በመተከል በተፈጸሙ ጥቃቶች የተፈረደባቸው የቀድሞ አመራሮችን ጨምሮ 86 ሰዎች “በልዩ ምህረት” ተለቀቁ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ባለፉት ዓመታት በተፈጸሙ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ጥፋተኛ ተብለው የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ 86 ሰዎች “በልዩ ምህረት” መለለቀቃቸውን ዞኑ አስታወቀ።

በመተከል ዞን በተለይም ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተፈጸሙ ጥቃቶች በመቶዎች የሚሆኑ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።

ጥቃቶቹን ለማስቆም ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት እንዲሁም በጥቃቶቹ ውስጥ እጃቸው በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ አለበት በሚል የፌደራል አመራሮችን ጨምሮ አያሌ የዞኑ አመራሮች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

‘ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል በመናድ’ እና ‘ሕዝብን በመንግሥት ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ’ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 240 እና 270 የተከሰሱ 86 ሰዎች ከሰሞኑ “በይቅርታ” መለለቃቸውን የመተከል ዞን ፍትሕ መምሪያ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የተለቀቁት ሰዎች ጉዳያቸው በፌደራል ፍ/ቤት ሲታይ የቆየ እና በዞኑ የቀድሞ ሰላምና ፀጥታ ኃላፊ በአቶ ፋንቻ አንሳያ መዝገብ ተከሰው ከ20 እስከ 22 ዓመት እስራት የተፈረደባቸው አርሶ አደሮችን እና ወጣቶችን ጨምሮ የዞን እና የወረዳ አመራሮች ናቸው።

በመዝገቡ ስር ከተካተቱት ውስጥ አብዛኞቹ የወረዳ አመራሮች ናቸው የተባሉ ሲሆን፤ ከሦስት ዓመት በላይ በእስር ላይ ቆይተዋል።

የዞኑ ፍትሕ መምሪያ “ይቅርታ” ሲል በገለጸው እርምጃ ግለሰቦቹ እንዲለቀቁ ዞኑ ለክልሉ መንግሥት ሀሳብ ማቅረቡን ገልጿል። ይህን ተከትሎ 86ቱ ሰዎች መለቀቃቸውን የጠቀሰው መምሪያው፤ ውሳኔው ለአካባቢው መረጋጋት ሲባል የተሰጠ ነው ብሏል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጉታ አበራ ግለሰቦቹ ለታጣቂዎች የመረጃ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ጠቅሰው፤ “መንግሥታቸው ለታጣቂዎች ይቅርታ እንዳደረገ ሁሉ ተባባሪ ለተባሉትም ሰዎች ይቅርታ አድርጓል” ብለዋል።

የመተከል ዞን አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ሽቱ የቀድሞ አመራሮቹ “በሐሰተኛ ምስክር ታስረናል” የሚል ቅሬታ እንደነበራቸው ጠቁመው፤ ግለሰቦቹ የተለቀቁት እርሳቸው “ልዩ ምህረት” ሲሉ በጠሩት እርምጃ መንግሥት በያዘው “የይቅርታ አቋም” ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐመድ ኡመርን (አብዲ ኢሌ) በማሳያነት ጠቅሰው፤ ምህረቱ “ለሕዝብ ጥቅም ሲባል” በሌሎች ክልሎች ላይ የተደረገው ዓይነት እንደሆነ ገልጸዋል።

“. . . የፀጥታውን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ [ጊዜ] ለመፍታት፤ ሕዝቡ ይቅርታን ስለሚፈልግ፤ የፀጥታውን ችግር ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ ሲባል መንግሥት እንደ አገር የወሰነው ውሳኔ ነው” ብለዋል።

በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ተደርጓል በተባለ እርቀ ሰላም ሕዝቡ የገጠመውን የፀጥታ ችግር በይቅርታ ለመሻገር ፍላጎት ማሳየቱ ለምህረቱ መነሻ እንደሆነ ያነሱት አቶ አትንኩት፤ የተፈረደባቸው የቀድሞ አመራሮች ካቀረቡት ጥያቄ ጋር ተዳምሮ “የምህረት ጥያቄው” በክልሉ መንግሥት በኩል ለፌደራል መንግሥቱ መቅረቡን አመልክተዋል።

