙ ነበር” ብለዋል።

አባይ ማዶ በተባለው አካባቢ ከሦስት ቀናት በፊት ጀምሮ የተኩስ ልውውጦች እንደነበሩ የተናገሩት ሌላ ነዋሪ፤ አየር ጤና በተባለው ሰፈር “ሌሊቱን ሙሉ” በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እንደነበር ተናግረዋል።

በመኖሪያ ሰፈሮች አካባቢ ተደርጓል የተባለው የዛሬው ውጊያ ለአንድ ሰዓት ያህል ተጋግሎ መደረጉንና ረፋድ 3፡00 ሰዓት አካባቢ ጋብ ማለቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል። ከዚያም በኋላ ረፋድ ላይ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጾች ይሰሙ ነበር ብለዋል።

ትናንት ሐሙስ የካቲት 21/2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ “ውጊያ ሊኖር ይችላል ተጠንቀቁ” የሚል መረጃ እንደሰሙ የተናገሩት አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ጥዋት 12፡00 ሰዓት አካባቢ የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን ተናግረዋል።

ግለሰቡ የተኩስ ልውውጡ በተደረገበት አንደኛው ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ይሰማ የነበረው “የተኩስ ልውውጥም በከባድ መሳሪያ የታገዘ ነበር” ብለዋል።

ውጊያ የመኖሪያ ሰፈሮች አካባቢ ላይ ቢደረግም እስካሁን ሰላማዊ ሠዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ለማወቅ እንዳልቻሉ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ከባድ የተኩስ ልውውጥ ከተሰማ በኋላ በከተማዋ “ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም” ብለዋል።

“ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆች ነበሩ። ምግባቸውን አዘጋጅተን ነበር [ትምህርት ቤት] ለመላክ። ነገር ግን 12፡00 ሰዓት አካባቢ ተኩሱ ሲጀመር . . . አስቀረናቸው። እኛም ሥራ አልሄድንም” ሲሉ በከተማዋን አርብ ጠዋት ላይ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል።

የፋኖ ታጣቂዎች ሳይሆኑ አይቀሩም ያሏቸው “ታጣቂዎች” በሰፈራቸው በኩል ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን መመልከታቸውንም ጠቅሰው ውጊያው የረገበው “ለዚህ ይመስላል” ብለዋል።

“ከተማዋ ጸጥ ረጭ ብላለች” ያሉት ሌላ ነዋሪ፤ ከቤታቸው መውጣት ስላልቻሉ “ምን እንደተፈጠረ ማወቅ አልቻልንም” ሲሉ እንቅስቃሴ እንደሌለ ተናግረዋል።

“ምንም አይነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የለም። ሱቆች እና ሆቴሎች ሁሉም ተዘግተዋል። ሰው በመኖሪያ ሰፈሩ አካባቢ በር ላይ ብቻ ነው ቆሞ የሚታየው” ብለዋል።

የልጆች አባት እንደሆኑ የተናገሩ አንድ ነዋሪ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረው፤ “የንጹሃን እልቂት” ይደርሳል የሚል ፍርሃት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር እና ከባሕር ዳር አዲስ አበባ ተይዘው የነበሩ በረራዎችን ለመሰረዝ መገደዱን ቢቢሲ አረጋግጧል።

ለዛሬ አርብ የተያዙ ስድስት የሚደርሱ በረራዎች መሰረዛቸው የታወቀ ሲሆን፤ በረራው መቼ ሊጀመር እንደሚችል “ማወቅ አይቻልም” ተብሏል።

ዛሬ ረፋድ ላይ መግለጫ ያወጣው የአማራ ክልል መንግሥት በባሕር ዳሩ ዙሪያ “ሰርጎ ገቦችን” መዋጋቱን ገልጾ፤ በውጊያ የበላይነትን መቀናጀቱን ጠቁሟል።

በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ የባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢው “ጽንፈኛ” ሲል ከጠራው ቡድን እንደጸዳ እና በተጨማሪም የፋኖ አባላትን እያሰሰ መሆኑንም አስታውቋል።

የክልሉ መስተዳደር በመግለጫው “ሕግ ማስከበር” ላለው እርምጃ ሕዝቡ ከጎኑ በመቆም “ለሰላም ዘብ ሊሆን ይገባል” በማለት ጥሪ አቅርቧል።

በባሕር ዳር ከተማ በመንግሥት እና በፋኖ ኃይሎች መካከል ውጊያ ሲደረግ የዛሬው የመጀመሪያ አይደለም። ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ጊዜ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ በርካታ የክልሉ ከተሞች ገብተው የነበረ ሲሆን፣ በባሕር ዳር እና በዙሪያዋ ውጊያዎች መካሄዳቸው ይታወሳል።

በወቅቱም የመንግሥት ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች ከሕግ ውጪ ሰላማዊ ሠዎችን መግደላቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በምርመራው ማረጋገጡን ከሰሞኑን ይፋ አድርጓል።

ይህኑ ግድያ በማስታወስ አንድ የከተማዋ ነዋሪ “ባለፈውም እንደሆነው ንጹሃን ያልቃሉ ብለን እንሰጋለን፤ የሚያሳስበን ነገር እሱ ነው” ሲል ተናግረዋል።

“...[የመንግሥት ኃይሎች] ‘እናንተ የፋኖ መደበቂያ ናችሁ፤ እናንተ ናችሁ እንደዚህ እንዲሆን የምታደርጉት’ ስለሚሉ ሠው ይፈራል። ለዚህ ይመስለኛል ሁሉም ነገር ጸጥ ያለው” በማለት ከዚህ ቀደም እንደሆነው ግድያ ይፈጸማል የሚል ስጋት እንዳለ ጠቁመዋል።

ሌላ ነዋሪም “የመንግሥት ኃይሎች “ፋኖን ትደግፋላችሁ” በሚል ሌላ አካባቢ እርምጃ ስለወሰዱ እኛ ላይም ይከሰታል የሚል ስጋት ሕዝቡ ላይ አለ” ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

ካለፈው ሳምንት መገባደጃ ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ማገርሸቱ ታውቋል።

በተለይም በጎጃም እና በሸዋ አካባቢዎች “ከባድ ውጊያዎች” እተደረጉ መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ከደብረ ብርሃን ወደ ደሴ የሚወስደው መንገድ ከቅዳሜ፣ የካቲት 16/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት መወሰኑን ማስታወቁ ይታወሳል።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ በኋላ የክልሉን ልዩ ኃይል ለመበተን እና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።

የክልሉ መስተዳደርም ሁኔታው ከአቅሙ በላይ መሆኑን በመግለጽ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ በመጠየቁ በክልሉ እና እንዳስፈላጊነቱ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሎ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ወደ ክልሉ ተሰማርቶ ይገኛል።

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በተካሄዱ ወታደራዊ ግጭቶች በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ መደበኛ እንቅስቃሴዎች የተስተጓጎሉ መሆናቸውነ ነዋሪዎች ሲናገሩ ቆይተዋል።

በተጨማሪም በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ኃይሎች መካከል በሚካሄዱ ውጊያዎች እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውነ እና የንብረት ውድመት ማጋጠሙ እየተዘገበ ነው።