በሸገር ከተማ ‘ያለ ዕቅድ እና ሕጋዊነት’ ተሠርተዋል ተብለው የፈረሱት 22 መስጊዶች መሆናቸው ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል፣ በሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ “ያለ ፕላን እና ሕጋዊነት ተሠርተዋል” በሚል የፈረሱት 22 መስጊዶች መሆናቸውን የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ “ለሕዝበ ሙስሊሙ የመስጊድ ጥያቄዎች በሙሉ አፋጣኝ መፍትሄ” እንዲሰጥ ለክልሉ ጥያቄ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ የተመራ የልዑካን ቡድን ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር መነጋገሩን ምክር ቤቱ ዛሬ ሰኔ 1/2015 ዓ.ም. ያወጣው መግለጫ አሳውቋል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ እየተከናወነ ስላለው የመስጊዶች ፈረሳ ከርዕሰ መስተዳደሩ ጋር “አምስት ሰዓታት የፈጀ ውይይት” መካሄዱ ተገልጿል።

በውይይቱ የኦሮሚያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት እንዲሁም የኦሮሚያ ከፍተኛ አመራሮች እንደተገኙም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም ሆነ ሕዝበ ሙስሊሙ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚካሄድ “ማዘመን፣ ማልማት እና እድገትን” እንደሚደግፍ፣ ሆኖም ዕቅዱ “በቂ የእምነት ተቋማትን ለአማኞች ማቅረብን እና ሰው ተኮር መሆን እንደሚገባው” ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

በተጨማሪም የፀጥታ አካላት “ሰላማዊ ሙስሊሞች ላይ በቀጥታ በመተኮስ ሙስሊሞችን መግደላቸው እና ማቁሰላቸው ተገቢ አለመሆኑ” በመግለጫው ተጠቅሷል።

ከኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ጋር በተደረገው ውይይትም “ንጹሃን ላይ በመተኮስ የገደሉ እና ያቆሰሉ አካለት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ” ጥያቄ ቀርቧል።

በውይይቱ ከተነሱ ነጥቦች መካከል በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመስጊድ መሬትን በሕጋዊ መንገድ የማግኘት እና የመሥራት እንዲሁም ለተሠሩት መስጊዶች ካርታ እና የማስፋፊያ መሬት ማግኘትን በተመለከተ “በርካታ ችግሮች መኖራቸው” አንዱ መሆኑ ተጠቅሷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ በውይይቱ ላይ “አስፈላጊው የቤተ እምነት መሥሪያ መሬቶችን በፕላኑ መሠረት ለምዕመኑ እንደሚሰጥ እና በቆርቆሮ ሳይሆን የከተማዋን ፕላን የሚመጥን በርካታ ዘመናዊ መስጊዶች በከተማው እንዲሠሩ እንደሚፈልጉ” መናገራቸው ተገልጿል።

አያይዘውም “በሸገር ከተማ ላይ በአገር ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል ትልቅ እና ዘመናዊ መስጊድ እንዲሁም ለሌሎች የእምነት ተቋማት መሥሪያ ቦታ እንደሚሰጥ” ገልጸዋል ተብሏል።

የሸገር ከተማ አስተዳደር “ከፕላን ውጪ ተሠርተዋል” ያላቸውን መስጊዶች ለማፍረስ ሲነሳ “ከሚመለከታቸው የእስልምና ጉዳዮች አካላት ጋር እንዳልተወያየ” በመግለጫው ተካቷል።

በተያያዘም በጉዳዩ ላይ እንወያይ በሚል በተደጋጋሚ የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ ለማወያየት አለመሞከሩ “በቅሬታ መልክ ቀርቧል” ይላል የምክር ቤቱ መግለጫ።

ውይይት ሳይደረግ መስጊዶችን ወደ ማፍረስ መገባቱ “በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ቅሬታ ፈጥሮ ጉዳዩ እስከ ነፍስ መጥፋት ማምራቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው” ብሏል መግለጫው።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ቀደም ብሎ በጉዳዩ ላይ ውይይት አለመደረጉ “ስህተት መሆኑን” እንደገለጹ እና “በተፈጠረው ሁኔታ ሕይወታቸውን ላጡት ሙስሊሞች ማዘናቸውን” መናገራቸውም ተጠቁሟል።

“ሕዝበ ሙስሊሙ ከሸገር ከተማ መስጊድ ፈረሳ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩት ሁኔታዎች እጅጉን መጎዳቱን እና ማዘኑን በማብራራት ተገቢው ካሳ እና የሞራል ሕክምና እንደሚያስፈልገው” በውይይቱ መነሳቱም ተገልጿል።

ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በኦሮሚያ ክልል፣ ሸገር ከተማ በርካታ መስጊዶች መፍረሳቸውን ለቢቢሲ ገለጾ ነበር።

እንደ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የነዋሪዎች ቤቶች እና የሃይማኖት ተቋማት ፈረሳን የሚኮንኑ መግለጫዎች ሲያወጡ ቆይተዋል።

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ሳምንታት ከጁመዓ ሶላት በኋላ የመስጊዶችን ፈረሳ በመቃወም ሕዝበ ሙስሊሙ ድምጹን ማሰማቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተከሰተ ግጭትም ሰዎች መሞታቸው እንዲሁም የአካል ጉዳት መድረሱም አይዘነጋም።

ባለፈው ሳምንት በታላቁ አንዋር መስጂድ የጁመዓ ሶላት ከተጠናቀቀ በተነሳው ግርግ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጉዳዩን በተመለከተ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር ውይይት እንደሚያደርግ በገለጸው መሠረትም ውይይቱ ተካሂዷል።

በዚህ ውይይት ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል፣ አዲሱ የሸገር ከተማ ዕቅድ ወደ ተግባር እስኪገባ ድረስ ሙሉ በሙሉ መኖሪያ ቤቶች ባልፈረሱባቸው አከባቢዎች ለሚኖሩ ሙስሊሞች የአምልኮ ቦታ ይዘጋጃል ማለታቸው ተገልጿል።

“በጊዜያዊነት የሚሰገዱባቸው መስጊዶች እንደሚዘጋጁ እና የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ እና የሸገር ከተማ አስተዳደር በጋራ በመጋገር መስጊድ መሥሪያ ቦታ እንደሚያዘጋጁ” መግለጫው አመልክቷል።

የሸገር ከተማ ዕቅድ ለሃይማኖት ተቋማት ያዘጋጃቸውን ስፍራዎችን የሙስሊም ተወካዮች ከክልሉ መንግሥት ጋር እንዲመለከቱ እና እንዲያረጋግጡ እንደሚደረግ በውይይቱ ተነስቷል፡፡

በተጨማሪም ሕዝበ ሙስሊሙ ያቀረባቸው እና የሚያቀርባቸው የመስጊድ ጥያቄዎች በዕቅዱ መሠረት ምላሽ እንደሚሰጣቸው ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

በሸገር ከተማ ውስጥ ካሉት 800 የተለያዩ ሃይማኖቶች ተቋማት መካከል 656 የሚጠጉት “ከዕቅድ ውጪ” መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህንም ወደ “ሕጋዊ እና ከተማውን በሚመጥኑ ተቋማት” ለማሻገር እንደሚሠራ ተገልጿል።

በዚህ ሂደት የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አቅሙን በማጠናከር እና በውይይት የሃይማኖት ተቋማቱ “ራሳቸው መፍረስ ያለባቸውን እንዲያፈርሱ” እንደሚደረግ እና ከአሁን በኋላ “መንግሥት በራሱ ማፍረስ እንደሚያቆም” ርዕሰ መስተዳድሩ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።