“አንደኛ በተወሰነባቸው ሰዎች ጥያቄ [በጠበቆቻቸው በኩል አቤቱታ] ተነሳ፤ ሁለተኛ በወረዳና በዞን በጋራ እርቀ ሰላም መደረጉ እና ሰላም መኖሩ” እንደምክንያት ጠቅሰው ጥያቄው ከወረዳ፣ ዞን እና ከክልል ለፌደራል መንግሥቱ ቀርቦ፤ “የፌደራል መንግሥት ወስኗል” ሲሉ ስለ ሂደቱ ተናግረዋል።

ይህ የበርካታ ዓመታት እስር ለተፈረደባቸው እስረኞች የቀረበው “የምህረት ጥያቄው” ተደራጅቶ ከገባ ከአንድ ዓመት በኋላ ምላሽ እንዳገኘም አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው “ምህረቱ” በተለይም ለተጎጂ ቤተሰቦች ፍትሕን አይነፍግም ወይ? ተብለው ለቀረባላቸው ጥያቄ፤ በአካባቢው ባህል እና ወግ መሠረት እርቀ ሰላም በመውረዱ እና እርቁን “ሁሉም በመቀበሉ” የቀድሞ አመራሮቹ በምህረት መለቀቅ ፍትሕን አያጓድልም ባይ ናቸው።

“የእነዚህ ሰዎች በይቅርታ መለቀቅ ፍትሕን ያጓድላል የሚል እምነት የለኝም። እንዲያውም ማኅበረሰቡ በጣም ደስተኛ ነው። . . . እርቀ ሰላም ስለታሰረ ምንም አይነት ሌላ ችግር አይፈጥርም፤ ፍትሕ አያጓድልም” ብለዋል።

የፍትሕ መምሪያ ኃላፊውም እርምጃው ፍትሕን የሚነፍግ አይደለም ይላሉ።

“. . . ‘ያለፈ ቁርሾ ይታለፍ፤ ቁስሉ ይብቃ፤ ያለፈውን ታሪክ ማንሳት የለብንም፤ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ይሄ ነው። ስለዚህ ሁላችንም ይቅርታ ተጠያይቀን፤ አብረን ተቻችለን፤ ተከባብረን እንኖራለን’ የሚል ሕዝባዊ ውይይት ተደርጎ ነበር” በማለት ውሳኔው ፍትሕን አያዛንፍም ብለዋል።

የተለቀቁት ሰዎች ‘ወደፊት የሕግ ተጠያቂነትን በሚያስከትል ይቅርታ’ እንደተለቀቁ የተናገሩት ኃላፊው፤ “ማኅበረሰቡን ለመካስ” ወደ ቀድሞው የመንግሥት ሥራቸው ሊመለሱ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

“ከዚህ በፊትም ታጥቀው ጫካ ከገቡት ውስጥ የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል” በማለት፤ መመለስ ከፈለጉ ጥያቄ መቅረብ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ከዓመታት እስር በኋላ የተፈተቱ ሰዎች ባለፈው ሳምንት ከመንግሥት እና ከማኅበረሰቡ ጋር መምከራቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

የ“ይቅርታ ይደረግልን” ጥያቄ ያቀረቡ እና ውሳኔ የሚጠብቁ ተጨማሪ ሌሎች 80 የሚሆን ሰዎች እንዳሉ የፍትሕ መምሪያ ኃላፊው ጠቁመዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ማንነትን በለዩ ጥቃቶች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከተወሰኑት ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች እንዳሉ ሲዘገብ ነበር።

የክልሉ ብሔሮች ተብለው ከተጠቀሱት ውጪ የሆኑ እና ለዘመናት በአካባቢው ሲኖሩ የቆዩ ማኅረበረሰቦች በጥቃቶቹ በተለይ ዒላማ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በተደጋጋሚ ሲፈጸሙ ከነበሩት ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ከተገደሉት እና ጉዳት ከደረሰባቸው በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው የመፈናቀል ዕጣ እንደገጠማቸው ሲዘገብ ቆይቷል።