ሳዑዲ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት በሞት የቀጣቻቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

ሳዑዲ አረቢያ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በሞት የቀጣቻቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የሰብአዊ መብት ድርጅት ገለጸ።

እአአ በ2025 በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር 347 ሲሆን፤ አምና ደግሞ 345 ሰዎች ላይ ቅጣቱ ተፈጽሟል።

መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው እና በሳዑዲ አረቢያ የሚፈጸሙ የሞት ቅጣቶችን የሚከታተለው ሪፕራይቭ፤ "ዓመቱ በከፍተኛ መጠን የሞት ቅጣት የተፈጸመበት ነው" ብሏል።

በቅርቡ ሁለት ፓኪስታናውያን ከአደንዛዥ ዕፅ ክስ ጋር በተያያዘ በሞት ተቀጥተዋል።

አንድ ጋዜጠኛ እና አምስት ሴቶችም በሞት የተቀጡ ሲሆን፤ ወንጀል ፈጽመዋል በተባሉበት ወቅት ታዳጊ የነበሩ ሁለት ወጣቶች ላይም ቅጣቱ ተፈጻሚ ሆኗል።

ሪፕራይቭ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በሞት ከተቀጡት ሰዎች ሁለት ሦስተኛው የተከሰሱት እምብዛም ጎጂ ካልሆኑ አደንዛዥ ዕፆች ጋር በተያያዘ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት "ይህ ከዓለም አቀፍ መርሕ እና አሠራር ጋር ይቃረናል" ብሏል።

ሳዑዲ አረቢያ "ፀረ አደንዛዥ ዕፅ ንቅናቄ" ከምትለው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በሞት ከተቀጡት ግማሹ የሳዑዲ ዜጎች አይደሉም።

ቢቢሲ ስለ ሞት ቅጣቶቹ ከሳዑዲ መንግሥት አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

የሪፕራይቭ የመካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ የሞት ቅጣት ጉዳዮች ኃላፊ ጂድ ባስዮኒ "ሰብአዊ መብት ላይ የመቀለድ ያህል ነው" ብለዋል።

በሳዑዲ የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ሰዎችን ማሰቃየት እና እንዲናዘዙ ማስገደድ የተለመደ መሆኑን ገልጸዋል።

"በጭካኔ የተሞላ እና የዘፈቀደ ድርጊት ነው" ሲሉም አክለዋል። ሳዑዲ ዒላማ የምታደርገው ስደተኞችን፣ ንጹኃን ዜጎችን እና የህዳጣን ማኅበረሰብ አባላትን እንደሆነም ጠቁመዋል።

ባለፈው ሳምንት ግብፃዊ ዓሣ አስጋሪ ወጣት ኢሳም አል-ሻዝሊ በሞት ተቀጥቷል።

በ2021 በሳዑዲ የባሕር ዳርቻ የተያዘ ሲሆን፤ አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወር ተከስሷል። በሞት ከተቀጡት 96ቱ ከሐሺሽ ጋር በተያያዘ የተከሰሱ ናቸው።

ጂድ ባስዮኒ "በማንኛውም ጉዳይ ላይ የሚያስተላልፉትን ውሳኔ ሕዝቡ ችላ እንዳይል ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ሲሉ የትኛውንም ሰው በሞት ሊቀጡ ይችላሉ" ብለዋል።

ሳዑዲ ተቃውሞ ከማሰማት፣ ከንግግር ነጻነት እና ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍ እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

እአአ በ2022 ሳዑዲ ውሳኔ ካሳለፈች በኋላ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ በሞት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ተመድ ውሳኔውን "አሳዛኝ" ብሎታል።

ቤተሰቡ ሞት የተፈረደበት አንድ ግለሰብ "በፍርሃት እየኖርን ነው" ብሏል።

"የምተኛው የሞት ቅጣት በማይፈጸምባቸው ቀናት ብቻ ነው። እነዚህም አርብ እና ቅዳሜ ናቸው" ሲል ተናግሯል።

ለዓመታት አብረዋቸው የታሰሩ ሰዎች እየተጎተቱ የሞት ቅጣት ወደሚፈጸምበት ሥፍራ እንደሚወሰዱ የዐይን እማኞች ገልጸዋል።

የሳዑዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን እአአ በ2017 ሥልጣን ከያዙ ወዲህ አንዳንድ ክልከላዎችን ቢያላሉም የተቃውሞ ድምጾችን አፍነዋል።

የሳዑዲ ምጣኔ ሃብት ነዳጅ ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዳይሆን አገሪቱን ለዓለም ክፍት አድርገዋል። ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ ተፈቅዷል። የሃይማኖታዊ ፖሊሶች ስምሪትም ተቋርጧል።

