ጎዳና ላይ ሰው የሚቃጠልባት በወሮበላ ቡድኖች ቁጥጥር ስር የምትገኘው የሄይቲ መዲና

ቬንዳ እና ልጇ ሻይና

የፎቶው ባለመብት, Jack Garland, BBC

የሁለት ዓመቷ ሻይና በሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት አው ፕሪንስ አገልግሎት ከሚሰጡ ጥቂት ሆስፒታሎች ውስጥ በአንዱ ተኝታ ግሉኮስ እየተሰጣት ነው። ሕክምናው ከደረሰባት ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚታደጋት እናቷ ቬንዳ ተስፋ አድርጋለች።

በሄይቲ በረሃብ አፋፍ ላይ ካሉ 760 ሺህ ህጻናት አንዷ ሻይና ነች።

ቬንዳ በሰፈሯ የሚካሄደውን የወሮበሎች ጦርነት በመፍራት ለሳምንታት ልጇን ወደ ሆስፒታል ሳትወስድ ቆይታለች።

ሆስፒታል ለመድረስ መዘግየቷ የልጇ ሕክምና ላይ ጫና እንደማይፈጥር ተስፋ አድርጋለች።

"ለልጄ ተገቢውን እንክብካቤ ማግኘት እፈልጋለሁ። እሷን ማጣት አልፈልግም" በማለት እያለቀሰች ትናገራለች።

እአአ በ2021 ፕሬዝዳንት ጆቬኔል ሞይሴ ከተገደሉ በኋላ ሄይቲ በወሮበሎች ሁከት እየታመሰች ነው። 85 በመቶ የሚሆነው ዋና ከተማዋ በወሮበሎቹ ቁጥጥር ስር ይገኛል።

ሄይቲዎች በሆስፒታል ውስጥ ሆነው እንኳን ከጦርነቱ ነጻ አይደሉም። የተባበሩት መንግስታት በዚህ ዓመት ብቻ 5 ሺህ ሰዎች ሆስፒታል ውስጥ ተገድለዋል፤ አገሪቱን የውድቀት አፋፍ ላይ ትገኛለች ብሏል።

አንድ ቀን ቀደም ብሎ ፖሊሶች በድንገተኛ ክፍል ውስጥ ከሚገኙት የወሮበሎች ቡድን አባላት ጋር ተጋጭቷል። ይህ ሁሉ ሲሆን ታካሚዎች እንደነበሩ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ገልጸዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች በየቦታው ይገኛሉ። አንደኛው የሆስፒታል ክፍል በጥይት የተጎዱ ወጣቶች እየታከሙበት ነው።

ፒየር አንዱ ነው።

በጥይት የተመታው ፒየር

የፎቶው ባለመብት, Jack Garland, BBC

ፒየር ሥራ ውሎ ወደ ቤት እየተመለሰ ነበር የተኩስ እሩምታ መሃል ራሱን ያገኘው። የትከሻ አጥንቱም በጥይት ተመታ።

"መንግስት ቢረጋጋ እና ጥሩ የወጣቶች መርሃ ግብሮችን ቢተገብር ወጣቶች ወሮበሎቹን አይቀላቀሉም ነበር ብዬ አስባለሁ" ሲል መዲናዋን እያሸበሩ ከሚገኙት መካከል ከፍተኛውን ድርሻ ስለሚይዙት ወጣቶች ይናገራል።

እየጨመረ የመጣውን ሁከት ለመቆጣጠር በሚልም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እአአ በ2023 የመልቲናሽናል ሴኪውሪቲ ሰፖርት ሚሽን (ኤምኤስኤስ) እንዲቋቋም ፈቀደ።

በዋነኛነት በዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት እና በኬንያ የሚመራ ጦር ህግ እና ስርዓትን ለማስፈን ከስድስት ወራት በፊት ወደ ሄይቲ ተሰማርቷል።

በመሐል በፖርት አው ፕሪንስ በጥበቃ ላይ መሆናቸው የወሮበሎች ጥቃት አስከፊነት የሚገልጽ ነው።

የኬንያ ወታደሮች በብረት ለበስ ተሽከርካሪ ሆነው አሁን ጭር ባሉት ጎዳናዎች ላይ ወዲያ ወዲህ ይላሉ።

በከባድ የታጠቁ የሰው ኃይል አጓጓዦች (ኤ.ፒ.ሲ) በጎዳናዎች ላይ እየነዱ በመዲናዋ አሁን በረሃማ በሆኑ አካባቢዎች በአንድ ወቅት ግርግር ይበዛባቸው ነበር። ሱቆች እና መኖሪያ ቤቶች ተዘግተዋል።

