ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሁለት ኢትዮጵያውያን ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ በሳዑዲ አረቢያ በሞት ተቀጡ
ሳዑዲ አረቢያ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ክስ የቀረበባቸውን ሁለት ኢትዮጵያውያንን በሞት መቅጣቷን የሳዑዲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በርካታ ሰዎችን በሞት በመቅጣት የምትታወቀው ሳዑዲ አረቢያ ሐሙስ ዕለት መገደላቸው የተገለጸውን ሁለት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ባለፉት ሰባት ወራት የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው የውጭ ዜጎች ብዛት 101 መድረሱን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት የዜና ተቋም ይፋ ባደረገው መግለጫ ላይ የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው የሁለቱ ኢትዮጵያውያን ስም የተጠቀሰ ሲሆን፣ "ሃሺሽ ወደ አገሪቱ ሲያስገቡ ተይዘው ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል" ብሏል።
ምንም እንኳን የሞት ቅጣቱ የተፈጸመባቸው የሁለቱ ኢትዮጵያውያን ስም ቢገለጽም፣ ቢቢሲ የሟቾቹ ቤተሰቦች ስለሞት ቅጣቱ በአግባቡ ስለመረዳታቸው ለማወቅ ስላልቻለ ማንነታቸውን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ዘገባው ጨምሮም የሁለቱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ቀርቦ "በክሳቸው ጥፋተኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ የሞት ፍርድ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል" ብሏል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰኞ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት በሳዑዲ አረቢያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ላይ የሞት ቅጣት መፈጸሙን አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት በሳዑዲ አረቢያ ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በውጪ ዜጎች ላይ የሚፈጸም የሞት ቅጣት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን አምነስቲ በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።
ከእነዚህ የሞት ቅጣቶች መካከል ከሦስቱ አንዱ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች የተፈፀመ ሲሆን፣ እነዚህም በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ እና መስፈርቶች በሞት የማያስቀጡ ወንጀሎች መሆናቸውን አምነስቲ በሪፖርቱ ላይ አብራርቷል።
ባለፉት አስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች የሞት ቅጣት ከተቀበሉት 597 ሰዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት የውጭ አገር ዜጎች መሆናቸውንም ጨምሮ አስታውቋል።
ከእነዚህም መካከል 34ቱ ከግብፅ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከዮርዳኖስ፣ ከናይጄሪያ፣ ከፓኪስታን፣ ከሶማሊያ እና ከሶሪያ የመጡ የውጭ አገር ዜጎች መሆናቸውን አምነስቲ በሪፖርቱ ላይ ዘርዝሯል።
ሰባት ወራት ባስቆጠረው ያለንበት የአውሮፓውያን ዓመት በአጠቃላይ 189 ሰዎች በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በሞት የተቀጡ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም 88ቱ የአገሪቱ ዜጎች ሲሆኑ 101ዱ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ዜጎች መሆናቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
በርካታ የዓለም አገራት የሞት ቅጣትን ያስቀሩ ሲሆን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አሁንም በመላው ዓለም የሞት ቅጣትን ለማስቀረት እያጣሩነው።
ሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ እና የባሕረ ሰላጤው አገራት የሞት ቅጣት በስፋት የሚፈጸምባቸው ናቸው።
በተለይ ሳዑዲ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በሞት ከሚቀጡባቸው ቀዳሚ አገራት መካከል ትገኛለች።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥር 2014 እስከ ሰኔ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ሳዑዲ አረቢያ 1,816 ሰዎችን በሞት መቅጣቷን የአገሪቱ የፕሬስ ኤጀንሲ አስታውቋል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ዳይሬክተር ክሪስቲን ቤከርል "ሳዑዲ አረቢያ ያለመታከት እና ያለ ርህራሄ የሞት ቅጣትን ከኢፍትሃዊ የፍርድ ሂደቶች በኋላ መጠቀሟ ለሰው ልጅ ሕይወት ያላትን ንቀት የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር ለተያያዙ ወንጀሎች መተግበሩም በከፍተኛ ሁኔታ የዓለም አቀፍ ሕግ እና ደረጃዎችን መጣስ ነው" ብለዋል።
በሳዑዲ አረቢያ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሠረተባቸውን ግለሰቦች በሞት መቅጣት በአውሮፓውያኑ 2020 አግዳ ነበር።
ከሁለት ዓመታት በፊትም ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን የሞት ቅጣት ተፈጻሚነት የግድያ ወንጀል የፈጸመ ግለሰብ ላይ ብቻ እንዲወሰን አውጀው ነበር።
ሆኖም በዚያው ዓመት ከጥቂት ወራት በኋላ ሳዑዲ ምንም ዓይነት ምክንያት ሳትሰጥ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ የተከሰሱ ግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ ማድረግ ጀምራለች።
ሳዑዲ አረቢያ፤ ኢራንን፣ ኩዌትን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስን ጨምሮ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ክሶች የሞት ቅጣት ከሚፈጸምባቸው በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አንዷ ነች።