ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምዕራባውያን ዩክሬንን ለማስታጠቅ ቢሊዮኖች ያወጡባቸው መሳሪያዎች የትኞቹ ናቸው?
ዩክሬን የሩሲያን ጦር ለመከላከል እንድትችል ምዕራባውያን ተጨማሪ የጦር መሳሪያ እንዲያቀርቡላት ጥያቄዋን በተጠናከረ ሁኔታ ዳግም ማሰማት ጀምራለች።
ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ባለፈው ሳምንት በነበረው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ስብሰባ ላይ፤ “የሩሲያ የከባድ ጦር መሳሪያ ብልጫን መስበር አለብን። በርካታ ዘመናዊ መሳሪያዎች ያስፈልጉናል” ብለዋል።
ዜሌንስኪ አገራቸው ዩክሬን የጠየቀችውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ማግኘት የማትችል ከሆነ፤ ወደፊት ምዕራባውያኑ የሞስኮን ጦር ፊት ለፊት መግጠማቸው የማይቀር ነው ሲሉ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል።
እስካሁን ከ30 ያላነሱ አገራት የተለያዩ ጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ዩክሬን የምትሻውን አይነት ከባድ ጦር መሳሪያዎችን በቀላሉ ማግኘት አልተቻላትም። በጦርነቱ ግንባሮች ላይም ዩክሬናውያን የከፍተኛ ጦር መሳሪያ ብልጫ ተወስዶባቸዋል።
ለዩክሬን ብዙ መሳሪያ የሚያቀርቡት እነማን ናቸው?
አሜሪካ ለዩክሬን ሠራዊት የጦር መሳሪያዎችን በማቅረብ ከየትኛው አገር በላይ ከፍ ያለ ወጪ እያደረገች ነው።
ዋይት ሐውስ እንደሚለው፤ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሥልጣን ከያዙ በኋላ ዋሽንግተን የኪዬቭን ደኅንነት ለማጠናከር 6.3 ቢሊዮን ዶላር ሰጥታለች።
ከአሜሪካ በመቀጠል ደግሞ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፖላንድ በቢሊዮን የሚያስወጡ በርካታ የጦር መሳሪያ ድጋፍን አቅርበዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም በበኩሏ ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ እስካሁን 1.6 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ለዩክሬን የሰጠች ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ተጨማሪ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ማቀዷን አስታውቃለች።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ግን ይህ በቂ አይደለም ይላሉ። ፕሬዝደንቱ የጦራቸው ወርሃዊ ወጪ 5 ቢሊዮን ዶላር መሆኑንም ይገልጻሉ።
ዩክሬን ያስፈልጉኛል የምትላቸው መሳሪያዎች
የውትድርና ሳይንስ አዋቂዎች በጦር ግንባሮች ላይ ድልን መቀዳጀት ከሚያስችሉ ጉዳዮች መካከል ከፍተኛ መጠን ያላቸው የተለያየ የጦር መሳሪያዎችን መታጠቅ አንዱ ነው ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ በቂ ወታደራዊ ሥልጠና ያገኘ ሠራዊት፣ መለዋወጫዎች እና ሌሎች ድጋፎች የጠላት ኃይልን ድል ለማድረግ ቁልፍ ናቸው።
“የትኛውም አይነት የጦር መሳሪያ ተዓምራዊ ውጤት ላያመጣ ይችላል” ይላሉ የአሜሪካ ጦር ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ማርክ ሚሊይ።
እስካሁን እንደታየው የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ሥርዓትን የያዙ ስብስቦች ግን በጦር ግንባር ላይ ልዩነት ፈጣሪ ሆነው ቆይተዋል።
ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሮኬቶች
በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በሩሲያ ጦር ከፍተኛ ድበደባ እየተፈጸመበት የሚገኘው የዩክሬን ጦር፤ ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎችን ይዞ መቆየት እንዲቻለው አስቸኳይ የሆነ የከባድ መሳሪያ ድጋፍ ያሻዋል።
እስካሁን ድረስ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን፤ በአንድ ግዜ ከሁለት በላይ ሮኬቶችን የሚተኩሱ 10 ረዥም ርቀት ሮኬን ማስወንጨፊያዎችን ለዩክሬን ሰጥተዋል ወይም በመንገድ ላይ ናቸው።
ዩክሬን ግን የሩሲያ ጦርን ግስጋሴ ለመግታት ከዚህ በላይ ያስፈልገኛል ትላለች።
አሜሪካ ሰራሹ ኤም142 ከቦታ ቦታ በቀላሉ ሊንቀሳቀስ የሚችል የረዥም ርቀት ተወንጫፊ የሮኬት ሥርዓት ዩክሬን እየጠበቀችው ያለ ከባድ መሳሪያ ነው።
ምንም እንኳ ይህ መሳሪያ ሮኬቶችን የሚያስወነጭፍበት ርቀት በተተኳሾቹ አይነት የሚለያይ ቢሆንም፤ ምዕራባውያን ለዩክሬን የሰጡት ተተኳሽ እስከ 70 ኪሎ ሜትር ድረስ ይምዘገዘጋል።
ሩሲያም ከዚህ ሮኬት ማስወንጨፊያ ሥርዓት ጋር ተቀራራቢ የሆነ ስሜራች የተባለ ከባድ መሳሪያ አላት። አሜሪካ ሰራሹ ግን ከሩሲያው በላይ ዒላማውን የመምታት አቅሙ የላቀ ነው።