ወሮበሎቹ እንቅስቃሴ ለመገደብ ሲሉ የተቃጠሉ መኪናዎች እና ፍርስራሾች በየጎዳናዎቹ ላይ አስቀምጠዋል።

የከተማዋ ጎዳናዎች

የፎቶው ባለመብት, Jack Garland, BBC

አንዱ መኪና ሲንቀሳቀስ ተኩስ ተከፈተበት።

ጥይቶች ብረት ለበስ መኪናዎቹን ይመቱ ጀመር። የኬንያ ፖሊሶች ከተሽከርካሪው ውስጥ ሆነው በመተኮስ ምላሽ መስጠት ጀመሩ።

ለአንድ ሰዓት ከሚጠጋ የተኩስ ልውውጥ በኋላ መኪናው መንቀሳቀስ ጀመረ።

የወሮበሎቹን ዘግናኝ ጥቃት ለመመልከት ግን ደቂቃዎች ብቻ በቂ ነበሩ። መሐል መንገድ ላይ አንድ ሰው አቃጠሉ።

የኬንያ ጦር አባል እየተኮሰ ምላሽ ሲሰጥ

የፎቶው ባለመብት, Jack Garland, BBC

በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎቹ ከሚገኙ የኬንያ ፖሊሶች አንዱ የሚቃጠለው ግለሰብ በተቀናቃኝ ወሮበላ ቡድን ተይዞ የተገደለ የሌላ ወሮበላ ቡድን አባል አንደሚሆን ጥርጣሬውን ገለጸ። አስከሬኑን አሰቃቂ በሆነ መልኩ የሚያቃጥሉት ለማስጠንቀቅ መሆኑነም አከለ።

በቅኝት ላይ ያሉት የኬንያ ፖሊሶች በፖርት አው ፕሪንስ ጎዳናዎች ላይ ይህን የመሰለ ጭካኔን ማየት ለምደዋል። እነሱም ግን ደክሞናል ይላሉ።

አራት መቶ መኮንኖች በሰኔ ወር ሄይቲ ቦኢደርሱም በቁጥር እጅግ በጣም ተበልጠዋል። የሄይቲ መንግስት በሀገሪቱ 12 ሺህ የታጠቁ የወሮበሎች ቡድን አባላት እንዳሉ በሐምሌ ወር ግምቱን አስቀምጦ ነበር።

ኬንያውያኑ ተጨማሪ የሰው ኃይል እንደሚቀላቀላቸው ቃል ተገብቶላቸዋል። የተባበሩት መንግስታት ተልዕኮውን ሲፈቅድ 2 ሺህ 500 ሰው እንደሚሰማራ ታቅዶ ነበር። ቀሪው የሰው ኃእይል በህዳር ወር ይደርሳል ቢባልም እስካሁን ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም።

ሁኔታው አሳሳቢ ቢሆንም የጦሩ አመራር ግን አሁንም ተስፋ ሰንቀዋል። ኮማንደር ጎድፍሬይ ኦቱንጌ ተልዕኮውን ስኬታማ እንዲያደርጉ ከኬንያ መንግስት ግፊት እየተደረገባቸው ነው።

የኬንያ ተልዕኮ አዛዥ ጎድፍሬይ ኦቱንጌ

የፎቶው ባለመብት, Jack Garland, BBC

በሄይቲ ያለው የኤምኤስኤስ ቡድን "አስደናቂ ድጋፍ" እንዳለውአዛዡ ተናግሯል።

"ህዝቡ ጦሩ እንዲሰፋ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲዳረስ እየጠየቀ ነው" ብለዋል።

በወሮበሎች ተይዞ የነበረውን የቀድሞ የሄይቲ ፖሊስ ጣቢያ አሁን በኬንያ ኃይሎች እጅ ስር ገብቷል።

ፖሊስ ጣቢያው አሁንም ሙሉ በሙሉ በወንበዴዎች በመከበቡ ፖሊሶች ለጥበቃ ወደ ማማ ሲወጡ ተኩስ ይከፈትባቸዋል።

የኬንያ መኮንኖች የአካባቢው ነዋሪን እያስጠነቀቁ እየተኮሱ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጎዳው ያለውን ሁኔታ ይገልጻል

የፎቶው ባለመብት, Jack Garland, BBC

ተጨማሪ ኃይል በዚህ በፈረንጆች ዓመት መጨረሻ እንደሚደርስና ይህም በሄይቲ የሚሰማራውን ቁጥር አንድ ሺህ እንደሚያደርሰው ኬንያውያኑ ያምናሉ።