ሂውማን ራይትስ ዋች እንደሚለው ግን የሰብአዊ መብት ረገጣ "አሳሳቢ" ሆኗል። ዋነኛው ስጋት ደግሞ የሞት ቅጣት ነው።

ከሳዑዲ በተጨማሪ ቻይና እና ኢራንም የሞት ቅጣት በመፈጸም በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተኮንነዋል።

በሂውማን ራይትስ ዋች የሳዑዲ አረቢያ ሰብአዊ መብት ጉዳዮች ተመራማሪ ጆይ ሺያ "መሐመድ ቢን ሳልማን ያለ ምንም ወጪ የሞት ቅጣት ይፈጽማሉ። በሳዑዲ የስፓርት እና መዝናኛ መሰናዶዎች ያለ ምንም እክል ይከናወናሉ" ብለዋል።

ሪፕራይቭ እንዳለው የሞት ቅጣት የሚፈጸምባቸው ሰዎች ቤተበሶች ስለ ቅጣቱ አይነገራቸውም፤ አስከሬንም አይሰጣቸውም።

ሳዑዲ በምን መንገድ የሞት ቅጣት እንደምትፈጽም ይፋ ባታደርግም በመቅላት ወይም በጥይት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።

በተመድ ከሕግ ውጭ የሚፈጸም ግድያ ልዩ መርማሪ የሆኑት ዶ/ር ሞሪስ ቲዳባል-ቢንዝ፤ ሳዑዲ የሞት ቅጣት መፈጸም ማቆም እንዳለባት ተናግረዋል።

ሳዑዲ ዓለም አቀፍ ሕግን እንድታከብር፣ የውጭ አገር ዜጎች ከኤምባሲያቸው ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድ እንዲመቻች፣ የሞት ቅጣት የሚፈጸምባቸው ሰዎች ቤተሰቦች መረጃ እንዲሰጣቸው፣ በሞት የተቀጡ ሰዎች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው እንዲሰጥ እና የሞት ቅጣት መረጃዎች ይፋ እንዲደረጉ ጠይቀዋል።

አብዱላሕ አል-ዳርዚኒ እና ጃላል አል-ላባድ ወንጀል ፈጽመዋል በተባሉት ወቅት ታዳጊዎች ነበሩ።

እአአ ከ2011 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት የሳዑዲ መንግሥት የሺአ ሙስሊሞች ላይ የሚፈጽመውን አፈና ተቃውመዋል። በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይም ተገኝተዋል።

አምነስቲ የፍርድ ሒደቱ ፍትሐዊ አይደለም ቢልም ሁለቱም በሞት ተቀጥተዋል። "ጥፋታቸውን እንዲያምኑ ስቅይት ደርሶባቸዋል" ሲልም አምነስቲ ገልጿል። ተመድ ሁለቱም ከእስር እንዲፈቱ አጥብቆ አሳስቦ ነበር።

ጋዜጠኛው ቱሪክ አል-ጀስር በ2018 ታስሮ ከጽሑፎቹ ጋር በተያያዘ በሽብር ክስ ሞት ተፈርዶበታል። ተመድ ጋዜጠኛው እንዲለቀቅ ሲጠይቅ ቆይቷል።

ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ እንዳለው ቱሪክ አል-ጀስ፤ መሐመድ ቢን ሳልማን ሥልጣን ከያዙ በኋላ የተገደለ የመጀመሪያው ጋዜጠኛ ነው።

ጀማል ኻሾግጂ በ2018 ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ ቆንጽላ ውስጥ መገደሉ አይዘነጋም።

ባለፈው ኅዳር ተመድ ለሳዑዲ በጻፈው ደብዳቤ 32 የግብፅ እና ዮርዳኖስ ዜጎች ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ በሞት እንዲቀጡ መወሰኑ እንዳሳሰበው ገልጿል።

ዘመዱ የተገደለበት ግለሰብ "እንደ ፍየል ወደ ሞታቸው እየተወሰዱ ነው" ብሏል።

ሳዑዲ ከተመድ ለተላከላት ደብዳቤ በሰጠችው ምላሽ አገሪቱ "ሰብአዊ መብትን እንደምታከብር" እንዲሁም "ሕጉ ስቅይትን እንደማይፈቅድ" ገልጻለች።

"የሞት ቅጣት የሚወሰነው አደገኛ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ብቻ። ሁሉንም የሕግ ማዕቀፎች ተከትሎ ውሳኔው ይተላለፋል" በማለትም ሳዑዲ አቋሟን አስታውቃለች።