ሆዊትዘር
እነዚህን መድፍ መሳይ ከባድ መሳሪያዎች አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና አሜሪካ ለዩክሬን ሰጥተዋል። ዩክሬን 100 ኤም777 ሆዊትዘር መሳሪያዎችን 155 ሚሊ ሚትር ከሆኑ 300 ሺህ ተተኳሾች ጋር ከአገራቱ ተረክባለች።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር የሩሲያ እና የሩክሬን ጦርነት ውስጥ ረዥም ርቀት ተተኳሾች ትልቅ ድርሻ አላቸው ብሎ ነበር ከዚህ በፊት።
ኤም777 ሆዊትዘር መሳሪያዎችም በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝን የጠላት ኃይልን ወይም ይዞታን የመምታት አቅም አላቸው።
ሩሲያ ከዚህ ጦር መሳሪያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ጊዘትሲን-ቢ ሆዊትዘር የተባለ የከባድ ጦር መሳሪያ ሥርዓት አላት።
ፀረ ታንክ መሳሪያዎች
በትከሻ ተይዞ የሚተኮስ እና በአንድ ምት ታንኮችን ማውደም የሚያስችለው NLAW (Next generation Light Anti-tank Weapon) ዘመናዊ ቀላል ፀረ ታንክ መሳሪያን ዩክሬን ከምዕራባውያኑ አጋሮቿ ተበርክቶላታል።
ዩክሬን እነኚህን ወሳኝ የሚባሉ 5000 ፀረ ታንክ መሳሪያዎችን ከወዳጆቿ ተቀብላ ጥቅም ላይ ማዋሏ የሩሲያ በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት በእጅጉ እንደጠቀማት ይነገራል።
በዚህም ሩሲያ ወረራውን በከፈተች ማግስት ከፍተኛ ቁጥር ያለቸውን ታንኮቿን አሰልፋ ወደ ኪዬቭ ስታደርግ የነበረውን ግስጋሴ በመግታት በኩል እነዚህ ፀረ ታንክ መሳሪያዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው።
ይህ መሳሪያ ክብደቱ ከ13 ኪሎ ግራም አለመብለጡ እንዲሁም አጠቃቀሙን ለመረዳት ከአንድ ቀን ያነሰ ጊዜ ብቻ መፍጀቱ ተፈላጊነቱን ከፍ አድርጎታል።
ታንኮች
ዩክሬን በቀዝቃዛው ጦርነት በሶቪየት ኅብረት መሪነት የኔቶ ተቀናቃኝ በሆነው የኮሚኒስት አገራት የጦር ትብብር በሆነው 'የዋርሶ ስምምነት' ዲዛይን የተደረጉ ከ230 በላይ ታንኮችን ከፖላንድ እና ከቼክ ሪፐብሊክ ተረክባለች።
የዩክሬን ጦር እነዚህን ቲ-72 የተሰኙ ታንኮችን ለአስርት ዓመታት ሲጠቀም የቆየ ሲሆን፤ በሰው ኃይል፣ በጥገና እና በመለዋወጫ አቅርቦት ረገድ የካበት ልምድ አለው።
ፖላንድ የነበሯትን ታንኮች ለዩክሬን ከሰጠች በኋላ ዩናይትድ ኪንግደም ለፖላንድ ምትክ እንዲሆኗት ቻሌንጀር 2 የተሰኙ ታንኮችን ሰጥታለች።
ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች
በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሰው አልባ አውሮፕላኖች [ድሮኖች] በከፍተኛ ሁኔታ ጥቅም ላይ ውለዋል።
በዚህም እነዚህ ድሮኖች ለስለላ፣ ወታደራዊ ዒላማዎችን ለመምታት እና ክብደት ያላቸውን ቁሳቁሶች ለማንቀሳቀስ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።
ባለፉት ጥቂት ወራት ቱርክ ዝነኛ የሆኑትን ባይራክታር ቲቢ2 የተሰኙ ወታደራዊ ድሮኖቿን ለዩክሬን ሽጣለች። ባይራክታር ቲቢ2 ድሮኖችን የሚያመርተው ኩባንያ ደግሞ ድሮኖችን ለዩክሬን በስጦታ መልክ አበርክቷል።
ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ፤ ባይራክታር ቲቢ2 ድሮኖች 25ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ እየበረሩ የሩሲያ ጦር ዒላማዎችን እያወደሙ ለዩክሬን ጦር ከፍተኛ መነቃቃት ሆነዋል።
እነዚህ ድሮኖች እስካሁን ድረስ የሩሲያን ሂሊኮፕተሮች፣ ወታደራዊ መርከቦች እና የሚሳኤል ሥርዓቶችን ሳያወድሙ እንደማይቀር ይገመታል።
ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ ድሮኖች መረጃ በመሰብሰብ የሩሲያ ጦር ትክክለኛ መገኛን በመጠቆም የዩክሬን ጦር ዒላማ ውስጥ እንዲገቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
አየር መቃወሚያ
ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ዩክሬን የሩሲያ ጦር የአየር ክልሏን ሙሉ በሙሉ እንዳይቆጣጠር ከፍተኛ ትንቅንቅ ስታደርግ ቆይታለች።
ይሁን እንጂ የፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ አስተዳደር በተደጋጋሚ የተሻለ አየር መቃወሚያ ሥርዓት እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል።
በቀጣይ ቀናት አሜሪካ እጅግ ዘመናዊ እንደሆነ የሚነገርለትን ናሳማስ (NASAMS) የተሰኘውን ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፍ የፀረ አውሮፕላን ሚሳኤል ሥርዓት ለዩክሬን እንደምትልክ ይጠበቃል።
ዩክሬን የምዕራባውያኑ አጋር ከሆነችው ስሎቫኪያ ኤስ-300 የተሰኙ አየር መቃወሚያ ሥርዓቶችን ማግኘቷ ተነግሯል።