የሰው ኃይል ማጠመናከሪያው በአስቸኳይ ያስፈልጋል። በፖርት አው ፕሪንስ ውስጥ በወሮበሎች ጥብቅ ቁጥጥር ስር ያሉ እና ፖሊሶች ማይደርሱባቸው አካባቢዎች አሉ።

እንደዚህ ካሉ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ዋርፍ ጀሬሚ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ባሉ ሁለት ቀናት ብቻ ወደ 200 የሚጠጉ ሠላማዊ ዜጎች በአንድ የወሮበሎች ቡድን መሪ ተገድለዋል።

እስከ 100 የሚደርሱ ወሮበሎች በፖርት አው ፕሪንስ አካባቢ እንደሚገኙ ይገመታል። ዕድሜያቸው እስከ ዘጠኝ ያሉ ወንዶችንም ወደ ቡድናቸው ቀላቅለዋል።

ችግሩ እየጨመረ ብቻ ነው የሚመስለው። የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ኤጀንሲ (ዩኒሴፍ) እንደገለጸው ከሆነ በአንድ ዓመት ውስጥ በወሮበላዎቹ የሚመለመሉ ህጻናት ቁጥር በ70 በመቶ ጨምሯል።

ልጆቹ ከሚቀላቀሏቸው የወሮበላ ቡድን መሪዎች አንዱ ቲ ላፕሊ ነው። በትክክለኛ ስሙ ሬኔል ዴስቲና ተብሎ ይጠራል።

የግራን ራቪን የወሮበሎች ቡድን መሪ እንደመሆኑ መጠን ከአንድ ሺህ የሚበልጡ አባላቱን ከፖርት አው ፕሪንስ ከፍ ብሎ ከሚገኘው ዋና ጣብያው ሆኖ ያዛል።

እንደ እሱ ያሉ ወሮበላዎች በሄይቲ የነበረውን አስከፊ ሁኔታ አባብሰውታል። ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል፣ በመድፈር እና በማሸበርም ይታወቃሉ።

ግራን ራቪን ለገንዘብ ተብሎ በሚፈጸም እገታ ዝነኛ ሲሆንበዚህ ተግባሩም በኤፍቢአይ ተፈላጊ ዝርዝር ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

የአንዱ ወሮበላ ቡድን መሪ አንዱ ቲ ላፕሊ ሲሆን ትክክለኛ ስሙ ሬኔል ዴስቲና ነው

የፎቶው ባለመብት, Jack Garland, BBC

እሱና የቡድኑ አባላቶቹ "አገራቸውን በጣም እንደሚወዱ" ቲ ላፕሊ ተናግሯል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ እንደሚያደርስ ስለሚነገረው ግድያ እና አስገድዶ መድፈር ሲጠየቅ አባላቱ "ማድረግ የማይገባቸውን ያደርጋሉ። ምክንያቱም [ተቀናቃኞቻችንም] ተመሳሳይ ነገር በእኛ ላይ ስለሚያደርጉ ነው" ብሏል።

"መንግስት ምንም አይነት ሥራ አይፈጥርም። ምንም አይነት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሌለባት ሀገር ናት፡ የምንኖረው በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ነው፡ በመሠረቱ የወደቀ መንግስት ነው ያለን" ሲል ህጻናት ቡድኑን የሚቀላቀሉበትን ምክንያት ቀላል መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ እሱ ያሉ የወሮበላ ቡድኖች በሄይቲ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ አምኖ መቀበል ግን አልፈለገም። ሰዎች ብዙ ጊዜ ወደ ሥራ ለመሄድ ከመፍራት ባለፈ በየጊዜውም ገንዘብ ይዘረፋሉ።

እንደ ግራን ራቪን ባሉ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት 700 ሺህ ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርገዋል። የመዲናዋ ትምህርት ቤቶችም የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ ሆነዋል።

ኔጎሲያትም መጠለያ ለመፈለግ ከተገደዱ መካከል አንዷ ናት።

ኔጎሲያት (መሐል) ከልጆቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Jack Garland, BBC

ከአምስት ልጆቿ ጋር አሁን ቤታችን ብለው በሚጠሩት የትምህርት ቤት በረንዳ ተቀምጠዋል።

"ከሳምንታት በፊት በራሴ ቤት እኖር ነበር። ሆኖም ወሮበሎቹ ሰፈሬን ተቆጣጠሩት" ብላለች።

ሶሊኖ ወደሚባል የከተማዋ አካባቢ እንደሄደች ገልጻ አካባቢው በወሮበሎች ጥቃት ሲፈጸምበት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ጋር ሸሸች።

"ዛሬም የራሴን እና የልጆቼን ህይወት ለማዳን እየሸሸሁ ነው" ብላለች።