አሜሪካ ለዩክሬን ሮኬቶችን በመስጠት ‘እሳቱ ላይ ቤንዚን እያርከፈከፈች ነው’- ሩሲያ

ፕሬዝዳንት ባይደን ለኪዬቭ አዳዲስ ረዥም ርቀት የሚወነጨፉ ሚሳኤሎች እሰጣለሁ ማለታቸው የዩክሬንን ጦርነት ለማስረዘም ነው ስትል ሩሲያ ከሰሰች።

ዩናይትድ ስቴትስ መሳሪያዎቹን በመስጠት “ሆን ብላ እሳቱ ላይ ነዳጅ እየጨመረች ነው” ያሉት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ናቸው።

“እንዲህ ያሉት ድጋፎች የዩክሬን አመራሮች የሠላም ድርድሩን ለመቀጠል ላሳዩት ፈቃደኝነት አስተዋጽኦ አያደርግም” ሲሉ አክለዋል።

የጀርመን መንግሥትም በተመሳሳይ የአየር መከላከያ መሳሪያዎችን ወደ ዩክሬን እንደሚልክ ቃል ገብቷል ።

መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ለህዝብ እንደራሴዎች እንደተናገሩት ጀርመን የአይአርአይኤስቲ-ቲ (IRIS-T ) የተባለውን በጣም ዘመናዊው መሳሪያ ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው ይህም ዩክሬን አንድን ከተማ ከሩሲያ የአየር ጥቃት ለመከላከል ያስችላታል ብለዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ድጋፎቹን ኮንነው የባይደን ውሳኔ “ሦስተኛ አገርን” ወደ ግጭት የመሳብ አደጋን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል ።

የረዥም ርቀት ሚሳኤሎቹ የዩክሬን ወታደሮች ጠላትን በተሳካ መልኩ ዒላማውን ጠብቆ እንዲመታ እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

አሜሪካ መጀመሪያ ላይ መሳሪያዎቹ ወደ ሩሲያ ክልል ሊተኮሱ ይችላሉ በሚል ስጋት ላለመስጠት ወስና ነበር። ይህ እንዳማይከሰት ኪዬቭ ቃሏን በመስጠቷ ውሳኔው ሊቀለበስ መቻሉን አሜሪካ አስታውቃለች።

መሳሪያዎቹ የዩክሬንን የመደራደር አቅም ከፍ ከማድረግ ባለፈ ችግሩ በዲፕሎማሲኣዊ መንገድ እንዲፈታ እንደሚያግዝ ፕሬዝዳንት ባይደን ረቡዕ ዕለት ገልጸዋል።

አንድ የአሜሪካ ባልስልጣን እንዳስታወቁት ከመሳሪያዎቹ መካከል አራቱ ኤም142 ሃይ ሞቢሊቲ አርቲለሪ ሮኬት ሲስተም (ኤችአይኤምኤአርኤስ) የሚባሉ ናቸው።

በአሜሪካ መከላከያ ውስት ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ዶር ኮሊን ኤች ካል “እነዚህ በረዥም ርቀት የሚገኝ ዒላምን በትክክል የሚያደባዩ ናቸው። በዚህም በግንባር ላይ ካሉ የዩክሬን ወታደሮች ላይ የተወሰነ ግፊት የሚቀንሱ ናቸው። እነዚህ መሳሪያዎች በጣም ጠቃሚ ይሆናሉ ብለን እናስባለን” በማለት ገልጸዋል።

መሳሪያው እስከ 70 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኝን ዒላማ በትክክል መምታት ያስችላል። ይህም አሁን ዩከሬን እጅ ካሉት መሳሪያዎች የሚበልጥ ነው። ከሩሲያዎቹ መሳሪያዎች በተሻለም ዒላማችውን አነጣጥረው መምታት እንደሚችሉ ይታመናል።

የዋይት ሃውስ ባለስልጣናት ሮኬቶቹ ለዩክሬን እንዲሰጡ ከውሳኔ የደረሱት መሳሪያዎቹን በሩሲያ ክልል ለሚገኙ ዒላማዎች ጥቅም ላይ እንደማይውሉ ከፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ቃል ከተገባላቸው በኋላ ነው።

“ወደ ሩሲያ የሚወነጨፍ ሮኬት ለዩክሬን አንሰጥም” ብለዋል ባይደን በጽሑፋቸው።

ዜለንስኪም ይህንን ኒውስማክስ ከተሰኘው የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ጋር በነበራቸው ቆይታ አረጋግጠዋል።

“በሩሲያ ስለሚፈጸመው ነገር ፍላጎት የለንም። እኛ ዋናው ዓላማችን በዩክሬን ሉዓላዊነት ላይ ነው” ብለዋል።

ሞስኮ የዜለንስኪን ሃሳብ እንደማታምን ፔስኮቭ ገልጸዋል።

“እምነት እንዲኖረን ኪዬቭ ቃሎቿን ስለመጠበቋ ማስረጃ ያስፈልግናል። ምንም ማስረጃ ግን የለም” ብለዋል።

“አሜሪካ በማወቅ እና በቀጥታ እሳቱ ላይ ቤንዚን እያርከፈከፈች ነው... አሜሪካ በእጅ አዙር እስከመጨረሻው ዩክሬናዊ ነፍስ ድረስ ከሩሲያ ጋር ጦርነቱን ለመቀጠል ፈልጋለች።”

የሮኬቶቹ ድጋፍ ረቡዕ ይፋ የተደረገው የ700 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አካል መሆኑን የኃይት ሃውስ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ከወረራው በኋላ 11ኛው ነው በተባለለትና ይሁኝታ ባገኘው ወታደራዊ ድጋፍ ሄሊኮፕተሮች፣ ጸረ-ታንክ፣ የመከላከያ መኪናዎች እና መለዋወጫዎችም ተካተዋል።