ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ አፍሪካ ጥቁር ተማሪዎች “በባርነት ለጨረታ” መውጣታቸው ቁጣ አስነሳ
በደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን ከተማ ጥቁር ተማሪዎችን እንደ ባሪያ ለመሸጥ ጨረታ ያወጡ ተማሪዎች ጉዳይ ቁጣ አስነሳ።
ጥቁር ተማሪዎቹን በብረት ፍርግርግ ውስጥ አስገብተው እንደ ባሪያ ለጨረታ አቅርበዋል የተባሉ ተማሪዎችም የዲሲፒሊን ክስ ሊቀርብባቸው መሆኑን የኬፕታውን ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጥቁር ተማሪዎቹ በፍርግርግ ብረት ውስጥ ሆነው ሌሎች ተማሪዎች ሲጫረቱባቸው የሚያሳየው ቪዲዮ ባለፈው ሳምንት አርብ በማህበራዊ ሚዲያ ተጋርቶ ከፍተኛ ቁጣን አስነስቷል።
ጥቁር ተማሪዎች በጨረታ ሲሸጡ የሚያሳየው ቪዲዮ የተቀረጸው በፓይንላንድ ትምህርት ቤት ሲሆን የተሳተፉትም ተማሪዎች ስምንተኛ ክፍል መሆናቸው ተነግሯል።
የደቡብ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በክስተቱ ላይ የራሱን ምርመራ መክፈቱን አስታውቋል።
የተማሪዎቹ ጨረታ መውጣት የተሰማው ሌሎች ሁለት ትምህርት ቤቶች የዘረኝነት ክስተት ተፈጽሟቸዋል በተባለ ማግስት ነው።
እንዲህ አይነት ዘረኝነት እየታየ ያለውም ጥቁሮችን ከሰው በታች ያወረደው የአናሳ ነጮች ስርዓት የሆነው አፓርታይድ ከተገረሰሰ ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ ነው።
“እነዚህ ክስተቶች አገሪቷ ወደ ዲሞክራሲ ካመራችበት ከ30 ዓመታት በኋላም ቢሆን መቀጠላቸው አሳሳቢ ነው” ያለው ኮሚሽኑ በተለይም በትምህር ቤቶች ውስጥ መከሰታቸው የበለጠ ስጋትን የፈጠረ ነው ብሏል።
ለቀልድ የተደረገውን የባርያ ጨረታ አካሂደዋል የተባሉ አራቱ የፓይንላንድስ ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት ታግደዋል።
“ምርመራው ይቀጥላል። ከስተቱ መፈጸሙ ሪፖርት መደረጉን ተከትሎ እስካሁን ድረስ 24 ተማሪዎችን አናግረናል” ሲሉ የዌስተርን ኬፕ የትምህርት ዲፓርትመንት ቃለ አቀባይ ብሮናግ ሃምሞንድ ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ ጠቅሰዋል።
አክለውም “የስነ ምግባር ደንቡን የተላለፉ ሌሎች ተማሪዎች ከተገኙም እርምጃዎች ይወሰድባቸዋል” ብለዋል።
ይህ ነገር መጀመሪያ ይፋ የወጣው አንደኛው ተማሪ ሌሎች ጥቁር ተማሪዎች እንደ ባሪያ ሲሸጡ የሚያሳየውን ቪዲዮ ለእናቱ ማሳየቱን ተከትሎ ነው። እናቲቱም ጉዳዪን ለትምህርት ቤቱ አስተዳደር እንዲሁም ለሃገር ውስጥ ሚዲያዎች ሪፖርት አድርጋለች።
በብረት ፍርግርግ ውስጥ የነበሩ ጥቁር ወንዶች ባሉበት ስፍራ የ14 ዓመት ልጇን በግዴታ ሊያስገቡት ከሞከሩ ተማሪዎች ጋር መታገሉን ተናግራለች።
እንደ እናቲቱ ገለጻ ይህንን የፈጸሙት ከነጭ እና ጥቁር የተቀላቀሉ በደቡብ አፍሪካ ከለርድ ተብለው የሚጠሩ ተማሪዎች ናቸው።
በቪዲዮው ላይ ተማሪዎቹ እስከ 100 ሺህ ራንድ (5 ሺህ 400 ዶላር) ድረስ የሚያወጡ የተለያዩ ጨረታዎችን ሲጠሩ ይደመጣሉ።
በዚህ ለተጎዱ ተማሪዎች በቅድሚያ የማማከር ድጋፍ መሰጠቱን የሚናገሩት ቃለ አቀባይዋ ሁሉም የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።
በኬፕታውን የባርያ ንግድ የተጀመረው ሆላንድ በአውሮፓውያኑ 1650ዎቹ ግዛቲቷን ከተቆጣጠረች በኋላ ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ በባርያ ንግድ ከደቡብ ምስራቅ እስያ፣ ማዳጋስካር እና ሞዛምቢክ ወደ ግዛቲቷ ገብተዋል።
በደቡብ አፍሪካ ካሉ ከተሞች ውስጥ የነጮች የበላይነት ከሚታዩባት ከተሞች አንዷ ኬፕታውን ናት።
ለዚህም ዋነኛው ምክንያቱ በወቅቱ የነበረው የነጮች አገዛዝ ጥቁሮችን እና ሌሎች ማህበረሰቦችን ወደ ከተማዋ ጫፍ የገፋቸው ሲሆን ይህም የአፓርታይድ ውርስ አሁንም ቀጥሏል።