በአዲስ አበባ የመንገድ ላይ ፍተሻዎች፣ እስሮች እና ማዋከቦች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ኢሰመጉ ገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ የፀጥታ ኃይሎች የሕግ አግባብ በሌለው መልኩ የመንገድ ላይ ፍተሻዎች እስሮች፣ ማዋከቦች እና እንግልቶችን በዜጎች ላይ እየፈጸሙ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አስታወቀ።

ኢሰመጉ እነዚህ እስሮች እና እንግልቶች በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉት የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በአዲስ አበባ ከተማ ተከታታይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን እንደሚያደርግ ማስታወቁን ተከትሎ እንደሆነ ሰኔ 07/ 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

የጋራ ግብረ ኃይሉ በአዲስ አበባ ከተማ “የተለያዩ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍጠር የተዘጋጁ ኃይሎች እንዳሉ ደርሼባቸዋለሁ” ሲል ግንቦት 30/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ግብረ ኃይሉ በእነዚህ ኃይሎች ላይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ለማካሄድ እንዳቀደ አስታውቆ ማኅበረሰሰቡ “ፀጉረ ልውጦችን ሲመለከት ጥቆማ እንዲሰጥ” እና እንዲተባባርም ጥሪ ማድረጉ ይታወሳል።

አምስት አካላትን የያዘው የፀጥታ እና ደኅንነት ግብረ ኃይል ሰላም እና ፀጥታን ለማስከበር እየሰራ ባለው ተግባር በአንዳንድ አካባቢዎች ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም መስተዋሉን ኢሰመጉ ጠቅሷል።

የጋራ ግብረ ኃይሉ “ከመደበኛው የሕግ ሥነ ሥርዓት ከፍ ያለ ሥልጣን እንዳለው በማሰብም” በአንዳንድ አካባቢዎች ሥልጣንን አላግባብ ለመጠቀም ምክንያት መሆኑም ከኢሰመጉ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ለሕግ አስፈጻሚው አካል ከፍ ያለ ሥልጣን የሚሰጡ እንዲህ አይነት እርምጃዎች በሕግ ከተደነገገው ውጪ በሚፈጸሙበት ወቅት፣ በሂደቱ የሚሳተፉ አካላት የሕግ ሥነ ሥርዓትን ያልተከተሉ ድርጊቶችን ለመቆጣጠር እና ሰዎች ሕጋዊ፣ አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ ባልሆነ መልኩ ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲገደቡባቸው ሲያደርጉ ይስተዋላል ብሏል።

ሰላም እና ደኅንነትን ለማስከበር ተብለው በመንግሥት የሚሰሩ እነዚህ ተግባራት አንዳንድ ጊዜ የሕግ ሥርዓትን ያልተከተሉ እንዲሁም የሰዎች ሰብዓዊ መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚጥሉ ሆነው መገኘታቸውን የመብት ተከራካሪው ድርጀት ገልጿል።

ኢሰመጉ ሰላም እና ፀጥታን የማስከበር ሂደቱ ላይ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ሕግ እና ሥርዓትን የተከተለ አሰራር እንዲኖርም ጠይቋል።

የፀጥታ አካላት ይህንን ኦፕሬሽን በሚያካሂዱበት ወቅት የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች አላግባብ እንዳይገድቡ እና እንዳይጥሱ ተገቢውን የሕግ ሥነ ሥርዓት እንዲከተሉ እና ያልተመጣጠነ እንዲሁም አላስፈላጊ የሆነ ኃይልን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

በተጨማሪ የጋራ ግብረ ኃይሉ በሚያካሂደው ኦፕሬሽን ሥልጣናቸውን አላግባብ የሚጠቀሙትን በሂደቱ የሚሳተፉ አካላትን የሚቆጣጠርበት እና በሕግ ተጠያቂ የሚያደርግበትን ሥርዓት እንዲዘረጋ ኢሰመጉ ጥሪውን አቅርቧል።