በደቡብ ኮሪያ የአውሮፕላን አደጋ 179 ሰዎች ሲሞቱ 2 ሰዎች ተረፉ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/YONHAP
በደቡብ ኮሪያ አንድ አውሮፕላን በማረፍ ላይ ሳለ ባጋጠመው አደጋ እስካሁን 179 ሰዎች መሞታቸው ተረጋገጠ።
ከሰዓታት በፊት የሟቾች ቁጥር 85 እንደነበር የተዘገበ ሲሆን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አሁን የሟቾች ቁጥር 179 መድረሱን አሳውቀዋል።
ጄጁ የተባለው አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን ከባንግኮክ መጥቶ በደቡብ ኮሪያው ሙዋን አየር ማረፊያ ሲያርፍ ነበር መንገዱን ስቶ ከግድግዳ የተጋጨው።
ከሥፍራው የወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የአውሮፕላን የፊተኛው ክፍል በእሣት ሲያያዝ አስመልክተዋል።
ምንም እንኳ እስካሁን የአደጋው መንስዔ ባይታወቅም የእሣት አደጋ አገልግሎት ምናልባትም ከወፍ ተጋጭቶ አሊያም ባለው ከባድ የአየር ፀባይ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብሏል።
አውሮፕላኑ 181 ሰዎች አሳፍሮ ነው ከታይላንድ የተነሳው። አብዛኛዎቹ ደቡብ ኮሪያዊያን መሆናቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ሁለት የበረራ ሠራተኛ በሕይወት ሲተርፉ ሌሎች ሌሎቹ በጠቅላላ መሞታቸው ተረጋግጧል።
በሥፍራው ሰዓት አቆጣጠር ቅዳሜ ጥዋት የተከሰተውን አደጋ ለመቆጣጠር ቢያንስ 80 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እየተሯሯጡ ይገኛሉ ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል አስነብቧል።
የእሣት አደጋ አገልግሎት ዋና ኃላፊ እንዳሉት የአውሮፕላኑ አንደኛው ክንፍ ምንም ዓይነት አደጋ አልደረሰበትም።
ባለፈው አርብ የተሾሙት የደቡብ ኮሪያ ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ቾይ ሳንግ-ሞክ በሥፍራው ተገኝተው መመሪያ መስጠታቸውን ቢሯቸው አስታውቋል።
ሙዋን አየር ማረፊያ በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኝ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2007 ነው አገልገሎት መስጠት የጀመረው። አየር ማረፊያ ከእስያ ለሚመጡ አውሮፕላኖች ቀንደኛ መተላለፊያ ነው።
የጄጁ አየር መንገድ ንብረት የሆነው 7ሲ2216 የተሰኘ አውሮፕላን 175 ተሳፋሪዎች እና 6 የበረራ ሠራተኞችን ይዞ ከታይላንድ መዲና ባንግኮክ ተነስቶ በሥፍራው ሰዓት አቆጣጠር ቅዳሜ ጥዋት 3፡00 ገደማ ነው የደረሰው።
ጄጁ አየር መንገድ አደጋውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ይቅርታ ጠይቋል።
በአውሮፓውያኑ 2005 የተቋቋመው ጄጁ አየር መንገድ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ከሚገኙ ግዙፍ አየር መንገዶች አንዱ ሲሆን በቅናሽ ዋጋ አገልግሎት በመስጠት ይታወቃል።
የዜና ወኪሉ አክሎ ከተሳፋሪዎች መካከል 173 ደቡብ ኮሪያዊያን ሁለቱ ደግሞ የታይላንድ ዜጋዎች ናቸው ብሏል።












